በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Uncategorized

በጉባኤው ማጠቃለያ ቀን 28 ምዕመናን የንሥሐ አባት እንዲይዙ ተደረገ!

ኤክቱስ ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መመሪያ ሰጪነት በማታው (በመጨረሻው) የጉባኤ መርሃግብር ሃያ ስምንት ምዕመናን የንሥሐ አባት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህም እያንዳንዱን ምዕመን ሕይወታቸውን በቅዱሳት ምሥጢራት ተሳታፊ ሆነው እንዲመሩ ለማስቻል የተከናወነ የመንፈሳዊ አገልግሎት አካል ነው። በዕለቱ በተላለፈው ትምህርት ምዕመናን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጸኑና እርስ በእርስ በፍቅር እንዲሁም በሰላም እንዲኖሩ ጥሪ ቀርቧል። የንሥሐ አባት ለመያዝ የተመዘገቡ ምዕመናንም በአስቸኳይ አባት ተመድቦላቸው በመንፈሳዊ አባቶቻቸው እየተመሩ ጠንካራ መንፈሳዊ መሠረት እንዲኖራቸው ሊደረግ እንደሚገባ መመሪያ ተሰጥቷል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ቀን 28 ምዕመናን የንሥሐ አባት እንዲይዙ ተደረገ! Read More »

የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት የእረፍት በዓል ብፁዕነታቸው በተገኙበት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ!

ኤክቱስ ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም የምድራዊው ሱራፊ፣ ሐዲስ ሐዋርያ፣ መምህረ ትሩፋት የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ተከበረ። በዕለቱ ታቦቱ ከመንበሩ ከወጣ በኋላ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን የሚያሳይ ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል። የዕለቱን ትምህርት መጋቤ ጥበባት መምህር ኤርምያስ እንዳሻው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ በሻሌ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የቁጥጥር ክፍል ኃላፊ የጻድቁን ዜና ሕይወታቸውን በመተረክ፣ ስለክብራቸው፣ ስለአማላጅነታቸው በሰፊው አስተምረዋል። በመቀጠል ቀሲስ ሙሉዓለም ዐባይ የሐዋሳ ደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ከሊቀ ትጉሃን ሀብታሙ አበበ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ጋር በመሆን በደብሩ ለሚሠሩ የልማት ሥራዎች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር አከናውነዋል። በመጨረሻም በወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ሰላም እኔምአየሁ ዓለሙ ጋባዥነት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በዚያ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው በንግግራቸው አሁን ያለውን የቅዱሳት ምሥጢራት ተሳትፎ ደካማነት በማንሳት ምዕመናን በቅዳሴ፣ በንሥሐ፣ በቅዱስ ቁርባን ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈው በጸሎት ፈጽመዋል።

የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት የእረፍት በዓል ብፁዕነታቸው በተገኙበት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ! Read More »

የሰሞኑን የአየር ንብረት መዛባትን አስመልክቶ በብፁዕ አቡነ ገሪማ መሪነት ጸሎተ ምሕላ ተካሄደ!

ኤክቱስ ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እየተከበረ በሚገኘው በጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት የእረፍት በዓል በታቦቱ ፊት በብፁዕነታቸው መሪነት የምሕላ ጸሎት ተካሂዷል። ይህ የጸሎተ ምሕላ ሥነ ሥርዓት በሀገሪቱ ከተከሰተው የአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳኑ ጸሎት ምሕረቱን እንዲልክና በወቅቱ ዝናቡን እንዲያዝንም ተማጽነዋል።

የሰሞኑን የአየር ንብረት መዛባትን አስመልክቶ በብፁዕ አቡነ ገሪማ መሪነት ጸሎተ ምሕላ ተካሄደ! Read More »

