በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Uncategorized

ታቦታት ከባሕረ ጥምቀት ወደ አብያተ ክርስቲያናት ጉዞ አደረጉ!

አክቱስ ጥር 11/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በዲላ ከተማ የጥምቀት በዓል አራት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የመዝገበ ምሕረት ቅድስት ልደታ ለማርያም፣ የዳግማዊት ጌቴሴማኒ በዓታ ለማርያም፣ ጎላ ቅዱስ ራጉኤል እና የዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ከባሕረ ጥምቀት ወደ አብያተ ክርስቲያናት ጉዞ አድርገዋል።

ታቦታት ከባሕረ ጥምቀት ወደ አብያተ ክርስቲያናት ጉዞ አደረጉ! Read More »

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበት ዓመታዊ የጥምቀት በዓል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ከተማ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል!

ኤክቱስ ጥር 11/2018 ዓ.ም

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበት ዓመታዊ የጥምቀት በዓል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ከተማ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል! Read More »

ተጠምቀ ሰማያዊ በዕደ መሬታዊጥምቀት ከሰባቱ  ምሥጢራተ  ቤተክርስቲያን  አንዱ ነው፡፡

  የምሥጢረ ጥምቀት መሥራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትህትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው። ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን “መጥተህ አጥምቀኝ” ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን “መጥታችሁ አጥምቁን” ባሉ ነበር። ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው ጌታችን “ጌታ” ሲሆን በባሪያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ ሲል ነው።  ቅደስ ዮሐንስ ጌታችን በእርሱ እጅ ለመጠመቅ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ “እኔ ባሪያህ በአንተ በጌታዬ እጅ ልጠመቅ ያስፈልገኛል እንጂ አንተ በእኔ በባሪያህ እጅ ትጠመቅ ዘንድ እንዴት ወደ እኔ ትመጣለህ?” አለው። ጌታችንም መልሶ “አሁንስ ፍቀድልኝ፣ እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና /ትንቢተ ነቢያትን እንዲህ ልንፈጽም ያስፈልጋል/” አለው። በዚህን ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን አጠመቀው። በዚህም “መጥምቀ መለኮት” ተብሎ የቅዱስ ዮሐንስ ገናንነቱ ይነገራል፣ ጌታችንም በባሪያው እጅ በመጠመቁ ፍጹም ትህትናው ይነገርለታል።መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በኃጢአት የተዳደፉት ሁሉ ንስሐ ገብተው የተዘጋጀላቸውን መንግሥት ወራሾች ይሆኑ ዘንድ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ሲሰብክ ነበር። ይህ “መንግሥተ ሰማያት በልጅነት፤ ልጅነት ደግሞ በሃይማኖት ልትሰጥ ቀርባለችና ከኃጢአት ተለይታችሁ፣ ከበደል ርቃችሁ ቅረቡ” ማለት ነው። በነቢያት እንደተነገረውም “ የእግዚአብሔርን መንገድ አዘጋጁ፣ ጥርጊያውንም አቅኑ” እያለ ድምጹን አሰምቶ ሰብኳል። ምሥጢሩንም በመጣ ጊዜ ተራራውና ኮረበታው ተንዶ፣ ጎድጓዳው ተመልቶ፣ ሥሩ ተነቅሎ፣ ደንጊያው ተለቅሞ ለፈረስ ለሰረገላ እንዲመች ተደልድሎ እንደሚቆይ ሁሉ እናንተም የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችሁን ከኃጢአታችሁ ንጹሕ አድርጋችሁ ጠብቁ ማለት ነው።  ቅዱስ ዮሐንስ ከንስሐው ስብከት በተጨማሪም ዘመን የማይቆጠርለት ሲሆን ሥጋን በመለበሱ ዘመን ተቆጥሮለት ከእርሱ በኋላ ስድስት ወር ዘግይቶ ስለሚመጣው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነትም ሰብኳል፦ “እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል። እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው። አውድማውንም ስንዴውንም በጎተረው ይከታል፤ ፈጽሞ ያጠራል፤ ሰንዴወንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል። /ማቴ 3፡11፤ ዮሐ 1፡26/ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ለምን ተጠመቀ? የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው” ያለው /ቆላ 2፥14/፡፡ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል።ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ምስጢረ ሥላሴን ለመግለጥ ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልጽ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/ ትንቢቱን ለመፈጸምአቤቱ ውሆች አዩህ፣ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ተጠመቀ /መዝ 77፥16/፡፡              ወስብሐት ለእግዚአብሔር           ሊቀትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ      የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ

ተጠምቀ ሰማያዊ በዕደ መሬታዊጥምቀት ከሰባቱ  ምሥጢራተ  ቤተክርስቲያን  አንዱ ነው፡፡ Read More »

የበዓለ ጥምቀት የከተራ በዓል በዲላ ከተማ ብፁዕነታቸው በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከበረ!!

