በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Public Relation

“የአትትዎ ለኀጥእ ከመኢይርአይ ስብሐተ እግዚአብሔር – የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ኀጢአተኛውን ሰው ያርቁታል”ኢሳ ፳፮፥፲

ቃሉን የተናገረው ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ ሲሆን ለጊዜው ለሰናክሬምና ለአሥሩ ነገድ የተነገረ ነው።ፍጻሜው ግን ለይሁዳ የተነገረ ነው። ይሁዳ በስም ተስፋ በግብር ዘለፋ የሆነ ያልታደለ ፍጡር ነው (ማቴ26፥24) የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት ፣እምነትና ቅድስና ያስፈልጋል። ያለ እምነትና ያለቅድስና የእግዚአብሔር የክብሩ ተካፋይ መሆን አይቻልም። (ዕብ11፥6) እግዚአብሔር ጻድቀ ባሕር፣ ንጹሐ ባሕርይ ነውና ያላመነ ልቡና ፣ ንስሓ ያልገባ ሰብእና  ያለውን ሰው ኀጢአት ግድግዳም ሆኖ ፣ ገደልም ሆኖ ከእግዚአብሔር ያርቀዋል (ሉቃ16፥26) የእግዚአብሔርን ክብር አያያም።  በዛሬው በዓል አዕማድ ተብለው የሚጠሩት (ገላ3፥9) የእምነት ፣የፍቅርና የወንጌል ሰዎች ቅዱስ ጴጥሮስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብ   የእግዚአብሔርን ክብር ያዩበት፣ የእምነት የፍቅር፣ የንስሓ ሰው ያልሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ ደግሞ የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ኀጢአት  ከእግዚአብሔር የማያገናኝ ገደል ሆኖ አርቆታል። የእግዚአብሔር ክብር ወደሚገለፅበት ተራራ  መውጣት አልቻለም። ይሁዳ ብቻ  ሳይሆን 8ቱ ደቀ መዛሙርትም ክብሩን ቢያዩም ወደተራራው እንዳይወጡ የሆኑበት ምክንያት የይሁዳ ኀጢአት ነው። የእኛ ኀጢአት ከእኛ ባለፈ ለሌላውም ይተርፋል። “ለኀጥአን የወረደ ለጻድቃን ይተርፋል” አይደል የሚባለው? በዓሉ ከጌታ 9 ዐበይት በዓላት አንዱ ነው የበዓሉ ስያሜም ደብረታቦር ይባላል ደብረ ታቦር ማለትም  ታቦር የሚባል ተራራ ማለት ነው። ማቴዎስ ፣ማርቆስና ሉቃስ ረዥም ተራራ ከማለት በቀር ታቦር ብለው አልገለፁም ዮሐንስ ጨርሶ ከነታሪኩ አያነሣም ቅዱስ ጴጥሮስም  “በቅዱሱ ተራራ ሳለን”2ኛ ጴጥ1፥18 አለ እንጂ ታቦር ብሎ አልነገረንም የሐዋርያት ሲኖዶስና የቤተክርስቲያን ትውፊት  ታቦር እንደሆነ ያስረዳሉ። ነቢዩ ዳዊትም “ታቦር ወአርሞንኤም ይትፌሥሑ በስመ ዚኣከ”ብሎ አንሥቶታል። በዚህ በዓል የምናከብረው ታራራውን አይደለም ።ጴጥሮስ ቅዱሱ ተራራ ብሎ እንደጠራው የእግዚአብሔር ክብር የተገለጠበት የአብ ድምፅ የተሰማበት  የብሉይኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ቅዱሳን የተገናኙበት የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የሆነ ቅዱስ ሥፍራ ቢሆንም  በዓሉ የተራራው አይደለም።