ስለ ጻድቃን ብዬ እምራለሁዘፍ 18:26

ይሔን ቃል የጻፈልን ያለፈውን ታሪክ በትንቢት ወደ ኋላ ተጉዞ የጻፈ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው። የዚህ ቃል የመነገሩ ታሪካዊ ክስተት ለጊዜው በቤቱ ጣራ (እልፍኝ) ፍጻሜው ግን በልቡናው እልፍኝ ሥላሴን ተቀብሎ በሥላሴ ዘንድ ሞገስ ያገኘው  ነቢዩም ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ተመልከቱ ብሎ የጠቀሰለት ኢሳ 5፥11 ደጉ አባት አብርሃም  ነው ። ታሪኩም እንዲህ ነው ….ሰዶም የምትባል በተፈጥሮ ሀብት ምቹና ባለ ብዙ ጸጋ፣ ለምለም ምድር ነበረች። እንደ ጸጋዋ አምላኳን ያላወቀች፣ አውቃም ማመስገን የተሳናት ምድር ናት ጸጋ ሲሰጥ አይታይም ሲነጠቅም አይታይም ይላል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ። ብዙ ጸጋ ያላቸው አካላት ያላቸው ጸጋ አልታያቸው ብሎ ብዙና ብዙ ሲሉ እናያለንና እንደ ጸጋችን መኖር መልካም ነው።ሎጥም የውስጧን በኃጢአት መለምለም ሳያይ ውጫዊ ገጽታዋን አይቶ ለኑሮ መርጧት ነበር። ዘፍ 13፥10 በደሏን ከሰማይ ሁኖ ያየ አምላክ ሊያጠፋት ሲነሳ ደጉና የጻድቃን አባት አብርሃም ተከተለውጌታም የልቡን ከባሪያችን አንሰውርም በማለት ከማንም ጋር ሳይመክር የፈጠረውን ዓለም  ለማዳን ግን ከቅዱሳን ጋር ይመክራል። ትን፡አሞ 3፥7 ስለዚህ የሰዶምን በደል  እ/ር ነገረው ለአብርሃም ቀደም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጦታል በአንተ የምድር ሰዎች ይባረካሉ ብሎ በተገባለት ቃል ኪዳን መሰረት አብርሃም ስለ ሰዶም ሊያማልድ በሥላሴ ፈት ቆመ ይላል። ዘፍ 18፥22 በዚህን ጊዜ ነው ስለ ጻድቃን ብለህ አታጥፋ ሲለው ስለ ጻድቃን ብዬ እምራለሁ ያለ  አምላካችን። ይሄ የምልጃ ሰንሰለት በአብርሃም ብቻ ሚቀር አይደለም በኋላ ዘመን ሙሴ  ስለ እስራኤል ለማማለድ ሲቆም የተጠቀመው ከሞቱ ብዙ ዘመን የሆናቸውን አባቶቹን አብርሃምን ፣ይስሐቅን፣ያዕቆብን ጠርቶ ስለ ነዚህ ብለህ ማር አለው የማይሞት ቃል ኪዳን ስላላቸው በማይሞተው ቃል ኪዳናቸው ምሯቸዋል። ዘጸ  32፥13  1ኛነገ 18፥35 ኤልሳዕ ባህር ለመክፈል የተጠቀመው የአባቱን የኤልያስን ስም ነው ። 2ነገ  2፥14 በሐዲስ ኪዳንም እንዲሁ እንደ አባቶቻችን የቅዱሳንን ስም ጠርተን ምንሻገራቸው በርካታ ፈተናዎች አሉ ። ጻድቁ አባታችን ተክለሃይማኖት ከአባታቸው ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከእግዚዕ ኀረያ በብዙ ልመና፣ ጸሎት የተገኙ የጸሎት ፍሬ ናቸው ። አባትና እናታቸውን በረቂቅ ጥበቡ እግዚአብሔር ከንጉሥ መተሎሚ ጦር ሰውሮ ጻድቁ አባታችን እንዲወለዱ የቸርነቱን ስራ ሰርቷል። በልደታቸው ቀን ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት ሳይቀር ደስ ተሰኝተዋል “በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” እንዲል  ሉቃ 1፥14 በቅዱሳን ልደት ደስ ብሎን ብንዘምር ከወንጌል ያገኘነውን ነው።