ኤክቱስ ጥር 10/2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ሁልጊዜ ከበዓለ ጥምቀት አንድ ቀን አስቀድሞ የሚከበረው እና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መውረዱ የሚያሰስብበት በዓል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በዲላ ከተማ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። በዕለቱ ታቦታቱ ከአድባራቱ ተነስተው በካህናትና በበርካታ ምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር ጉዞ አድርገዋል። በበዓሉ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በዶክተር መስፍን ደምሴ ጋባዥነት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበዓሉ ተገኝተው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ንግግር ያደረጉ ሲሆን በዕለቱ በዓሉ በልዩ ሁኔታ እንዲከበር አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላትና በዓሉን ከሚመሩት ሕዝብ ጋር በጋራ ለማክበር ለመጡ የመንግሥት አካላት ምሥጋና አቅርበው በጸሎት ፈጽመዋል። በዕለቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የጌዴኦ ዞን እና የዲላ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጠበብት መሪጌታ መሰረት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በርካታ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን ተገኝተዋል። “ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምዮሐንስ – ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ” ማቴ ፫፥፲፫

የበዓለ ጥምቀት የከተራ በዓል በዲላ ከተማ ብፁዕነታቸው በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከበረ!! Read More »

In the Name of the Father, and of the Son, and of the Holy Spirit, One God. Amen.

To our beloved children in the Holy Spirit, the faithful throughout our Diocese, across our nation, and in the Diaspora;May the peace of the Lord be with you as we celebrate the Glorious Feast of the Epiphany. We congratulate you on reaching this great public festival, commemorating the baptism of our Lord and Savior Jesus Christ in the River Jordan by the hand of John, for the sake of the salvation of the entire world. “ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ ደንገፁ ቀላያተ ማያት ወድምጸ ማያቲሆሙ”“The waters saw Thee, O Lord, the waters saw Thee and were afraid; the depths also were troubled. The waters poured out a sound.” (Psalm 77:16 / 76:16) This prophetic utterance of the Holy Prophet David describes the awe of creation as it recognized its Creator. When our Lord and Savior stood in the Jordan to be baptized, the inanimate elements manifested their fear and reverence for Him who became man through the Mystery of the Incarnation (ተዋሕዶ). Our Lord did not approach the Jordan because He was in need of purification; rather, as the “Source of Life” from whom “አፍላገ ማየ ሕይወት ዘይውኅዝ እምከርሡ”—”rivers of living water flow” (John 7:38) — He went down into the waters to sanctify them, transforming them into a womb of spiritual rebirth and divine adoption for us.On that day, the Jordan recoiled and the depths trembled, acknowledging the Divine Nature of the Christ standing in their midst. As the Holy Scripture bears witness: “ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ” — “The sea saw it and fled; Jordan was driven back” (Psalm 114:3). This marks the great day of triumph where the debt of human sin was annulled, and humanity was led from the shadows of darkness into the marvelous light of grace.Beloved children in the Holy Spirit;The baptism of our Lord in the Jordan was intended to pave the way for our salvation and to grant us new life by washing away our transgressions. Therefore, as we celebrate this sublime feast, we must reflect deeply on the price Christ paid for our redemption. Our celebration should be marked by Christian conduct that honors the dignity of the sonship we received through Holy Baptism.We must refrain from worldly excesses and secular behaviors that obscure the spiritual depth of this mystery or deviate from the ancient traditions of the Church (ጥንታዊ ሥርዓት). Instead, let us observe the feast through liturgy (ሥርዓተ አምልኮ), fervent prayer, and acts of charity.In conclusion, may our Lord and Savior Jesus Christ, through the grace of His baptism, strengthen us to live in faith and righteousness throughout this year. May He, who stood in the midst of the Jordan, grant enduring peace to our nation and bestow health and divine blessings upon all our people. May God Bless Ethiopia! Abba GerimaBishop of the Diocese of Gedeo, Kore, and BurjiMember of the Holy Synod

In the Name of the Father, and of the Son, and of the Holy Spirit, One God. Amen. Read More »

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት!

