በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Uncategorized

በጨለለቅቱ ከተማ የመጀመርያ ዙር የወጣቶች መርሃግብር ተካሄደ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አባታዊ መመሪያ መሠረት በኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በጨለለቅቱ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በሥነ ምግባር ታንጸው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያግዛቸው የሚረዳቸው ወርኃዊ የወጣቶች መርሃግብር ተከናውኗል። በዕለቱ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት እና አገልግሎት በሚል ርእስ ሥልጠና ተሰጥቷል። በመርሃግብሩ የአድባራቱ አስተዳዳሪ በኩረ ትጉሃን አእምሮ ሙሉ፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አካላት፣ ካህናትና ምዕመናን ተገኝተዋል።

በጨለለቅቱ ከተማ የመጀመርያ ዙር የወጣቶች መርሃግብር ተካሄደ! Read More »

በሀገረ ስብከቱ ሥር ለሚገኙ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም ማኅበረ አቡቀለምሲስ በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሥር ለሚገኙ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የሚሆን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል። ማኅበሩ ይህንን ድጋፍ ያደረገው በተለያዩ ምክንያቶች የመማሪያ ቁሳቁስ ለማሟላት ለተቸገሩ ተማሪዎች ድጋፍ ለማድረግና የመማር እድላቸውን ለማመቻቸት በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል። ለዚሁ የበጎ አድራጎት ተግባር ከአራት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍም 608 ደርዘን ደብተር፣ 50 ደርዘን እርሳስ፣ 50 ደርዘን ላጲስ፣ 50 ደርዘን መቅረጫ እንዲሁም 50 ደርዘን እስክሪብቶ ያካተተ ነው። ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ ለማኅበሩ አባላት እንዲሁም ለተወካዮቹ ለላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ እና ለሰላም አያሌው ምሥጋናቸውን አቅርበዋል። አያይዘውም የተበረከተው ቁሳቁስ ለተያዘለት በጎ ዓላማ ብቻ እንዲውል መመሪያ በመስጠት ድጋፉን ለስድስቱም ወረዳ ቤተ ክህነት አከፋፍለዋል።

በሀገረ ስብከቱ ሥር ለሚገኙ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ! Read More »

ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት የወንጌል አገልግሎት የሚውል ሞንታርቦ ድጋፍ ተደረገ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሥር ለሚገኙ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ለወንጌል ማስፋፊያ አገልግሎት የሚውሉ ስድስት ዘመናዊ የድምፅ መሣሪያዎች (ሞንታርቦ) ድጋፍ ተደረገ። የድጋፍ ቁሳቁሶቹ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው የሀገረ ስብከቱ መማክርት ጉባኤ የተበረከቱ መሆናቸው ተገልጿል። የተበረከቱት እነዚህ የድምፅ ማጉያ፣ ስፒከር እና ሚክሰርን በአንድ ላይ አዋሕደው የያዙት ሞንታርቦዎች በቻርጅ የሚሠሩ፣ ለአጠቃቀም ቀላልና ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ አመች የሆኑ ናቸው። ይህም የኤሌክትሪክ መብራትና የመጓጓዣ መሠረተ ልማት ችግር ባለባቸው የገጠር አካባቢዎች ድምፅ ሳይበታተን ጥራት ባለው መልኩ እንዲሰማ በማድረግ ለሚካሄዱ የወንጌል አገልግሎቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል። ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት የተደረገው ቁሳቁስ በየገጠር አካባቢዎች በሀገር በቀል ቋንቋዎች ለማካሄድ ለታቀደው የወንጌል አገልግሎት እጅግ ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል። ብፁዕነታቸው የተረከቧቸውን ስድስት የድምፅ መሣሪያዎች ለስድስቱ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና ጸሐፍት በአንድነት ያስረከቡ ሲሆንቁሳቁሶቹ ለአገልግሎት የተለዩበትን ዓላማ ብቻ መሠረት አድርገው ጥቅም ላይ እንዲውሉ አሳስበዋል።

ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት የወንጌል አገልግሎት የሚውል ሞንታርቦ ድጋፍ ተደረገ! Read More »

በይርጋጨፌ ደብረ ታቦር አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሩጫ ተከናወነ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት በይርጋጨፌ ደብረ ታቦር አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሩጫ ተከናወነ። በመርሃግብሩ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ኃይማኖት ብዙአየሁ ዳመነ፣ አቶ ዮሴፍ የይርጋጨፌ ከተማ ምክትል ከንቲባ፣ የይርጋጨፌ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ይስማሸዋ ዘለቀ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ሥርዓት አክሊሉ ነጋሽ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ምዕመናን ተገኝተዋል።

በይርጋጨፌ ደብረ ታቦር አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሩጫ ተከናወነ! Read More »