ስለዚህ ጻድቃን የሚወለዱ ሊኖሩ ሳይሆን በዚህ ምድር ስራ ሰርተው በሞት በኩል ለዘላለማዊ ልደት ተወልደው ሊኖሩ ነው ሚወለዱ ሊሞቱ  ነው ሚሞቱ ሊኖሩ ነው። በኖሩባት ምድር በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል፣ ወንጌልን በስፋት አስፋፍተዋል፣ በርካታ ነፍሳትን ወደ በረታቸው መልሰዋል፣ ህሙማንን፣ጋኔንን ያደረባቸውን ፣ሽባዎችን፣ዕውሮችን፣አንካሶችን ፈውሰዋል። የሟርትን፣የጥንቆላን፣የመተትን  ጎጂነትና ባዕድ አምልኮ መሆኑን በግልጽ አስተምረዋል በተጨማሪም በርካታ መከራዎችን ተቀብለዋል። ስለዚህ የቅዱሳንን አማላጅነት፣ገድል፣ቃልኪዳን በመቀበል በዚህ በኩል ሚገኘውን በረከት ማግኘት ከኛ ከአማኞች ይጠበቃል ።ለሚገባው ሰላማችሁ ይደረግለት ስለሚል ማቴ  10፥13 ተቀባይ ልቡና ከሌለ ስለማያድርበቅዱሳን በኩል በረከቱን ለመስጠት እግዚአብሔር የታመነ ነው። የላባን ቤት የባረከ በያዕቆብ በኩል መሆኑን መጽሐፍ ነገረንየፈርኦንን ቤት የባረከ በዮሴፍ መግባት መሆኑን ሙሴ በቅዱሳኑ በኩል ሚገኘውን በረከት ነገረን ዘፍ  30፥27   ዘፍ  39፥2 ወውዕቱ ፍሬክሙ ይነብር ለዝሉፉይሄ የምልጃ፣የቃልኪዳን ፍሬአችሁ ለዘለዓለሙ ይኖራል እንዲል ዮሐ 15፥16 ለጻድቁ አባታችን ለተክለ ሃይማኖት ለእናታችን ክርስቶስ ሰምራ ከዚህ ዓለም ወደዚያኛው ቢነጠቁም እንኳ ቅሉ የማይታጠፍ ቃል ኪዳን ስላላቸው። በመጨረሻ  ከገድል ወደ ገድል እያሉ ሳለ በጾም፣በጸሎት፣በምንኩስና ፣በአጽንኦ በዓት ተወስነው ሲኖሩ ወደሚናፍቁት ዓለም ለመውሰድ አምላካቸው የኔን መስቀል ተሸክመህ ስለ ኖርክ የኔን ክብር ትወርስ ዘንድ ይገባሀል ብሎ በመከራው ከመሰልነው በክብሩ እንመስለዋለን እንዲል  ሮሜ  6፥4 ብዙ ቅዱሳን መላዕክትንና ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትሎ መጦ በስምህ መታሰቢያ ያደረገውን፣ ለተራበ ያበላውን ለተጠማ ያጠጣውን፣ በስምህ ቤተክርስቲያን የሰራውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ የሰማውን እና ያሰማውን እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለሁ ብሎ ነፍሳቸውን ከስጋው ለይቶ አሳረጋት። በመሆኑም ስለ ጻድቃን ስም፣ ቃልኪዳን፣ ገድል ለመማር ስለነሱ ዘመን በማይሽረው ቃሉ ዛሬም እምራለሁ ካለ ነሐሴ 24 ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት እናታችን ክርስቶስ ሰምራ በተጨማሪም የበርካታ ቅዱሳን የዕረፍታቸውን ክብረ በዓል እናከብራለን ነገር ግን  በስጋ ከኛ ተለዩ ማለት በአማላጅነት፣በቃልኪዳናቸው ፣በተአምራታቸው፣ወዘተ ማይለዩን መሆናቸውን ማዎቅ ይኖርብናል ። ሀገራችንን በቅዱሳኑ ጸሎት ይጠብቅ።ከቅዱሳኑ ረድኤት በረከት  ይክፈለን  አሜን ። ከመ/ር ህላዌ  ዘለዓለምየብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መምህር