ኤክቱስ ጥር 10/2018 ዓ.ም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። በሀገረ ስብከታችን፣ በሀገር ውስጥና በሌሎች ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ወምእመናት፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ድኅነተ ዓለም ሲል በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ለተጠመቀበት፣ ለታላቁ የአደባባይ በዓላችን ለብርሃነ ጥምቀቱ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ! “ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ  ደንገፁ ቀላያተ ማያት ወድምጸ ማያቲሆሙ – አቤቱ ውኃዎች አዩህ ውኃዎችም አዩህና ፈሩ ጥልቆችም ተነዋወጡ ውኃዎችም ጮሁ።” መዝ. ፸፮፥፲፮ ይህ የቅዱስ ዳዊት ቃለ ትንቢት ባሕርየ ሰብእን ለማዳን በተዋሕዶ ሰው የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሊጠመቅ በቆመ ጊዜ ግዑዛን ፍጥረታት ፈጣሪያቸውን አውቀው ያሳዩትን ድንጋጤ የሚገልጽ ነው። ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ የሄደው መጠመቅ የሚገባው ሆኖ ሳይሆን፣ እርሱ ማየ ሕይወት በመሆኑ “አፍላገ ማየ ሕይወት ዘይውኅዝ እምከርሡ – ከሆዱ የሕይወት ውኃ ወንዝ ይፈስሳል” (ዮሐ. ፯፥፴፰) ተብሎ እንደተጻፈ፤ ውኃውን ቀድሶ ለእኛ የልጅነት መገኛ እንዲሆንልን ነው። በዚያን ዕለት ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የሸሸውና ጥልቆች የተነዋወጡት፣ በማዕከለ ዮርዳኖስ የቆመውን የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት ተረድተው ነው። ይህ ምስጢርም “ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ – ባሕር አየችና ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” (መዝ. ፻፲፫፥፫) ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተመሰከረ፣ የሰው ልጅ የኃጢአት ዕዳ ተደምስሶ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገረበት ታላቅ የድል ቀን ነው። የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ለእኛ የድኅነትን መንገድ ሊከፍትልንና በጥምቀቱ የኃጢአት ዕዳችንን ደምስሶ አዲስ ሕይወትን ሊሰጠን ነው። በመሆኑም ይህን ታላቅ የድኅነት በዓል ስናከብር ክርስቶስ የከፈለንን ዋጋ እያሰብንና በጥምቀት ካገኘነው ልጅነት ጋር በሚስማማ ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ሊሆን ይገባል። በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት ከሚጋርዱ፣ ከቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ሥርዓት ውጭ ከሆኑና የምስጢረ ጥምቀቱን ረቂቅነት ከሚያደበዝዙ ሥጋዊ ድርጊቶች ተቆጥበን፤ በዓሉን በሥርዓተ አምልኮ፣ በጸሎት እና መልካም ሥራዎችን በመሥራት  ልናከብረው ይገባል።  በመጨረሻም፣ ይህ የ፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት የጥምቀት በዓል አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ የሰጠንን የልጅነት ጸጋ በሃይማኖትና በምግባር አጽንተን እንድንኖር ይርዳን። በማዕከለ ዮርዳኖስ የቆመው የባሕርይ አምላክ ለሀገራችን ሰላምን፣ ለሕዝባችንም ጤናንና በረከትን ያድልልን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! አባ ገሪማየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት! Read More »

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በሀገረ ስብከቱ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ!

ኤክቱስ ጥር 6/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሚሠሩ በርካታ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ሀገረ ስብከቱ በዲላ ከተማ የሚያስገነባው የመንበረ ጵጵስና ግንባታ፣ በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚሠራው የውኃ እና የዶሮ ልማቶች ተጎብኝተዋል። በተጨማሪም በአንዲዳ የሚገኘው የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት መደበኛ የመማር የማስተማር ሂደት፣ አዲስ ለመገንባት የታሰበበት ቦታ፣ የተማሪዎች የማደርያና የመመገቢያ ክፍላት እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቱ ጽሕፈት ቤት ተጎብኝቷል። ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ በአጠቃላይ ስለሚሠሩ የልማት ሥራዎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከቱ የተሠሩ ሥራዎችን እና ደቀ መዛሙርቱን በመጎብኘታቸው እና ቡራኬ በመስጠታቸው እጅግ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በተመለከቱት ሥራዎች ፍጥነት መገረማቸውን የገለጹ ሲሆን ሁሉም አካል ከብፁዕነታቸው አጠገብ ከሆነ ከዚህ በላይ በርካታ ሥራዎችን በሀገረ ስብከታቸው እንደሚሠሩና ገና ብዙ ያልተጠቀምንባቸው አባት መሆናቸውን ገልጸው እግዚአብሔር ሀገረ ስብከቱን በፍጹም ሰላም እንዲጠብቅ በመማጸን ጉብኝታቸውን በጸሎት ፈጽመዋል። በመርሃግብሩ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌን ጨምሮ የክፍል ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በሀገረ ስብከቱ የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ! Read More »

