ኤክቱስ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም
ለብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከቢታንያ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የእውቅናና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበረከተላቸው።
ሽልማቱ የተበረከተላቸው በዛሬው ዕለት ኮሌጁ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት ታላቅ መርሃ ግብር ላይ ነው።
ቢታንያ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ትምህርትና ሙያ ከማስተማር ባሻገር፣ ለማኅበረሰቡ ሰላም፣ አብሮነት፣ መተሳሰብና ሁለንተናዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ግለሰቦችንና ተቋማትን ማክበርና ማመስገን እንደሚገባው ባመነው መሠረት ይህንን እውቅና መስጠቱ ተገልጿል።
ብፁዕነታቸው ወደ አካባቢው በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ከተመደቡበት ጊዜ አንስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሃይማኖታዊ አገልግሎት ባሻገር ለማኅበረሰቡ ሰላም፣ አብሮነትና ልማት በርካታ አወንታዊ ተግባራትን ማከናወናቸውን የመርሃግብሩ መሪ በንግግራቸው አሳትውቀዋል።
በተለይም በበጋና በክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት በመሳተፍ፣ አቅመ ደካሞችንና አስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያሉ ወገኖችን በማስተባበር፣ የቤት ግንባታን ጨምሮ ከኪስ ገንዘባቸውና ከጉልበታቸው በመለገስ ላከናወኗቸው የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከፍተኛ አድናቆት ተሰጥቷቸዋል።
በተጨማሪም በሃይማኖት ተቋማት የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በማበራታትና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ማኅበራዊ ሀላፊነት ጋር በማጣመር ሃይማኖት ለሰላምና ለልማት ያለውን አወንታዊ ሚና በተግባር ማሳየታቸውና ለትውልዱ መልካም አርአያ መሆናቸው ተመልክቷል።
በመሆኑም ቢታንያ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ብፁዕነታቸው ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለማኅበረሰብ ድጋፍ ላደረጉት ላቅ ያለ አስተዋጽዖ ያለውን አድናቆትና ምስጋና ለመግለጽ የዛሬውን የምስክር ወረቀትና የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።
