በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በዛሬው ዕለት የተጠመቃችሁ ልጆቻችን ከዛሬ ጀምሮ በቤቱ ያላችሁ የክርስቶስ ሙሽራዎች ናችሁ!ብፁዕ አቡነ ገሪማ

ኤክቱስ ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት የይርጋጨፌ ደብረ ታቦር አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን በነበረው የሰንበት መርሃግብር ጉባኤ ላይ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ኃይማኖት ብዙአየሁ ዳመነ የዕለቱን ትምህርት በጌዴኡፋ ቋንቋ ያስተማሩ ሲሆን፣ በመቀጠል በማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል የስብከተ ወንጌልና ዜማ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ በመምህር መልአኩ ጌታቸው የማኅበሩ መግለጫ ተነቧል። እንዲሁም በደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት፣ በነባር አባላትና በማኅበረ ቅዱሳን ይርጋጨፌ ወረዳ ማዕከል የመዝሙር ክፍል አባላት ዝማሬ ቀርቧል።

በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በመልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ ጋባዥነት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተለያዩ ቋንቋዎች መዝሙር በመዘመርና የዕለቱን ወንጌል በማንሳት በአማርኛ፣ በጌዴኡፋ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች አስተምረዋል።

ብፁዕነታቸው በንግግራቸው መካከል “በዛሬው ዕለት ቤተ ክርስቲያናችን አዳዲስ ምዕመናንን አግኝታለች፤ ይህ በሰማያት በቅዱሳን በመላእክት ዘንድም ትልቅ የምስራች ነው። በዛሬው ዕለት የመጣችሁ ልጆቻችን እንኳን የክርስቶስ ልጆች ለመሆን አበቃችሁ! ከዛሬ ጀምሮ በቤቱ ያላችሁ የክርስቶስ ሙሽራዎች ናችሁ” በማለት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈው መርሃ ግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል።

Scroll to Top