በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ሀገረ ስብከቱ በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ለሁለት ወር ያሰለጠናቸውን ካህናት አስመረቀ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በአንዲዳ መድኃኔዓለም የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ለሁለት ወራት ሲያሠለጥናቸውን የቆየውን ካህናት አስመርቋል። በመርሃግብሩ በተመራቂ ካህናቱ አቅራቢነት ቅኔዎች፣ ያሬዳዊ ዝማሬዎችና የተለያዩ ሥነ ጽሑፎች ቀርበዋል። በተጨማሪም የመርሃ ግብሩን ተደራሽነትና አካታችነት ባረጋገጠ መልኩ በጌዴኡፋ፣ በኮሪቴ እና በዳሸቴ (Dhashete) ቋንቋዎች መንፈሳዊ መልእክቶች ተ አስተላልፈዋል።

​በሥነ ሥርዓቱ ላይ የማኅበረ አቡቀለምሲስ ተወካይ ላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፣ ተመራቂዎች የተቀበሉትን መንፈሳዊ አገልግሎት በታማኝነትና በትጋት እንዲወጡ አሳስበዋል። ማኅበሩ ተመራቂዎችን ለመደገፍና በቀጣይ የአገልግሎት ዘመናቸው አቅም የሚሆኗቸውን የሃይማኖት መጻሕፍት ስጦታ ያበረከተ ሲሆን ከተበረከቱት መጻሕፍት መካከል መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድምታ ወንጌል እና መድሎተ ጽድቅ ይገኙበታል።

​በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂ ካህናት ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሽልማቶች የተሰጡ ሲሆን ለሁሉም ተመራቂዎች ደግሞ ትምህርታቸውን ማረጋገጣቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) እና ትራንስክሪብት ተበርክቶላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተመራቂዎቹን በትጋት ላሠለጠኑ መምህራን የማበረታቻ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ለመርሃ ግብሩ መሳካትና ለቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት በጎ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ የምስክር ወረቀትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

​በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ መልእክትና መመሪያ አስተላልፈዋል። መልአከ ሕይወት ብርሃኑ በተላለፉት መልእክት ተመራቂዎች ያገኟቸውን እውቀቶች ወደ ተግባር በመለወጥ ምዕመናንን በቅንነትና በእውነት እንዲያገለግሉ አሳስበው መርሃ ግብሩን በጸሎት አጠናቀውታል።

Scroll to Top