ስለ ጻድቃን ብዬ እምራለሁዘፍ 18:26 Read More »

ብፁዕነታቸው እርስ በእርስ ተጣልተው የነበሩ ምዕመናንን አስታረቁ

ኤክቱስ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ እርስ በእርስ ተጣልተው የነበሩ ምዕመናን ወደ ዐውደ ምሕረት በመውጣት አስታረቁ። ይህ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት የተከናወነው የጻድቁ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን የእረፍት በዓል ምክንያት በማድረግ በኮቾሬ፣ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ቀናት በተዘጋጀው ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ነው። በዕለቱ ምዕመናኑ በሙሉ ፈቃዳቸው ወደ ዐውደ ምሕረት በመውጣት የቆየ ቅሬታቸውን እና ጥላቸውን በመተው ይቅር ተባብለዋል። ይህም ክስተት የዕለቱ ትምህርተ ወንጌል ዋና ፍሬ ሆኖ መሆኑንም ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው እርስ በእርስ ተጣልተው የነበሩ ምዕመናንን አስታረቁ Read More »

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ወደ ገደብ ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው!

ኤክቱስ ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የጻድቁ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን የእረፍት በዓል በማስመልከት በኮቾሬ፣ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ቀን በተዘጋጀው መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልክቶ ወደ ገደብ ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ወደ ገደብ ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው! Read More »

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የሐዋርያት የአንድነት የኑሮ ማኅበር ለ4 ወራት ያሰለጠናቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት አስመረቀ!

ኤክቱስ ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም በዛሬው ዕለት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የከምባታ ሀላባ ጠምባሮና የዳውሮ ኮንታ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የሐዋርያት የአንድነት የኑሮ ማኅበር ለ4 ተከታታይ ወራት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት በቡራዩ ከተማ አስመርቋል። ከጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ተልከው ላለፉት 4 ወራት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ብዛታቸው 30 ሲሆን በቆይታቸውም በርካታ ትምህርቶችን እና ሥልጠናዎችን መውሰዳቸው ተገልጿል። በመጨረሻም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት አባታዊ ቡራኬና መመሪያ ሰጥተዋል። 📷 ዜና ጎርጎርዮስ

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የሐዋርያት የአንድነት የኑሮ ማኅበር ለ4 ወራት ያሰለጠናቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት አስመረቀ! Read More »

አሥራ አራት አዳዲስ አማንያን ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አገኙ!

ኤክቱስ ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት በገርቦታ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አሥራ አራት አዳዲስ አማንያን በዛሬው ዕለት ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል። ተጠማቂያኑ በደብሩ የስብከተ ወንጌል ክፍል አማካኝነት ከዚህ ቀደም በቱሊሴ አከባቢ በተቋቋመው የስብከተ ወንጌል ኬላ የቅድመ ጥምቀት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።

አሥራ አራት አዳዲስ አማንያን ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አገኙ! Read More »

“ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ – አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት”( መዝ ፻፴፩ ፣፰)

​ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከብዙ ዘመናት በፊት የተናገረው ይህ ምስጢራዊ ኃይለ ቃል፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ድንቅ ትንሣኤ እና ዕርገት የሚያበስር ታላቅ የትንቢት መነሻ ነው። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ታቦት የክብሩ ማደሪያ  ሕጉ የተገኘባት እንደነበረች  ሁሉ  በአዲስ ኪዳን ደግሞ እውነተኛውን ህግ ኢየሱስ ክርስቶስን በማህፀኗ የተሸከመችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማናዊት ታቦት ናት። ​የእመቤታችን የሕይወት ታሪክ ከኢያቄም እና ከሐና ከመወለዷ ጀምሮ፣ በሦስት ዓመቷ ወደ ቤተ መቅደስ ገብታ በንጽህናና በቅድስና ማደጓ፣ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት በ15ዓመቷ የዓለምን መድኀኒት የመውለዷ ምስጢር የሰው ልጅ የመዳን ታሪክ መሠረት ነው። እሷ ለዓለም ሁሉ መድኃኒት የሚሆን አምላክን በድንግልና  በመውለድ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቀባት እውነተኛዋ  የመቅደሱ ታቦት ናት። ጌታንም ከወለደች በኋላ የቆየችው 49 አመት መሆኑ አንድ ኢዮቤልዩ ነው ይህም ማለት ሰባት ሱባኤ ማለት ሲሆን በዚህም እመቤታችን በነብያት ትንቢት በአባው ሱባኤ የተገኘች የአባቶቻችን የጸሎት ውጤት መሆኗን እንረዳለን ጌታን ከመወለዷ አስቀድሞ 15 አመት ጌታን ከወለደች በኋላ ወላዲተ አምላክ ተብላ እየተጠራች 49 አመት በምድር ቆየች  ዘመናቱ ጥቂት ቢሆኑም በመከራ የተፈጸሙ አመታት ናቸው ከዚህ የመከራ ዓለም ሊያሳርፋት ልጇ በእግርማ መለኮት በቅዳሴ መላእክት እርሷ ወደ ነበረችበት ወደ ዮሐንስ ቤት ወረደ  ጌታን የመጽነሷን ዜና በቤተ ዮሴፍ ሰማች የልጇን ሞት በቤተ ዮሐንስ ዛሬ ደግሞ የእርሷን ሞት በዚህው ስፍራ ተነገራት ስለ ክብሯ ሊቀበላት የወረደው ጌታ ሐዋርያትን ከየሀገረ ስብከታቸ  በፍጣን ደመና ሰበሰባቸው እመቤታችንን እንዲሰናበቷት አዘዛቸው ከዚህ በኋላ በስጋ አይገናኙምና ሁሉም ደቀመዛሙርት ዝቅ እያሉ ተሰናበቷት በረከቷን ተቀበሏት ወደ ፈጣሪ  እንድታሳስብላቸው አደራ አሏት። ከዚህ በኋላ አባቷ ዳዊት ንግስቲቱ በቀኝ ትቀመጣለች የሚለውን መዝሙር እየዘመረላት ሰሎሞን ንዒ ርግብየ  እያላት ሌሎችም ነብያት እያወደሷት የሰማይ መላእክት ማንም ሊሰማው  በማይችለው የምስጋና ቃል እያመሰገኗት በልጇ ቃል ቅድስት ነፍሷ ከስጋዋ ተለይታ በተወደደ ልጇ እቅፍ ላይ ተቀመጠች ቀኑ ልዩ ነበር በአጸደ ስጋ የነበሩ ሐዋርያት በአጸደ ነፍስ ከነበሩ ነብያት ጋራ መሬታውያን ከሰማያውያን ጋራ አንድ ሆነው የዘመሩበት ነውና ነፍሷ ወደ ፈጣሪ ከተመለሰች በኋላ ሐዋርያት ስጋዋን ገንዘው ለመቅበር ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሄዱ  ምንም መድኀኒትን ያሰገኘች ብትሆንም ተፈጥሮዋ እንደ ሰው ናት እና በሞት በኩል ይህን  ዓለም በሥጋ ተሰናበተችው።  ጌቴሴማኒ ከመድረሳቸው በፊት ግን አይሁድ ከጎዳና ላይ በጠላትነት ተነስተውባቸዋል በእሳት አቃጥለን በድንጋይ ቀጥቅጠን እናጠፋለን ወደ መቃብር እንዳትደርስ እናደርጋታለን አሉ። በህይወት ሳለች ያነሱ እንደነበር ከሞተችም በኋላ ተቃውሟቸው አላቆምም ቅዱሳን እንደማይሞቱ በዚህ ይታወቃል ቢሞቱማ ኖሮ የሞተውን ሰው ምን ይሰራል ብለው ማን ይቃወመዋል በክርስቶስ የሞቱት ግን ያንቀላፉት ለእረፍት እንጂ ለሞት አይደለምና ከሞቱም በኋላ ስራ ይሰራሉ ጠላቶቻቸውን ይጎዳሉ ወዳጆቻቸውን ይጠቅማሉ ከዚህም የተነሳ አጋንንት ሰዎችን እያስነሱ ሲጣሏቸው ይኖራሉ የልጇን ትንሳኤ እንደሰማን የእሷንም ትንሣኤ ልንሰማ አይደለም ብለው በመፍራት እናጠፋለን ብለው የቀረቡት አይሁድን በመቅጣት የእግዚአብሔር መልአክ ዮሐንስን ጨምሮ እሳተ መለኮትን በመሸከም የከበረ ስጋዋን በገነት ካሉት እጽዋት መካከል አስቀመጠው ዮሐንስ በህይወት ዘመኗ እንዳገለገላት ከሞተች በኋላ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ በማጠን አገለገላት” እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረፈችው ጥር 21 ቀን ነው። በዕረፍቷ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ነፍሷን ከሥጋዋ በክብር ለይቶ ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት አሳረፋት። ሐዋርያት ሥጋዋን ሊቀብሩ ሲወስዱ አይሁድ በቅናት ሊያቃጥሉ ስለሞከሩ፣ እግዚአብሔር ሥጋዋን ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አሰቀመጠው። ​ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ ተለይቷቸው በመቅረቱ እጅግ አዝነው፣ ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ በ14ኛው ቀን የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ለሐዋርያት ሰጣቸው፤ ቀኑ ነሐሴ 14 ቀን 49 ዓ ም እለተ እሁድ ነበር እነርሱም ደስ ብሏቸው ተቀብለው እለቱን ቀብረዋታል የተነሳችም እነሱ ቀብረዋት ከሄዱ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን ነው 49 ዓመተ ምህረት በዚሁ እለት በእለተ እሁድ ነው አልዋችም አላደረችም ከመትንሣኤ ወልዳ የሚለው ንባብ ስለ ሁለት ነገር ነው አንደኛ በእለተ እሁድ መነሳቷን ሲያይ ነው  ልጇ የተነሳ በእለተ እሁድ ነው እና  ሁለተኛ በሐዲስ ስጋ መነሳቷን ያጠይቃል ከፍጡራን መካከል ዳግም ሞት የሌለበት አማናዊ ትንሣኤ የተነሳ ከእመቤታችን በቀር ሌላ ፍጡር የለምና ትንሣኤዋ ከእነ አልዓዛር ትንሣኤ ልዩ መሆኑን ለማስረዳት ከመትንሣኤ ወልዳ ተብሏል እንጂ በሶስተኛው ቀን ተነሳች ለማለት አይደለም  ከእነ አልዓዛር ትንሣኤ ልዩ ነው ማለት የእነ አልዓዛር ትንሣኤ በብሉይ ስጋ ነው የእሷ በሐዲስ ስጋ ነው የእነ አልአዓዛር ትንሣኤ ዳግም ሞት አለበት እርሷ ግን ዳግም ሞት የለበትም እና ከእነ አልዓዛር ትንሣኤ የእመቤታችን ትንሣኤ ልዩ ነው። እለተ እሑድ ለኖርነው ዓለም መጀመሪያ እንደሆነች ወደፊት ለሚመጣውም ዓለም ለመንግስተ ሰማይ ቀዳሚት ናትና ከትንሳኤ ዘጉባኤ በኋላ ትኖራለች ሰው ዳግም ሞት እንደሌለበት ይታወቅ ዘንድ በዚህች እለት አዲስ ህይወት ይጀምራል እመቤታችንም በአዲስ ተፈጥሮ ለተፈጠረው ትውልድ የመጀመሪያ ሆና በእግዚአብሔር ፊት በመገኘቷ ተስፋ ለምናደርጋት ዓለማችን መንግስተ ሰማያትንም የመጀመሪያ አድርጎ ነፍስና ስጋ ተዋህደው በአንድነት በሚኖሩበት መንግስተ ሰማያት እንድትኖር አደረጋት። ምናልባት ዛሬ ለምንድነው ፍልሰተ ስጋዋን ነሐሴ በገባ በ፲፮ኛው ቀን የምናከብረው የሚል ጥያቄ ከተነሳ ነገሩ ሌላ ነው ምስጢሩ ይህ ነው ቀደም ሲል በጠቀስው መሠረት እመቤታችን በተነሳችበት እለት ከደቀ መዛሙርት መካከል ከቶማስ በስተቀር ያያት ማንም አልነበረም ቶማስ ብቻ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም በደመና ተጭኖ ሲመለስ እመቤታችን መላእክት በብርሃን ሰረገላ ሲያሳርጓት አገኛት የመግነዟን ሰበን ለምልክት ሰጥታው