በዓላትን ቤተክርስቲያን በሦስት መንገድ ስያሜ ትሠጣለች አንደኛ ቀጥታ ስምን በመውሰድ ነው  በስም ሚካኤል፣ ገብርኤል ፣ አማኑኤል ሁለተኛ በድርጊት ፅንሰት፣ልደት፣ስቅለት ሦስተኛ በቦታ ቁስቋም፣ደብረ ዘይት ፣ደብረ ታቦር ይባላል ከቅኔ ቤት ትውስታዬ  የደብረ ታቦር በዓል ጊዜ አንድ ተማሪ ለአንድ መነኩሴ የተቆረሰ ዳቦ አንሥቶ ስለደብረ ታቦር አላቸው እሳቸውም ተራራው ይሥጥልኝ ብለው ተቀበሉ  የምንዘክረው ታራራውን ሳይሆን ክርስቶስን ነው ማለታቸው ነበር።ይህ ተራራ ከገሊላ ተራራ በምዕራብ በኩል 10 ኪሎ ሜትር የራቀ ሲሆን ከባሕር ወለል በላይ 572 ሜትር ከፍታ ያለው፣ የተራራው አናት 1000 ሜትርበ400 ሜትር ስፋትያለው ደልዳላ መስክ ያለበት ተራራ  እንደሆነ ባለሙያዎች ይገናገራሉ። ነገደ ዛብሎን፣ነገደ ንፍታሌምና ነገደይሳኮር የሚገናኙበትነው።ታሪኩ በማቴ 17፥1-9 በማር9፥1በሉቃ 9፥28  እንደተመዘገበው  ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደረዥም ተራራ ወጣ  በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደፀሐይ በራ ልብሱም እንደብርሃን ነጭ ሆነ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ  ታዩኣቸው ጴጥሮስም በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው አለ አብም በብሩህ ደመና ሆኖ የምደወው ልጄ ይህነው እርሱን ስሙት አለ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበርኢየሱስም  ዳሶ ተነሱ አትፍሩም  አላቸው ቀና ብለው ሲያዩም ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን አንድ ለአንተ አንድ ለሙሴ፣አንድ ለኤልያስ ዳስ ሠርተን በዚህ መኖር መልካም ነው ብሎ የተናገረለት ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነውከብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሙሴና ኤልያስ ከሐዲስ ኪዳን ቅዱሳን ጴጥሮስ ያዕቆብና ዮሐንስ፣ከደናግል ኤልያስና ዮሐንስ ከሕጋውያን ሙሴና ጴጥሮስ ከጌታ  ጋር መገኘታቸው ቤተክርስቲያን የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ኅብረት መሆኗን ያሳያል  በደብረ ታቦር ቅዱሳን እንደተገኙ ቤተክርስቲያም የምእመናን መገኛ ናት።በደብረ ታቦር የእግዚአብሔር ክብር እንደተገለፀ ቤተክርስቲያንም የእግዚአብሔር ክብር የሚገለፅባት ናት። ይሁዳ ወደብረ ታቦር ባለመውጣቱ ምሥጢር እንደተሠወረበት ወደቤተክርስቲያን የማይመጣ ምእመንም ከምሥጢራት የራቀ ይራቀ ይሆናል። ይሁዳን ከዚህ ኅብረት የለየ ኀጢአት እኛንም ኀጢአት ከቤተክርስቲያን ኅብረት እንዳይለየን! የምሕረት አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቀን። ሊቀ ማእምራን ሰሎሞን ፈጠነየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከትየሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ

“የአትትዎ ለኀጥእ ከመኢይርአይ ስብሐተ እግዚአብሔር – የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ኀጢአተኛውን ሰው ያርቁታል”ኢሳ ፳፮፥፲ Read More »

መልአከ ሰላም ድረስ ታደሰ የዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው ተመደቡ!

ኤክቱስ ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መልካም ፈቃድ መልአከ ሰላም ድረስ ታደሰ የዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው ተመድበዋል። በዕለቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውዳሴ እና ቅዳሴ ከተተረጎመ በኋላ ጸሎተ ወንጌል የተነበበ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የዕለቱን ወንጌል አስተምረው ደብዳቤውን አንብበዋል። ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ሰንበት ትምህርት ቤትን በማጠናከር፣ የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት፣ ማኅበረ ካህናትንና ምዕመናንን በፍቅር በአንድነት መምራት እንደሚገባ እንዲሁም ምዕመናን ከአዲሱ አስተዳዳሪ ጋር በመሆን በአንድነት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። በመቀጠል አዲሱ የደብሩ አስተዳዳሪ ትውውቅ አድርገዋል። በዕለቱ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጠበብት መሠረት ይልማ፣ የደብሩ ካህናትና መምህራን፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አካላት እንዲሁም ምዕመናን ተገኝተዋል።

መልአከ ሰላም ድረስ ታደሰ የዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው ተመደቡ! Read More »

የዲላ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም ለጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የምስጋናና የእውቅና ምስክር ወረቀት አበረከተ!

ኤክቱስ ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም የዲላ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በተለያዩ ጊዜያት ለተቋሙ ላደረገው የቁሳቁስ ድጋፍና ለሰጠው ሃይማኖታዊ አገልግሎት እውቅና በመስጠት የምስጋናና የምስክር ወረቀት አበረከተ። የተዘጋጀውን የእውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከተቋሙ አዛዥ ከኢንስፔክተር ትእግስት ሮቤ ተረክበዋል። በስነ ሥርዓቱ ወቅት ተቋሙ ሀገረ ስብከቱ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማቅረብና ሃይማኖታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ላበረከተው አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ይህ አዎንታዊና ድጋፍ ሰጪ አጋርነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ የቀረበበት መልእክት ተካቷል። ብፁዕ አቡነ ገሪማ የምስጋና ምስክር ወረቀቱን ከተረከቡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት ቤተ ክርስቲያን የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት ተደራሽነቷን በማስፋፋት በማረሚያ ቤት የሚገኙ ወገኖች በሥነ-ምግባር ታንጸውና ተስፋ ሰንቀው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የምታደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የዲላ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም ለጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የምስጋናና የእውቅና ምስክር ወረቀት አበረከተ! Read More »

በዲላ ማረሚያ ተቋም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲማሩ የቆዩ የሕግ ታራሚዎች ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት ተመረቁ!

ኤክቱስ ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ የሕግ ታራሚዎች በተጠናከረ መልኩ በዘረጋው የትምህርት መርሃ ግብር መሠረት ላለፉት ስድስት ወራት የመንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የሕግ ታራሚዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ተመረቁ። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በመገኘት ለተመራቂዎቹ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል። በዕለቱ የምርቃት መርሃ ግብር ላይ መምህር ያሬድ አደመ ለቦታው የሚሆን ትምህርት በሰፊው አስተምረዋል። ተመራቂዎቹ በስድስት ወራት የትምህርት ቆይታቸው ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ነገረ ማርያም እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ተከታተለዋል። ይህም በማረሚያ ቤት በቆዩበት ጊዜ ያገኟቸው መንፈሳዊና ሥነ-ምግባራዊ እውቀቶች ለቀጣይ ሕይወታቸው መልካም ዜጋ ሆነው እንዲወጡና ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑ ተገልጿል። በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የዲላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኢንስፔክተር ትእግስት ሮቤ፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን እሸቱ ዋለ እንዲሁም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አባላት ተገኝተዋል። በመርሃግብሩ ንግግር ያደረጉት የዲላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኢንስፔክተር ትእግስት ሮቤ የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት በሚኖራቸው ቆይታ በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲወጡ መንፈሳዊ ትምህርት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም ብፁዕ አቡነ ገሪማ ወደ ሀገረ ስብከቱ ከተመደቡ በኋላ የማረሚያ ቤት መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል። ብፁዕነታቸው በበኩላቸው ለማረሚያ ተቋሙ ምስጋና አቅርበው፣ ተመራቂዎች ያገኙትን መንፈሳዊ እውቀት በስብዕናቸውና በአኗኗራቸው በመግለጥ በበጎ መንገድ እንዲመላለሱ አባታዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል። ማረሚያ ቤቶች የቅጣት ቦታዎች ብቻ ሳይሆኑ የሥነ-ምግባር፣ የሃይማኖትና የዕውቀት መማሪያ ተቋማት እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑንም አስረድተዋል። በመጨረሻም በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተመራቂ የሕግ ታራሚዎች የማጠናቀቂያ ምስክር ወረቀትና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን ለማረሚያ ተቋሙ፣ ትምህርቱን ላስተማሩ መምህራን እና ለወረዳ ቤተ ክህነቱ የምሥጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ መርሃ ግብሩ በብፁዕነታቸው ጸሎተ ቡራኬ ተጠናቋል።

