በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

«ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች» ቅዱስ ያሬድ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቁ ሊቅና የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በደረሳቸው ድርሰቶቹ ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅድስና፣ ክብርና ነገረ ድኅነት በጥልቀት ካስተማራቸው መካከል «ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ» (ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች) በማለት የተናገረው ምስክርነት የቤተ ክርስቲያናችን ነገረ ማርያም መሠረታዊ መግለጫ ነው። ይህ ታላቅ መለኮታዊ ትምህርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሰው ልጅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ያላትን ልዩና አምላካዊ ምርጫ ያመላክታል። ቅዱስ ያሬድ እመቤታችንን «ነጭ ዕንቁ» ብሎ ሲመስላት፣ የንጽሕናዋን፣ የድንግልናዋን፣ የቅድስናዋንና ከማንኛውም የኃጢአት እርኩሰት የተጠበቀች መሆኗን ለመግለጽ ነው።

ነቢዩ ኢሳይያስ «የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር» (ኢሳይያስ 1:9) ብሎ የተናገረው ያ ዘር ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገረ ትንቢት ነው። የሰው ልጅ ባሕርይ በኃጢአት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ እግዚአብሔር አምላክ ዓለም ሳይፈጠር በነበረው ዘለዓለማዊ እቅዱ መሠረት እመቤታችንን ንጽሕት አድርጎ አዘጋጃት። ይህ በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እቅድ የተዘጋጀው ድንቅ የድኅነት ዘርና የነጭ ዕንቁ ምሳሌ በታሪክ ውስጥ በተግባር ይገለጥ ዘንድ መነሻ የሆነው የጻድቃኑ የኢያቄምና የሐና የታመነ ሕይወት እንዲሁም የተስፋ ጸሎት ነበር።

ቅዱስ ኢያቄምና የቅድስት ሐና በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት የሚመላለሱ፣ ሕጉን የሚያከብሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ፤ የከበረች ሐናም መካን ነበረች። በዚያ ዘመን በእስራኤል ዘንድ ልጅ አለመውለድ ታላቅ ነቀፌታና ውርደት ነበር። «ልጅ ያልወለደ ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው» እያሉ ያቀልሏቸው፣ ይነቅፏቸውም ነበር። ጻድቃኑ ግን በዚህ ሳይከፉ ይልቁንም ዘወትር በቤተ መቅደስ ተገኝተው ዕንባቸውን እያፈሰሱ ወደ እግዚአብሔር መማጸናቸውን አላቋረጡም።

«ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ብንወልድ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ እናደርገዋለን» ብለው ስዕለትን ተሳሉ፤ በጽናትም ጸለዩ።  ሐናም «አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ! እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ፤ ስማኝ፣ ለዓይኔ ማረፊያ ለልቤ ተስፋ የምትሆነኝ የተባረከች ሴት ልጅ የማኅፀኔን ፍሬ ስጠኝ» ብላ ስትለምን ዋለች። ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት ዓይታ በተሰበረ ልብ ሆና «አቤቱ ጌታዬ ለዚች እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለእኔ ልጅ ነሳኸኝ?» በማለት ምርር ብላ አለቀሰች።

ኢያቄምና ሐና ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ካህኑ ዘካርያስ ዘንድ ሄዱ። የስዕለታቸውን ነገር ነገሩት፦ «አቤቱ ጌታችን ሆይ! ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ውኃ ቀድታ፣ መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ፣ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን» አሉ።

ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስም እጆቹን ዘርግቶ «እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ፤ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ፤ የልቡናችሁን መሻት ይፈጽምላችሁ!» ብሎ በቡራኬ ሸኛቸው።  ከዚህ በኋላ ሁለቱም ዕለቱን ድንቅ ራእይ አዩ፡፡ ቅዱስ ኢያቄም ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ርግብ ወርዳ በሐና ራስ ላይ ስታርፍ፣ በጆሮዋም ገብታ በማኅፀኗ ስትተኛ ራእይ አየ። ቅድስት ሐናም  የኢያቄም መቋሚያ ለምልማ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት ራዕይን አየች።