ሀገረ ስብከቱ በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ለሁለት ወር ያሰለጠናቸውን ካህናት አስመረቀ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በአንዲዳ መድኃኔዓለም የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ለሁለት ወራት ሲያሠለጥናቸውን የቆየውን ካህናት አስመርቋል። በመርሃግብሩ በተመራቂ ካህናቱ አቅራቢነት ቅኔዎች፣ ያሬዳዊ ዝማሬዎችና የተለያዩ ሥነ ጽሑፎች ቀርበዋል። በተጨማሪም የመርሃ ግብሩን ተደራሽነትና አካታችነት ባረጋገጠ መልኩ በጌዴኡፋ፣ በኮሪቴ እና በዳሸቴ (Dhashete) ቋንቋዎች መንፈሳዊ መልእክቶች ተ አስተላልፈዋል። ​በሥነ ሥርዓቱ ላይ የማኅበረ አቡቀለምሲስ ተወካይ ላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፣ ተመራቂዎች የተቀበሉትን መንፈሳዊ አገልግሎት በታማኝነትና በትጋት እንዲወጡ አሳስበዋል። ማኅበሩ ተመራቂዎችን ለመደገፍና በቀጣይ የአገልግሎት ዘመናቸው አቅም የሚሆኗቸውን የሃይማኖት መጻሕፍት ስጦታ ያበረከተ ሲሆን ከተበረከቱት መጻሕፍት መካከል መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድምታ ወንጌል እና መድሎተ ጽድቅ ይገኙበታል። ​በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂ ካህናት ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሽልማቶች የተሰጡ ሲሆን ለሁሉም ተመራቂዎች ደግሞ ትምህርታቸውን ማረጋገጣቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) እና ትራንስክሪብት ተበርክቶላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተመራቂዎቹን በትጋት ላሠለጠኑ መምህራን የማበረታቻ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ለመርሃ ግብሩ መሳካትና ለቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት በጎ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ የምስክር ወረቀትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ​በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ መልእክትና መመሪያ አስተላልፈዋል። መልአከ ሕይወት ብርሃኑ በተላለፉት መልእክት ተመራቂዎች ያገኟቸውን እውቀቶች ወደ ተግባር በመለወጥ ምዕመናንን በቅንነትና በእውነት እንዲያገለግሉ አሳስበው መርሃ ግብሩን በጸሎት አጠናቀውታል።

ሀገረ ስብከቱ በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ለሁለት ወር ያሰለጠናቸውን ካህናት አስመረቀ! Read More »

በሁለት ወሩ የካህናት ሥልጠና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እስከ ፕሮጀክት ቀረጻ ድረስ መዳሰሱ በሪፖርቱ ተመላከተ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የመንፈሳዊ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ ለሁለት ወራት በአንዲዳ መድኃኔዓለም የአብነት ትምህርት ቤት ለሁለት ወራት በተሰጠው ሥልጠና የምርቃት መርሃግብር ሪፖርት አቅርበዋል። ኃላፊው እንዳብራሩት ሥልጠናው ከሐምሌ 7 ቀን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ወራት በአንዲዳ መድኃኔዓለም አብነት ትምህርት ቤት የተካሄደ ሲሆን ዓላማውም የካህናቱን ቀኖናዊ፣ ዶግማዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም የአመራር፣ የማኅበረሰብ ምክርና የልማት አቅም ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ 27 ካህናት በአዳሪነት የሠለጠኑ ሲሆን 1 ካህን ከአንዲዳ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በራሳቸው ወጪ በመከታተላቸው በአጠቃላይ 28 ካህናት ሥልጠናውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። በሁለት ወራት ቆይታቸውም ትምህርተ ሃይማኖት፣ አምስቱ አእማደ ምሥጢራት፣ ነገረ ክርስቶስና ነገረ ድኅነት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትና ሥርዓት፣ ነገረ ማርያምና ነገረ ቅዱሳን፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ አንጻራዊ ትምህርተ መለኮት፣ ትምህርተ ኖሎት እና ባሕረ ሐሳብን ጨምሮ 12 ዋና ዋና መደበኛ ኮርሶችን ተምረዋል። ከእነዚህ መደበኛ ኮርሶች ጎን ለጎን የተግባቦት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የምክር አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ኦርቶዶክሳዊ የልጆች አስተዳደግና ጋብቻ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ቃለ አዋዲ እንዲሁም የፕሮጀክት ቀረጻና ሀብት ማሰባሰብ የክህሎትና የአስተዳደር ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል። በተጨማሪም እያንዳንዱ ሠልጣኝ ለሁለት ዙር ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት የስብከት ልምምድ ማቅረባቸውን የተከታታይ ምዘና ሲደረግበት መቆየታቸው ገልጸዋል። ለሥልጠናው መሳካት በሀገረ ስብከቱ በበጎ ፈቃደኝነት እና በቋሚነት ከሰጡት መምህራን በተጨማሪ ከዲላ ውጭ እንደ መጋቤ ሐዲስ ግሩም፣ ላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ፣ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ እና ሊቀ ሊቃውንት ብርሃን ያሉ ሊቃውንት መጥተው ኮርሶችንና ሥልጠናዎችን መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በሁለት ወሩ የካህናት ሥልጠና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እስከ ፕሮጀክት ቀረጻ ድረስ መዳሰሱ በሪፖርቱ ተመላከተ! Read More »

፫ኛው ሀገረ ስብከት አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠናቀቀ!