ነበርና በዓመቱ ማለትም በ፶ ዓም ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ሁሉም ሐዋርያት ከቶማስ በጆሯቸው የሰሙትን ዜና ትንሣኤዋን በዓይናቸው ለማየት እንደገና ሱባኤ ጀምረዋል በ፲፮ኛውቀን ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በክብር ተገልጦ ቀድሶ  እንዳቆረባቸውና እንደባረካቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ ስለዚህም አባቶቻችን ሐዋርያት ትንሣኤዋን ያዩበትን ቀን ፍልሰተ ስጋሃ ብለን እናከብራለን እናም የነሐሴ ፲፮ኛው ቀን ትንሣኤዋ የተገለጠበት ቀን እንጂ የተነሳችበት ቀን አይደለም” ነብዩ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረው ጌታ ከሙታን መካከል በአብ ቀኝ ለመቀመጥ ማለትም በክብር በአብ ዕሪና ለመኖር እንደተነሳ እናቱ ድንግል ማርያም ዳግመኛ ሞት በማያስፈራው ትንሣኤ በልጇ ቀኝ ለመቀመጥ ተነሳች ተንሥእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ አቤቱ ምዕመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግስተ ሰማያት ተነስ አንተና የታቦትህ መቅደስ መዝ ፻፴፩ ፣፰ በዚህ አረፍተ ነገር ውስጥ ነብዩ የተናገረው ስለ ጌታና ስለ እመቤታችን ትንሳኤ ነበር መቅደስ የተባለች ኢየሩሳሌም ስትሆን ታቦት የተባለች ደግሞ ማኅደረ ግዚአብሔር ድንግል ማርያም ናት በዚህ መሠረት የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውና እመቤታችን ተነስታለች።  ከዚያች እለት ጀምሮ በእግዚአብሔር ፈቃድ በተሰጣት ስልጣን በቀኙ ተቀምጣ ትኖራለች ያ ማለት በመንግስተ ሰማያት ማለት ነው ። አምላከ ቅዱሳን እኛንም እርሷ ከገባችበት ውሳጤ መንጦላዕት ያግባን  አሜን!!!!

“ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ – አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት”( መዝ ፻፴፩ ፣፰) Read More »

የበዓለ ደብረ ታቦር ዋዜማ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተከበረ!

ኤክቱስ ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ከሐዋርያት ሁለቱን ከነቢያት መርጦ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት የበዓለ ደብረ ታቦር ዋዜማ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በታላቅ መንፈሳዊ ድምቀት ተከብሯል። በዕለቱ የደብሩ መሠረተ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት ለዕለቱ የሚሆን ዝማሬ፣ ኪነ ጥበብ አቅርበዋል። የዕለቱን ትምህርት ላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ “በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” የማቴዎስ ወንጌል ፲፯፥፬ ላይ የሚገኘውን ኃይለ ቃል በማንሳት እና የዕለቱን ታሪክ በመተረክ በሰፊው አስተምረዋል። በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ጸሎት አድርገው እንዲሁም የተዘጋጀውን ችቦ ባርከው እንደ አባቶቻችን ሥርዓት የማብራት መርሃግብር ተከናውኗል።

የበዓለ ደብረ ታቦር ዋዜማ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተከበረ! Read More »

Scroll to Top