ይሔን ቃል የጻፈልን ያለፈውን ታሪክ በትንቢት ወደ ኋላ ተጉዞ የጻፈ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው። የዚህ ቃል የመነገሩ ታሪካዊ ክስተት ለጊዜው በቤቱ ጣራ (እልፍኝ) ፍጻሜው ግን በልቡናው እልፍኝ ሥላሴን ተቀብሎ በሥላሴ ዘንድ ሞገስ ያገኘው ነቢዩም ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ተመልከቱ ብሎ የጠቀሰለት ኢሳ 5፥11 ደጉ አባት አብርሃም ነው ።
ታሪኩም እንዲህ ነው ….
ሰዶም የምትባል በተፈጥሮ ሀብት ምቹና ባለ ብዙ ጸጋ፣ ለምለም ምድር ነበረች። እንደ ጸጋዋ አምላኳን ያላወቀች፣ አውቃም ማመስገን የተሳናት ምድር ናት ጸጋ ሲሰጥ አይታይም ሲነጠቅም አይታይም ይላል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ።
ብዙ ጸጋ ያላቸው አካላት ያላቸው ጸጋ አልታያቸው ብሎ ብዙና ብዙ ሲሉ እናያለንና እንደ ጸጋችን መኖር መልካም ነው።ሎጥም የውስጧን በኃጢአት መለምለም ሳያይ ውጫዊ ገጽታዋን አይቶ ለኑሮ መርጧት ነበር። ዘፍ 13፥10
በደሏን ከሰማይ ሁኖ ያየ አምላክ ሊያጠፋት ሲነሳ ደጉና የጻድቃን አባት አብርሃም ተከተለው
ጌታም የልቡን ከባሪያችን አንሰውርም በማለት ከማንም ጋር ሳይመክር የፈጠረውን ዓለም ለማዳን ግን ከቅዱሳን ጋር ይመክራል። ትን፡አሞ 3፥7 ስለዚህ የሰዶምን በደል እ/ር ነገረው ለአብርሃም ቀደም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጦታል በአንተ የምድር ሰዎች ይባረካሉ ብሎ በተገባለት ቃል ኪዳን መሰረት አብርሃም ስለ ሰዶም ሊያማልድ በሥላሴ ፈት ቆመ ይላል። ዘፍ 18፥22
በዚህን ጊዜ ነው ስለ ጻድቃን ብለህ አታጥፋ ሲለው ስለ ጻድቃን ብዬ እምራለሁ ያለ አምላካችን። ይሄ የምልጃ ሰንሰለት በአብርሃም ብቻ ሚቀር አይደለም በኋላ ዘመን ሙሴ ስለ እስራኤል ለማማለድ ሲቆም የተጠቀመው ከሞቱ ብዙ ዘመን የሆናቸውን አባቶቹን አብርሃምን ፣ይስሐቅን፣ያዕቆብን ጠርቶ ስለ ነዚህ ብለህ ማር አለው የማይሞት ቃል ኪዳን ስላላቸው በማይሞተው ቃል ኪዳናቸው ምሯቸዋል። ዘጸ 32፥13 1ኛነገ 18፥35 ኤልሳዕ ባህር ለመክፈል የተጠቀመው የአባቱን የኤልያስን ስም ነው ። 2ነገ 2፥14
በሐዲስ ኪዳንም እንዲሁ እንደ አባቶቻችን የቅዱሳንን ስም ጠርተን ምንሻገራቸው በርካታ ፈተናዎች አሉ ።
ጻድቁ አባታችን ተክለሃይማኖት ከአባታቸው ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከእግዚዕ ኀረያ በብዙ ልመና፣ ጸሎት የተገኙ የጸሎት ፍሬ ናቸው ።
አባትና እናታቸውን በረቂቅ ጥበቡ እግዚአብሔር ከንጉሥ መተሎሚ ጦር ሰውሮ ጻድቁ አባታችን እንዲወለዱ የቸርነቱን ስራ ሰርቷል።
በልደታቸው ቀን ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት ሳይቀር ደስ ተሰኝተዋል “በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል” እንዲል ሉቃ 1፥14 በቅዱሳን ልደት ደስ ብሎን ብንዘምር ከወንጌል ያገኘነውን ነው።