ኤክቱስ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ርእሰ መንበርነት በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሲካሄድ የዋለው ፫ኛው ሀገረ ስብከት አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠናቋል። በጉባኤው የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የ2018 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በመቀጠልም ቀሲስ ጤናው እንዳላማው የሀገረ ስብከቱን የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ለጉባኤው አቅርበዋል። በቀረቡት የ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ከታዳሚዎች በርካታ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና ጠቃሚ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን ለተነሱት ጥያቄዎች በቂና አጥጋቢ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። በተጨማሪም በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ሀገረ ስብከቱን በበርካታ ነገሮች ሲያግዙና ሲደግፉ ለቆዩት “ማኅበረ አቡቀለምሲስ” ልዩ የእውቅና ምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን በ2018 ዓ.ም ከፍተኛ የሥራ አፈጻጸም ላመጡ የወረዳ ቤተ ክህነቶች የምሥጋና የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በመጨረሻም ጉባኤው በ2019 ዓ.ም የተቀመጡትን አቅጣጫዎች ሙሉ በሙሉ በመቀበልና የጋራ አቋም በመያዝ በብፁዕነታቸው ቃለ በረከትና ጸሎት ፍጻሜ አግኝቷል።

፫ኛው ሀገረ ስብከት አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠናቀቀ! Read More »

ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ 3,558 አዳዲስ አማንያንን እንዳስጠመቀ ገለጸ!

ኤክቱስ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ፫ኛው ዙር ሀገረ ስብከት አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በደመቀ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ከዚህ ቀደም በነበሩ ዜናዎቻችን መግለጻችን ይታወሳል። በጉባኤው ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የ2018 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም አጠቃላይ ሪፖርት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። ክቡር ሥራ አስኪያጁ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፤ ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ 8 ዋና ዋና ስልታዊ ግቦችንና 205 አበይት ተግባራትን አቅዶ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ወንጌልን በማስፋፋት፣ በአብነትና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች፣ በፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻልና በልማት ሥራዎች ላይ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። በዚሁ መሠረት በሀገረ ስብከቱ 3,558 አዳዲስ ምእመናን የተጠመቁ ሲሆን ትምህርተ ወንጌልም በአማርኛ፣ በጌዴኦፋ፣ በኮሪቴና በDhaሸቴ ቋንቋዎች ተደራሽ መደረጉን አስረድተዋል። በካህናት ማብቃትና አብነት ትምህርት ቤቶች በኩል በአንዲዳ መድኃኔዓለም አብነት ት/ቤት ተማሪዎችን ማስመረቅ የተቻለ ሲሆን በ12 ሚሊዮን ብር በጀት የሚገነባው የአብነት ት/ቤት ህንፃ ግንባታ 60% መድረሱ ተገልጿል። በተጨማሪም 111 ደቀ መዛሙርት ማዕረገ ዲቁና እንዲሁም 19 ዲያቆናት ቅስና የተቀበሉ ሲሆን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ቁጥር 11,500 ማድረስ ተችሏል። በፋይናንስና ልማት ዘርፍ የደብል ኢንትሪ የሂሳብ አሠራር በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሙሉ በሙሉ የተተገበረ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የ35% ክፍያ ገቢ በ47.5% ዕድገት ማሳየቱ ተገልጿል። በልማት በኩልም ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶበት ግንባታው 85% የደረሰና ከጥቂት ወራት በኋላ የሚጠናቀቅ ዘመናዊ የመንበረ ጵጵስና ህንፃ፣ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብና ከ25,000 በላይ ችግኞችን የመተከል ልማታዊ ሥራዎች ተከናውነዋል። በማኅበራዊ አገልግሎት በኩል ደግሞ በቡሌና በራጴ ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖችና ለተቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፈጣን ድጋፍ ተደርጓል። መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ በሪፖርታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ የ2018 ዓ.ም ስኬቶች ለቀጣዩ 2019 ዓ.ም የተሻለ ሥራ መነሻ እንደሚሆኑ ጠቁመው በ2019 ዓ.ም “ሙሉ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ የበቁ አገልጋዮች፣ የተደራጀ አስተዳደር፣ የተረጋጋ ፋይናንስና የተጠናከረ ሐዋርያዊ ተልእኮ” ትኩረት የሚሰጣቸው ዋና ዋና አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ 3,558 አዳዲስ አማንያንን እንዳስጠመቀ ገለጸ! Read More »

ለብፁዕ አቡነ ገሪማ የክብር አምባሳደርና የእውቅና ሽልማት ተበረከተላቸው!