ይህንን ራእይ ከተነጋገሩ በኋላ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለማዘጋጀት ተስማሙ። «አዳምንና ሔዋንን ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ብሎ ያበሰረ አምላክ ለእኛስ ይልክልን የለምን?» ብለው መኝታ ለይተው ለ፯ ቀን ያህል በጸሎትና በጾም ሰነበቱ። ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ቅዱስ ገብርኤል ለጻድቁ ኢያቄም በተራራ ላይ ሳለ ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፦ «ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች፤ ዓለም ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን፣ የብዙዎችም ዐይነ ልቡናቸው በእርሷ የሚበራላቸውን፣ በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች» አለው። ለሐናም ተገልጦ «ከሰው የበለጠች፣ ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ» ብሎ አበሰራቸው። በዚሁ ዕለት ነሐሴ ፯ ቀን በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በብሥራተ መልአክ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሐና ማኅፀን ተፀነሰች! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያንም ይህን ቀን «ፅንሰታ ለማርያም»በማለት በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዓለም ድኅነት የተዘጋጀች ታላቅ የካሳ መሠረት ናት። እግዚአብሔር አምላክ ለዳዊት በማህላ የተናገረው የታመነ ቃል ፍጻሜ አገኘ፦ «እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ፥ አይጸጸትምም፥ ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ» (መዝሙር 132:11)። ከዳዊት ወገን የተገኘችው እመቤታችን፣ የዚሁ የመለኮታዊ ቃል ኪዳን ፍሬና የክርስቶስ የማኅፀን ማደሪያ ለመሆን የተመረጠች ናት።

አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ የእመቤታችንን ንጽሕናና የፅንሰቷን ቅድስና ሲገልጥ እንዲህ ብሏል፦ «ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ»(ድንግል ሆይ! በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ):: እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነች፣ የመላእክት አክሊል፣ የነቢያት ትንቢት፣ የሐዋርያት ሞገስ፣ የዓለም ሁሉ ቅድስና ናት። እርሷ በቅድስናዋና በትሕትናዋ ምክንያት የእግዚአብሔርን ዓይን ሳበች፤ የራሷም ትሕትና ሲገልጥ ራሷ እመቤታችን፦ «የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና፤ እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል» (ሉቃስ 1:48) በማለት ተናግራለች።

ጻድቃኑ ኢያቄምና ሐና ከሰው የደረሰባቸውን መነቀፍና ውርደት በትዕግሥት አልፈው በጸሎት፣ በጾም፣ በዕንባና በሕግ በሆነ ቅዱስ ጋብቻ ለእግዚአብሔር በመታመናቸው እግዚአብሔር የታመነ አምላክ መሆኑንና የዓመታት ዕንባን አይቶ በራሱ ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጥ እናስተውላለን፡፡ ስለሆነም ዛሬ በሕይወታችን በመካንነት፣ በሕመምና በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ የምንገኝ ወገኖች ተስፋ ሳንቆርጥ በተሰበረና ንጹሕ ልብ ወደ ፈጣሪያችን ልንመላለስ ይገባል። በተጨማሪም ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን በረከትና ስጦታ ልጅን፣ ሀብትንና ዕውቀትን መልሰን ለእግዚአብሔር ቤትና ለምስኪኖች በመስጠት፣ ልጆቻችንንም በእግዚአብሔር ፍርሃት በማሳደግ የተሳልነውን የስዕለት ክፍያ ልንፈጽም ይገባናል፡፡ እመቤታችን በአዳም ባሕርይ ውስጥ ያበራች ነጭ ዕንቁ እንደሆነች ሁሉ፣ እኛም የክርስቶስ አካላትና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች በመሆናችን ማንነታችንን ከኃጢአት ጠብቀን ልባችንን፣ ጆሯችንንና ዓይናችንን ለቅድስናና ለእግዚአብሔር ቃል የተከፈተ በማድረግ በቅድስና ልንመላለስ ይገባል።

እግዚአብሔር አምላክ የቅዱስ ኢያቄምንና የቅድስት ሐናን ጸሎት የሰማ፣ የልቡናቸውን መሻት የፈጸመ አምላክ፤ ዛሬም የእያንዳንዳችንን የልባችንን በጎ መሻት ይፈጽምልን። የሕይወታችንን መካንነትና የልባችንን ድርቀት አስወግዶ መንፈሳዊ ፍሬ እንድናፈራ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷና አማላጅነቷ አይለየን።

ቀሲስ ጤናው እንዳላማው
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የፕሮጀክት ማናጀር

Scroll to Top