ስለዚህ ጻድቃን የሚወለዱ ሊኖሩ ሳይሆን በዚህ ምድር ስራ ሰርተው በሞት በኩል ለዘላለማዊ ልደት ተወልደው ሊኖሩ ነው ሚወለዱ ሊሞቱ ነው ሚሞቱ ሊኖሩ ነው።
በኖሩባት ምድር በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል፣ ወንጌልን በስፋት አስፋፍተዋል፣ በርካታ ነፍሳትን ወደ በረታቸው መልሰዋል፣ ህሙማንን፣ጋኔንን ያደረባቸውን ፣ሽባዎችን፣ዕውሮችን፣አንካሶችን ፈውሰዋል። የሟርትን፣የጥንቆላን፣የመተትን ጎጂነትና ባዕድ አምልኮ መሆኑን በግልጽ አስተምረዋል በተጨማሪም በርካታ መከራዎችን ተቀብለዋል።
ስለዚህ የቅዱሳንን አማላጅነት፣ገድል፣ቃልኪዳን በመቀበል በዚህ በኩል ሚገኘውን በረከት ማግኘት ከኛ ከአማኞች ይጠበቃል ።
ለሚገባው ሰላማችሁ ይደረግለት ስለሚል ማቴ 10፥13 ተቀባይ ልቡና ከሌለ ስለማያድር
በቅዱሳን በኩል በረከቱን ለመስጠት እግዚአብሔር የታመነ ነው። የላባን ቤት የባረከ በያዕቆብ በኩል መሆኑን መጽሐፍ ነገረን
የፈርኦንን ቤት የባረከ በዮሴፍ መግባት መሆኑን ሙሴ በቅዱሳኑ በኩል ሚገኘውን በረከት ነገረን ዘፍ 30፥27 ዘፍ 39፥2
ወውዕቱ ፍሬክሙ ይነብር ለዝሉፉ
ይሄ የምልጃ፣የቃልኪዳን ፍሬአችሁ ለዘለዓለሙ ይኖራል እንዲል ዮሐ 15፥16
ለጻድቁ አባታችን ለተክለ ሃይማኖት ለእናታችን ክርስቶስ ሰምራ ከዚህ ዓለም ወደዚያኛው ቢነጠቁም እንኳ ቅሉ የማይታጠፍ ቃል ኪዳን ስላላቸው።
በመጨረሻ ከገድል ወደ ገድል እያሉ ሳለ በጾም፣በጸሎት፣በምንኩስና ፣በአጽንኦ በዓት ተወስነው ሲኖሩ ወደሚናፍቁት ዓለም ለመውሰድ አምላካቸው የኔን መስቀል ተሸክመህ ስለ ኖርክ የኔን ክብር ትወርስ ዘንድ ይገባሀል ብሎ በመከራው ከመሰልነው በክብሩ እንመስለዋለን እንዲል ሮሜ 6፥4
ብዙ ቅዱሳን መላዕክትንና ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትሎ መጦ በስምህ መታሰቢያ ያደረገውን፣ ለተራበ ያበላውን ለተጠማ ያጠጣውን፣ በስምህ ቤተክርስቲያን የሰራውን፣ ገድልህን የጻፈውን ያጻፈውን፣ የሰማውን እና ያሰማውን እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለሁ ብሎ ነፍሳቸውን ከስጋው ለይቶ አሳረጋት።
በመሆኑም ስለ ጻድቃን ስም፣ ቃልኪዳን፣ ገድል ለመማር ስለነሱ ዘመን በማይሽረው ቃሉ ዛሬም እምራለሁ ካለ ነሐሴ 24 ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት እናታችን ክርስቶስ ሰምራ በተጨማሪም የበርካታ ቅዱሳን የዕረፍታቸውን ክብረ በዓል እናከብራለን ነገር ግን በስጋ ከኛ ተለዩ ማለት በአማላጅነት፣በቃልኪዳናቸው ፣በተአምራታቸው፣ወዘተ ማይለዩን መሆናቸውን ማዎቅ ይኖርብናል ።
ሀገራችንን በቅዱሳኑ ጸሎት ይጠብቅ።
ከቅዱሳኑ ረድኤት በረከት ይክፈለን አሜን ።
ከመ/ር ህላዌ ዘለዓለም
የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መምህር