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ፍቁረ እግዚእ) ዓመታዊ በዓል በዲላ ማረሚያ ተቋም ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ!

ኤክቱስ ጥር 4/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ስር በሚገኘው የዲላ ማረሚያ ተቋም የፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሱ ዓመታዊ የፍልሰቱ መታሰቢያ በዓል ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት ተከብሮ ውሏል። በዲላ ከተማ የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሥፍራው ተገኝተው የዕለቱን በዓል የሚገልጽ ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል። ይህ በማረሚያ ተቋሙ ውስጥ የሚገኘው የፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ለታራሚዎች መንፈሳዊ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በሥነ-ልቦና ጥንካሬ እና በሥነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የሀገረ ስብከቱ የምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ መምህር በየነ ክፍሌ ገልጸዋል። በዕለቱ ብፁዕነታቸው ለታራሚዎች እና ለበዓሉ ታዳሚዎች የዕለቱን ትምህርት አስተምረዋል። ብፁዕነታቸው በትምህርታቸው የቅዱስ ዮሐንስን የፍቅርና የጽናት ሕይወት መነሻ በማድረግ፣ ታራሚዎች በማረሚያ ቆይታቸው በሥነ-ምግባር ታንጸው ለተሻለ ሕይወት እንዲዘጋጁ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል። በተጨማሪም የሕግ ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚያሳልፉት ጥቂት ጊዜ ብቻ መሆኑን በመግለጽ ከዚህ በላይ ግን ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ከዘለዓለም እስራት ነጻ መውጣት እንደሚገባ በመግለጽ መርሃ-ግብሩን በጸሎት አጠናቅቀዋል።

የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ፍቁረ እግዚእ) ዓመታዊ በዓል በዲላ ማረሚያ ተቋም ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ! Read More »

እመኬ ፈቀድኩ የሀሉ እስከ ሶበ እመጽእ ሚ ላዕሌከ(እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?) ዮሐ ፳፩ ፥ ፳፪

