ኤክቱስ ግንቦት 26/2018 ዓ.ም
“አቤቱ፥ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀለውም?” (ራእ ፮፥፲)
በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በአሰኮ እና በሺርካ ወረዳዎች ከግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በንጹሃን ምእመናን ላይ የተፈጸመው ግድያ የሰዎች መፈናቀል እንዲሁም ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው የጠላታ ጨፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በእሳት መውደም እና የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን መዘረፍ ቤተክርስቲያናችንን በጥልቅ ሐዘን ውስጥ ጥሏታል። በአካባቢው መሰል የጸጥታ ችግሮች በተደጋጋሚ መከሰታቸውና ንጹሃን ዜጎች፣ እናቶችና ሕፃናት ለከፋ እንግልትና ስደት መዳረጋቸው ሊታረም የሚገባውና ሁላችንንም በእጅጉ ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል።
በመሆኑም መንግሥትና የጸጥታ አካላት ሕግና ሥርዓትን የማስከበር እንዲሁም የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአስቸኳይ እንዲወጡ እናሳስባለን። በጥቃቱ ላይ እጃቸው ያለበትን አካላት ለሕግ በማቅረብ፣ ለተፈናቀሉና መጠለያ ላጡ ወገኖቻችን አስፈላጊው ድጋፍና መልሶ ማቋቋም እንዲደረግላቸው፣ እንዲሁም ለአብያተ ክርስቲያናቱ እና ለምዕመናን አስተማማኝ ጥበቃ እንዲደረግ በጽኑ እንጠይቃለን።
በዚህ ከባድ ፈተና ውስጥ ለምትገኙ ለሟች ቤተሰቦችና ለተፈናቀሉ ምእመናን በሙሉ እግዚአብሔር መጽናናትን እንዲሰጣችሁ እንጸልያለን። እግዚአብሔር አምላክ ለተጎዱት መጽናናትን ይስጥ፤ ሀገራችንንና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ።
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
