በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ 3,558 አዳዲስ አማንያንን እንዳስጠመቀ ገለጸ!

ኤክቱስ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ፫ኛው ዙር ሀገረ ስብከት አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በደመቀ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ከዚህ ቀደም በነበሩ ዜናዎቻችን መግለጻችን ይታወሳል። በጉባኤው ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የ2018 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም አጠቃላይ ሪፖርት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።

ክቡር ሥራ አስኪያጁ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፤ ሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ 8 ዋና ዋና ስልታዊ ግቦችንና 205 አበይት ተግባራትን አቅዶ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን ወንጌልን በማስፋፋት፣ በአብነትና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች፣ በፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻልና በልማት ሥራዎች ላይ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። በዚሁ መሠረት በሀገረ ስብከቱ 3,558 አዳዲስ ምእመናን የተጠመቁ ሲሆን ትምህርተ ወንጌልም በአማርኛ፣ በጌዴኦፋ፣ በኮሪቴና በDhaሸቴ ቋንቋዎች ተደራሽ መደረጉን አስረድተዋል።

በካህናት ማብቃትና አብነት ትምህርት ቤቶች በኩል በአንዲዳ መድኃኔዓለም አብነት ት/ቤት ተማሪዎችን ማስመረቅ የተቻለ ሲሆን በ12 ሚሊዮን ብር በጀት የሚገነባው የአብነት ት/ቤት ህንፃ ግንባታ 60% መድረሱ ተገልጿል።

በተጨማሪም 111 ደቀ መዛሙርት ማዕረገ ዲቁና እንዲሁም 19 ዲያቆናት ቅስና የተቀበሉ ሲሆን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ቁጥር 11,500 ማድረስ ተችሏል።

በፋይናንስና ልማት ዘርፍ የደብል ኢንትሪ የሂሳብ አሠራር በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሙሉ በሙሉ የተተገበረ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የ35% ክፍያ ገቢ በ47.5% ዕድገት ማሳየቱ ተገልጿል።

በልማት በኩልም ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጥቶበት ግንባታው 85% የደረሰና ከጥቂት ወራት በኋላ የሚጠናቀቅ ዘመናዊ የመንበረ ጵጵስና ህንፃ፣ የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብና ከ25,000 በላይ ችግኞችን የመተከል ልማታዊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በማኅበራዊ አገልግሎት በኩል ደግሞ በቡሌና በራጴ ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖችና ለተቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፈጣን ድጋፍ ተደርጓል።

መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ በሪፖርታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ የ2018 ዓ.ም ስኬቶች ለቀጣዩ 2019 ዓ.ም የተሻለ ሥራ መነሻ እንደሚሆኑ ጠቁመው በ2019 ዓ.ም “ሙሉ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ የበቁ አገልጋዮች፣ የተደራጀ አስተዳደር፣ የተረጋጋ ፋይናንስና የተጠናከረ ሐዋርያዊ ተልእኮ” ትኩረት የሚሰጣቸው ዋና ዋና አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

Scroll to Top