ጥር ፬ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ከዚህ ዓለም የተሰወረበት ዕለት ነው ።የቅዱስ ዮሐንስን መሰወር ከመናገራችን በፊት ቅዱስ  ዮሐንስ ወንጌላዊ ማን ነው ?ምን ምን አደረገ የሚሉትን ነጥቦች በአጭር እንመልክት።ቤተሰቦቹ፦ የቅዱስ ዮሐንስ አባቱ ዘብዴዎስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ማቴ 4፥21 እናቱንም የዘብዴዎስ ልጆች እናት በማለት ስሟን ሳይጠራ ይገልጣታል። ማቴ 27፥56 20፥22 የትርጓሜ ሊቃውንት ግን ማርያም ባውፍልያ ናት በማለት ገለጠዋታል።ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንሰ ክርስቶስን ከመከተሉ በፌት    የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር። ዮሐንስ መጥምቅ እነሆ የእግዚአብሔር  በግ ብሎ ሲያስተምር ሰምተው ክርስቶስን ከተከተሉት ከሁለቱ ደቀመዛሙርት ስሙ ያልተጠቀሰው  አንዱ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው ዮሐ 1፥35-41። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ለሐዋርያነት የተጠራው ከአባቱና ከወንድሙ ጋር በገሊላ ባሕር ዓሣ ሲያጠምድ ነው ።እነርሱም ከወንድሙ ጋር ዓሣ የሚያጠምዱበትን መረብ እና አባታቸውን በመተው ክርስቶስን እንደተከተሉት በመጽሐፍ ቅድስ ተመዝገቧል ማቴ 4፥21 ክርስቶስን ለመከተል ዓለማዊ ነገርን ሁሉ ትቶ መከተል እንደሚገባ የተማርነው ከሐዋርያት ነው ። ክርስቶስን ለመከተል መረብን(ወጥመድን) መተው ያስፈልጋል።አንድ አንድ ጊዜ ዓሣ የምናሠግርበት መረብ እኛን የሚያሠግርበት አጋጣሚ ይፈጠራል ስለዚህ  መረብን መተው ክርስቶስን ለመከተል ቁልፍ ጉዳይ ነው ። መረብ ለዓሣ አሥጋሪ የኑሮ መሠረትና  ሀብት ነው ። ዮሐንስ ግን ዘለዓለማዊውን ሀብት ክርስቶስን ለማግኘት ጊዜያዊውን ሀብት መረቡን ትቷል። የዮሐንስ ስሞች፦ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን ከተከተለ በኋላ ብዙ ስሞች ተሰጥተውታል እነርሱም ፦              1 ወልደ ነጎድጓድ ተብሏል              2 ፍቁረ እግዚእ   ተብሏል              3 ቴዎጎሎስ/ታዎጎሎስ ተብሏል              4 አቡቀለምሲስ ተብሏል1ኛ ወልደ ነጎድጓድ ብሎ የሰየመው መድኅነ ዓለም ክርስትስ ነው ። ዮሐንስንና ወንድሙ ያዕቆብን በአኔርጌስ ብሏቸዋል ትርጉሙም  ደቂቀ ነጎድጓድ/የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው ማር 3፥17ይህም  ማለት ደቂቀ ምስጢር ማለት ነው። ይህም ስም ለቅዱስ  ዮሐንስ ይስማማዋል ብዙ ምስጢራት በራዕይ ተገልጠውለታልና።2ኛ ፍቁረ እግዚእ (ጌታ የሚወደው ደቀመዛሙር )  ተብሏል ይህስያሜ በዮሐ 13፥23 ላይ ተመዝግቧል ። ጌታ የሚወደው መባሉም ከሌሎች ደቀ መዛሙርቱ አብልጦ ይወደው ስለነበረ ነው። ከሌሎች በተለየ የዮሐንስ መወደዱ ዮሐንስ በእምነቱ ጠንካራ ስለነበረ ነው።ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ከመስቀሉ ሥር የተገኘ ዮሐንስ ብቻ ነውና ዮሐ19፥26 በዚህም  በእምነቱ ምን ያህል  ጠንካራ እንደሆነ እንረዳለን።  3 ቴዎሎጎስ /ታዎሎጎስ ተብሏል። ነባቤ መለኮት ማለት ነው  ይህም ማለት የአምላክን የመለኮትን ነገር የተናገረ ማለት ነው ። ዮሐንስ ነባቤ መለኮት የተባለበት ምክንያት «በመጀመርያ ቃል ነበረ » ዮሐ1፥1በማለት የወልድን መለኮታዊ ህልውና፣የወልድን ቀዳማዊነት እና የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ስለ ተናገረ ነው።4 አቡቀለምሲስ ይባላል ።አቡቀለምሲስ የጽርዕ ቃል ነው። በግእዝ አበ ራዕይ አበ ትንቢት ማለት ሲሆን በአማርኛ ደግሞ ባለ ትንቢት የትንቢት ባለቤት ባለ ራዕይ የራዕይ ባለቤት ማለት ነው ።ሁለተኛው ትርጉም ረዐየ ኅቡአት/የተሰወሩ ነገሮችን የሚያይ ማለት ነው ። ዮሐንስ በልዩ ልዩ ፀጋዎች የደመቀ ሐዋርያ ነው ።ፀጋውም፦ ንጽሕና ፣ ቅድስና እና ድንግልና ናቸው።እንደ ዮሐንስ ስለ ንጽሕና የተነገረለት ሐዋርያ የለም።ቅዱስ ያሬድ ዮሐንስን ስለ ንጽሕናው እንዲህ  ይገልጠዋል፦ ለትጉሓን ይኤምሮሙ እስመ ኀብረ ንጽሐ ምሥሌሆሙ ዮሐንስ ክቡር ሰባኬ ወንጌል መምህር ወድንግል /ወንጌልን የሚሰብክ ክቡር መምህር ዮሐንስን መላእክትን ይመለከታቸዋል ፤ በንጽሕና ከእነርሱ ጋር አንድ ሆኗልና በማለት የዮሐንስን  ንጽህና ይገልጠዋል።/ድጓ ገጽ 191/ሀገረ ስብከቱ፦ ሐዋርያት ጌታ ካረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስንም ከተቀበሉ በኋላ ይህን  ዓለም  በዕጣ ተካፍለው ለስብከተ ወንጌል ወጥተዋል።