ኤክቱስ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም ለብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከቢታንያ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የእውቅናና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበረከተላቸው። ሽልማቱ የተበረከተላቸው በዛሬው ዕለት ኮሌጁ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት ታላቅ መርሃ ግብር ላይ ነው። ቢታንያ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ትምህርትና ሙያ ከማስተማር ባሻገር፣ ለማኅበረሰቡ ሰላም፣ አብሮነት፣ መተሳሰብና ሁለንተናዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ግለሰቦችንና ተቋማትን ማክበርና ማመስገን እንደሚገባው ባመነው መሠረት ይህንን እውቅና መስጠቱ ተገልጿል። ብፁዕነታቸው ወደ አካባቢው በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ከተመደቡበት ጊዜ አንስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሃይማኖታዊ አገልግሎት ባሻገር ለማኅበረሰቡ ሰላም፣ አብሮነትና ልማት በርካታ አወንታዊ ተግባራትን ማከናወናቸውን የመርሃግብሩ መሪ በንግግራቸው አሳትውቀዋል። በተለይም በበጋና በክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት በመሳተፍ፣ አቅመ ደካሞችንና አስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉ ወገኖችን በማስተባበር፣ የቤት ግንባታን ጨምሮ ከኪስ ገንዘባቸውና ከጉልበታቸው በመለገስ ላከናወኗቸው የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከፍተኛ አድናቆት ተሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም በሃይማኖት ተቋማት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በማበራታትና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ማኅበራዊ ሀላፊነት ጋር በማጣመር ሃይማኖት ለሰላምና ለልማት ያለውን አወንታዊ ሚና በተግባር ማሳየታቸውና ለትውልዱ መልካም አርአያ መሆናቸው ተመልክቷል። በመሆኑም ቢታንያ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ብፁዕነታቸው ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለማኅበረሰብ ድጋፍ ላደረጉት ላቅ ያለ አስተዋጽዖ ያለውን አድናቆትና ምስጋና ለመግለጽ የዛሬውን የምስክር ወረቀትና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።

ለብፁዕ አቡነ ገሪማ የክብር አምባሳደርና የእውቅና ሽልማት ተበረከተላቸው! Read More »

ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመንፈሳዊ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ!

ኤክቱስ ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት የዕረፍት መታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀው መንፈሳዊ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። ይህ መርሃ ግብር ተግባራዊ ክርስትና በተግባር የታየበት ጉባኤ ሆኖ አልፏል። በጉባኤው ወቅት መጋቤ ጥበባት መምህር ኤርምያስ እንዳሻው እና መምህር ሙሉዓለም ዐባይ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን በዝማሬ ደግሞ ዘማሪ ዕዝራ ኃይለሚካኤል በአማርኛ ቋንቋ፣ ዘማሪ ጌታሁን ታደሰ እና ዘማሪት የአብሥራ መለሰ በጌዴኡፋ ቋንቋ መንፈሳዊ መዝሙራትን አቅርበዋል። ዘማሪ ኃይለአብ ግርማ ደግሞ በዜማ መሣሪያ ሲያገለግል ቆይቷል። በጉባኤው ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል እርስ በእርስ ተጣልተው የነበሩ ምዕመናን በብፁዕነታቸው ጥሪ በታማኝነት ወደ ዐውደ ምሕረት በመውጣት እርቅ እንዲፈጽሙ የተደረገበት ይገኝበታል። በተጨማሪም በሀገራችን ወቅቱን የጠበቀ ዝናም አለመኖሩን ምክንያት በማድረግ በብፁዕነታቸው መሪነት በታቦቱ ፊት ጸሎተ ምሕላ የተደረገ ሲሆን የምሕረት አምላክ ዝናመ ምሕረቱን እንዲልክ በመማጸን ጸሎተ ምሕላው ተከናውኗል። በሌላ በኩል በማጠቃለያው ቀን በማታው መርሃግብር የንሥሐ አባት ያልነበራቸው ሃያ ስምንት ምዕመናን የንሥሐ አባት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህም ምዕመናኑ በምክረ ካህን እየተመሩ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጸኑ ለማስቻል የተከናወነ የመንፈሳዊ አገልግሎት አካል ነው።

ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመንፈሳዊ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ! Read More »

Scroll to Top