በዲላ ማረሚያ ተቋም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲማሩ የቆዩ የሕግ ታራሚዎች ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት ተመረቁ! Read More »

ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በኮቾሬ፣ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የጻድቁ የአቡነ ተክለኃይማኖትን በዓለ እረፍት ምክንያት በማድረግ ከነሐሴ 22 እስከ ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም ድረስ ዐቢይ መንፈሳዊ ጉባኤ ስለተዘጋጀ ሁላችሁም እንድትሳተፉ መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን! ኤክቱስ ነሐሴ 09/2018 ዓ.ም

ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ Read More »

«ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች» ቅዱስ ያሬድ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቁ ሊቅና የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በደረሳቸው ድርሰቶቹ ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅድስና፣ ክብርና ነገረ ድኅነት በጥልቀት ካስተማራቸው መካከል «ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ» (ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች) በማለት የተናገረው ምስክርነት የቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ማርያም መሠረታዊ መግለጫ ነው። ይህ ታላቅ መለኮታዊ ትምህርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሰው ልጅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ያላትን ልዩና አምላካዊ ምርጫ ያመላክታል። ቅዱስ ያሬድ እመቤታችንን «ነጭ ዕንቁ» ብሎ ሲመስላት፣ የንጽሕናዋን፣ የድንግልናዋን፣ የቅድስናዋንና ከማንኛውም የኃጢአት እርኩሰት የተጠበቀች መሆኗን ለመግለጽ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር» (ኢሳይያስ 1:9) ብሎ የተናገረው ያ ዘር ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገረ ትንቢት ነው። የሰው ልጅ ባሕርይ በኃጢአት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ እግዚአብሔር አምላክ ዓለም ሳይፈጠር በነበረው ዘለዓለማዊ እቅዱ መሠረት እመቤታችንን ንጽሕት አድርጎ አዘጋጃት። ይህ በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እቅድ የተዘጋጀው ድንቅ የድኅነት ዘርና የነጭ ዕንቁ ምሳሌ በታሪክ ውስጥ በተግባር ይገለጥ ዘንድ መነሻ የሆነው የጻድቃኑ የኢያቄምና የሐና የታመነ ሕይወት እንዲሁም የተስፋ ጸሎት ነበር። ቅዱስ ኢያቄምና የቅድስት ሐና በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት የሚመላለሱ፣ ሕጉን የሚያከብሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ፤ የከበረች ሐናም መካን ነበረች። በዚያ ዘመን በእስራኤል ዘንድ ልጅ አለመውለድ ታላቅ ነቀፌታና ውርደት ነበር። «ልጅ ያልወለደ ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው» እያሉ ያቀልሏቸው፣ ይነቅፏቸውም ነበር። ጻድቃኑ ግን በዚህ ሳይከፉ ይልቁንም ዘወትር በቤተ መቅደስ ተገኝተው ዕንባቸውን እያፈሰሱ ወደ እግዚአብሔር መማጸናቸውን አላቋረጡም። «ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ብንወልድ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ እናደርገዋለን» ብለው ስዕለትን ተሳሉ፤ በጽናትም ጸለዩ።  ሐናም «አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ! እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ፤ ስማኝ፣ ለዓይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማኅፀኔን ፍሬ ስጠኝ» ብላ ስትለምን ዋለች። ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት ዓይታ በተሰበረ ልብ ሆና «አቤቱ ጌታዬ ለዚች እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለእኔ ልጅ ነሳኸኝ?» በማለት ምርር ብላ አለቀሰች። ኢያቄምና ሐና ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ካህኑ ዘካርያስ ዘንድ ሄዱ። የስዕለታቸውን ነገር ነገሩት፦ «አቤቱ ጌታችን ሆይ! ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ውኃ ቀድታ፣ መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ፣ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን» አሉ። ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስም እጆቹን ዘርግቶ «እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ፤ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ፤ የልቡናችሁን መሻት ይፈጽምላችሁ!» ብሎ በቡራኬ ሸኛቸው።  ከዚህ በኋላ ሁለቱም ዕለቱን ድንቅ ራእይ አዩ፡፡ ቅዱስ ኢያቄም ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ርግብ ወርዳ በሐና ራስ ላይ ስታርፍ፣ በጆሮዋም ገብታ በማኅፀኗ ስትተኛ ራእይ አየ። ቅድስት ሐናም  የኢያቄም መቋሚያ ለምልማ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት ራዕይን አየች። ይህንን ራእይ ከተነጋገሩ በኋላ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለማዘጋጀት ተስማሙ። «አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለእኛስ ይልክልን የለምን?» ብለው መኝታ ለይተው ለ፯ ቀን ያህል በጸሎትና በጾም ሰነበቱ። ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ቅዱስ ገብርኤል ለጻድቁ ኢያቄም በተራራ ላይ ሳለ ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፦ «ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች፤ ዓለም ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን፣ የብዙዎችም ዐይነ ልቡናቸው በእርሷ የሚበራላቸውን፣ በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች» አለው። ለሐናም ተገልጦ «ከሰው የበለጠች፣ ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ» ብሎ አበሰራቸው። በዚሁ ዕለት ነሐሴ ፯ ቀን በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በብሥራተ መልአክ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሐና ማኅፀን ተፀነሰች! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያንም ይህን ቀን «ፅንሰታ ለማርያም»በማለት በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዓለም ድኅነት የተዘጋጀች ታላቅ የካሳ መሠረት ናት። እግዚአብሔር አምላክ ለዳዊት በማህላ የተናገረው የታመነ ቃል ፍጻሜ አገኘ፦ «እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ፥ አይጸጸትምም፥ ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ» (መዝሙር 132:11)። ከዳዊት ወገን የተገኘችው እመቤታችን፣ የዚሁ የመለኮታዊ ቃል ኪዳን ፍሬና የክርስቶስ የማኅፀን ማደሪያ ለመሆን የተመረጠች ናት። አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ የእመቤታችንን ንጽሕናና የፅንሰቷን ቅድስና ሲገልጥ እንዲህ ብሏል፦ «ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ»(ድንግል ሆይ! በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ):: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነች፣ የመላእክት አክሊል፣ የነቢያት ትንቢት፣ የሐዋርያት ሞገስ፣ የዓለም ሁሉ ቅድስና ናት። እርሷ በቅድስናዋና በትሕትናዋ ምክንያት የእግዚአብሔርን ዓይን ሳበች፤ የራሷም ትሕትና ሲገልጥ ራሷ እመቤታችን፦ «የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና፤ እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል» (ሉቃስ 1:48) በማለት ተናግራለች። ጻድቃኑ ኢያቄምና ሐና ከሰው የደረሰባቸውን መነቀፍና ውርደት በትዕግሥት አልፈው በጸሎት፣ በጾም፣ በዕንባና በሕግ በሆነ ቅዱስ ጋብቻ ለእግዚአብሔር በመታመናቸው እግዚአብሔር የታመነ አምላክ መሆኑንና የዓመታት ዕንባን አይቶ በራሱ ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጥ እናስተውላለን፡፡ ስለሆነም ዛሬ በሕይወታችን በመካንነት፣ በሕመምና በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ የምንገኝ ወገኖች ተስፋ ሳንቆርጥ በተሰበረና ንጹሕ ልብ ወደ ፈጣሪያችን ልንመላለስ ይገባል። በተጨማሪም ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን በረከትና ስጦታ ልጅን፣ ሀብትንና ዕውቀትን መልሰን ለእግዚአብሔር ቤትና ለምስኪኖች በመስጠት፣ ልጆቻችንንም በእግዚአብሔር ፍርሃት በማሳደግ የተሳልነውን የስዕለት ክፍያ ልንፈጽም ይገባናል፡፡ እመቤታችን በአዳም ባሕርይ ውስጥ ያበራች ነጭ ዕንቁ እንደሆነች ሁሉ፣ እኛም የክርስቶስ አካላትና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች በመሆናችን ማንነታችንን ከኃጢአት ጠብቀን ልባችንን፣ ጆሯችንንና ዓይናችንን ለቅድስናና ለእግዚአብሔር ቃል የተከፈተ በማድረግ በቅድስና ልንመላለስ ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ የቅዱስ ኢያቄምንና የቅድስት ሐናን ጸሎት የሰማ፣ የልቡናቸውን መሻት የፈጸመ አምላክ፤ ዛሬም የእያንዳንዳችንን የልባችንን በጎ መሻት ይፈጽምልን። የሕይወታችንን መካንነትና የልባችንን ድርቀት አስወግዶ መንፈሳዊ ፍሬ እንድናፈራ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷና አማላጅነቷ አይለየን። ቀሲስ ጤናው እንዳላማውየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የፕሮጀክት ማናጀር

«ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች» ቅዱስ ያሬድ Read More »

ሦስት አዳዲስ አማንያን በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት አገኙ!

ኤክቱስ ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በዲላ ሰዓሊተ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሦስት አዳዲስ አማንያን በዛሬው ዕለት ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል።

ሦስት አዳዲስ አማንያን በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት አገኙ! Read More »

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ከዚህ በታች ባለው ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟላ ሠራተኛ አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል።

ኤክቱስ ነሐሴ 4/2018 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ከዚህ በታች ባለው ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟላ ሠራተኛ አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል። Read More »

መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ታደሰ (ቆሞስ) የይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው ተመደቡ!

ኤክቱስ ነሐሴ 3/2018 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መልካም ፈቃድ መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ታደሰ (ቆሞስ) በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት የይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው ተመድበዋል። በዕለቱ የትውውቅ መርሃግብር የተደረገ ሲሆን መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ ደብዳቤውን ያነበቡ ሲሆን ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ሰንበት ትምህርት ቤትን በማጠናከር፣ የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት፣ ማኅበረ ካህናትንና ምዕመናንን በፍቅር በአንድነት መምራት እንደሚገባ እንዲሁም ምዕመናን ከአዲሱ አስተዳዳሪ ጋር በመሆን በአንድነት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። የዕለቱን ትምህርት አዲሱ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ታደሰ (ቆሞስ) አስተምረው ትውውቅ አድርገዋል። በዕለቱ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ፥ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ኃይማኖት ብዙአየሁ ዳመነ፣ የደብሩ ካህናትና መምህራን፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አካላት እንዲሁም ምዕመናን ተገኝተዋል።

መልአከ ምሕረት አባ ሀብተ ማርያም ታደሰ (ቆሞስ) የይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው ተመደቡ! Read More »

የዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት 6ተኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ!

ኤክቱስ ነሐሴ 02/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት 6ተኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን በዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ፍሬ ተዋሕዶ ሰንበት ትምህርት ቤት አደራሽ አካሂዷል ። በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቱ አጠቃላይ ሪፓርተር እና የየአድባራቱ የሥራ ክንውን ሪፓርት የቀርበ ሲሆን በቀረበው ሪፓርት ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በጉባኤው የተነሱ ጠንካራ የሥራ ተሞክሮዎችን አድባራት በመውሰድ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮችን በትኩረት ተመልክቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጠበብት መሠረት ይልማ በመርሃግብሩ ላይ ተናግረዋል። በጉባኤው የሀገረስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ ፣ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን እሸቱ ዋለ፣ የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤ አስተዳደር አካላትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት 6ተኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ! Read More »

Scroll to Top