ዕጣ በሚጣጣሉበትም ጊዜ ምድረ ጽርዕ /ግሪክ/ለቅዱስ ዮሐንስ ደርሳዋለች። በምድረ ጽርዕ በኤፌሶን አርጤምስ የምትባል ጣዖት ትመለክ ነበር። ዮሐንስ ሰው በሚመለከት ሀገር አልሄድም ብሎ ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስ አጽናንቶ ወስዶ አድርሶት ተመልሷል።እንዲህ ሆኖ ቢሄድም ቅሉ ወንጌልን ለማስተማር ምቹ ሁኔታ ባለማግኘቱ ምክንያት ከደቀ መዝሙሩ ከአብሮኮሮስ ጋር በመመካከር ከአንዲት ሮምና ከምትባል ሴት ቤት አግልጋይ በመሆን ገቡ።ዮሐንስ ለውሽባ ቤት እሳት  አንዳጅ ሆነ።ደቀመዝሙሩ አብሮኮሮስም አጣቢ/ጽዳተኛ/ሆነ።ሮምናን በተአምራት /የሞተውን  ልጅ በማስነሳት/አሳምነው አግልግሎታቸውን ጀምረዋል።በጣም የሚገርመኝ ግን ፦ አባቶቻችን ሐዋርያት የክርስቶስን ወንጌል ለዓለም ለማዳረስ ብዙ ዓይነት መንገዶችን ተጠቅመዋል  የጽዳት ሰራተኛ በመሆን ፣ከሕመምተኞች ጋር ሕመምተኛ  በመሆን ፣የውሽባ ቤት እሳት አንዳጅ በመሆን…አስተምረዋል። የእኛ ዘመን ሐዋርያት ግን ይገርሙኛል ለ3 ቅን አገልግሎት 50እና 60 ሺህ ብር ይጠይቃሉ የሚገርም ነው! ይህም እንኳ ተከፍሏቸው  በሰዓት  ቢገኙ መልካም ነበር። ምን አልባት እነ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ የሰባኪዎችን ሁኔታ በአካለ ስጋ ቢያዩት ምን ይሉ ይሆን! ቅዱስ ዮሐንስ ግን የክርስቶስን ወንጌል ያስተማረ የቤት ሰራተኛ በመሆን ነበር። ያውም የሞተውን  ልጅ አስነስቶ  ቅድስናው እስኪታወቅ ድረስ በመገፋትና በመለጋት ነበር። ይህን ድንቅ ተአምር ከፈጸመ  በኋላ ግን ሮምናን ከነቤተሰቦቿ  የክርስቶስን  ልጅነት እንድታገኝ አስተምሯታል። በኋላም ከንጉሡ ጀምሮ እስከ ሕዝቡ ድረስ በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል።ቅዱስ ዮሐንስም ወንጌልን እያስተማረ ብዙ ድንቅድንቅ ተአምራትን አያደረገ ብዙ ዘመን  ኑሯል ። ለሕዝቡም               ካህናትን ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ  ወደሌሎች አቅራቢያ ሀገሮች ሄደ።በመጨረሻም በከሀዲውና በጨካኙ ንጉሥ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ ። በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋላ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት ።በዚያም ሳለ ራዕዩን አይቶ ጻፈው ።ክፉዎች  ያሰቃየነው ቢመስላቸውም እግዚአብሔር ግን ለራዕይ ተስማሚ የሆነ ቦታ አዘጋጅቶለት ነበር!ድምጥያኖስ ከሞተ በኋላ ከግዞት ተመልሶ ወንጌሉንና ሶስቱን መልእክታቱን ጽፋል።እግዚአብሔር ሙት ያላለውን መግደል ስለማይቻል ከሳሾቹ ሲሞቱ እንዲሞት የተፈረደበት ቅዱስ ዮሐንስ ግን በሕይወት ወደቦታው ተመልሶ ወንጌልን ያህል  የአምላኩን ቃል ለመጻፍ በቃ።እግዚአብሔር ሲመርጥ ከግዞት ቤት አውጥቶ ሥራ  ያሠራል /ወንጌልን ያጽፋል/። አንዳዱ ደግሞ ከክርስቶስ ወንጌል ወጥቶ  በሉተር ተረት ያብዳል።ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ከማስተማር በተጨማሪ ታዋቂ እና የተዋጣለት ስዕል ሳይ ነበር።የክርስቶስን ስዕለ ስቅለት በመጀመርያ የሳለው እርሱ ነው ።ቅዱስ ዮሐንስ ከሶስቱ  የምስጢር ደቀመዛሙርት አንዱ ነው እናታችን ድንግል ማርያምንም ከመስቀሉ ስር በእናትነት የአዳምን ልጆች ወክሎ የተቀበለ እርሱ ነው ። እንዴት ያስደስታል የሚወዳትን  እናቱን ለሚወደው ደቀመዝሙሩ  ሰጠው ።ለድንግሉ ደቀመዝሙሩ ድንግል እናት ሰጠው።ቅዱስ ዮሐንስ እስከ መጨረሻው መጽናቱ ድንግል ማርያምን በእናትነት ለመቀበል አብቅቶታል ።ዮሐ 19፥26 ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ሁሉም ሐዋርያት ሲበተኑ እርሱ ብቻ ቅርቶ ነበርና ነው ። በመጨረሻም ከዚህ ዓለም የሚሰወርበት ጊዜ ሲደርስ 99 ዓም ደቀመዛሙርቱን የመቃብር ገደል አስቆፍሮ ለኤፌሶን ሰዎች በተማራችሁበት ትምህርት  ጸንታችሁ ኑሩ የሚል መልእክት አስተላልፎላቸው ከዚያ ውስጥ ገብቶ ከጸለየ በኋላ እንደ ሄኖክና እንደ ኤልያስ ወደ ብሔረ ሕያዋን ሄዷል።ከላይ በርእሱ እንደተጠቀሰው  አስቀድሞ ጌታ የሐንስ እስከ ዳግም ምጽአት ሞትን እንደማይቀምስ ተናግሮለት ስለ ነበር ሞትን አልቀመሰም። ዮሐንስ ሞትን እንደ ማይቀምስ ሁለት ጊዜ ተናግሯል፦   1እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ በመንግሥቱ እስኪመጣ ሞትን የማይቀምሱ አሉ ብሎ ነበር ሜቴ16፥28 በዚህ  ንባብ ውስጥ ማን እንደ ማይሞት አልተጠቀሰም ነገር ግን የሞይሞት እንዳለ ተገልጧል።   2 ሁለተኛው እኔ እስክመጣ ቢኖር ምን  አግድህ?ያለው ነው ዮሐ 21፥22 በዚህ ንባብ ውስጥ ደግሞ ዮሐንስ ሞትን እንደማይቀምስ በግልጥ ክርስቶስ አስተሞሯል። ስለዚህ ቅዱስ ዮሐንስ  ወንጌላዊ ሞትን አልቀመሰም።ጥር አራት ቀን ወደ ብሔረ  ሕያዋን ሄዷል።

እመኬ ፈቀድኩ የሀሉ እስከ ሶበ እመጽእ ሚ ላዕሌከ(እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ?) ዮሐ ፳፩ ፥ ፳፪ Read More »

አስራ አንድ የሕግ ታራሚ ኢ-አማንያን በብፁዕ አቡነ ገሪማ ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አገኙ!

ኤክቱስ ጥር 4/2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ማረሚያ ተቋም በሚገኘው በወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ አስራ አንድ የሕግ ታራሚዎች በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል። ተጠማቂዎቹ ከዚህ በፊት የቅድመ ጥምቀት መደበኛ ትምህርት የተማሩ መሆናቸውንና አሁን ደግሞ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ኃይማኖት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን እና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እየተማሩ እንደሚገኙ ተገልጿል። በተጨማሪም የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና የምግባረ ሰናይ ክፍላት ከመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት እንዲሁም ከማረሚያ ቤቱ ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በመተባበር እንደተሠራና ሌሎችም በርካታ ሥራዎች በመሠራት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ተጠማቂያኑ በኃይማኖት እንዲጸኑና እንዲበረቱ እንዲሁም መንፈሳዊ ትምህርታቸው በሚገባ እንዲከታተሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰው በጸሎት ፈጽመዋል።

አስራ አንድ የሕግ ታራሚ ኢ-አማንያን በብፁዕ አቡነ ገሪማ ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አገኙ! Read More »

Scroll to Top