ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤና በዓለ ንግሥ በጪጩ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከታኅሣሥ 17-19 2018 ዓ.ም ስለተዘጋጀ ሁላችሁም እንድትሳተፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!
ኤክቱስ ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት
ኤክቱስ ታኅሣሥ 7/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሀገረ ስብከቱን የፋይናንስ አስተዳደር ለማሻሻል የሚያስችል ውይይት ከአስተዳደር አካላት ጋር አደርገዋል። የውይይቱ ዋና ትኩረት የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ሲጠቀምበት የቆየውን ድርብ የሒሳብ አመዘጋገብ (Double-Entry Accounting) ሥርዓት በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተግባራዊ ማድረግ ላይ ነበር። የሀገረ ስብከቱ የፕሮጀክት ማናጀር ቀሲስ ጤናው እንዳላማው ስለ ድርብ የሒሳብ አመዘጋገብ (Double-Entry) አስፈላጊነት ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል። ይህ ሥርዓት እያንዳንዱ ገንዘብ በሁለት የሒሳብ መዝገቦች መመዝገብ እንዳለበት የገለጹ ሲሆን ይህም የሒሳብ ስህተቶችን ለመቀነስ እና የገንዘብ አያያዝን ሚዛናዊ (Balanced) ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል። በውይይቱ የተሳተፉት የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የአስተዳደር አካላት ሀገረ ስብከቱ ይህንን ዘመናዊ ሥርዓት ወደ አድባራት ለማውረድ እየሠራ ያለው ሥራ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በአግባቡ እና በግልጽነት ማስተዳደር እንዲቻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹ ሲሆን ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ይህንን የዘመናዊ የሒሳብ ሥራ በብቃት ለመምራት የሚያስችል የሰው ኃይልን ለማጠናከር በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ የተመረቀ እና የሒሳብ ሥራዎችን በብቃት ለመሥራት የፒችትሪ (Peachtree) አመዘጋገብ ሶፍትዌር ዕውቀት ያለው ሰው እንዲቀጠር ተወስኗል። ይህ ቅጥር ሀገረ ስብከቱ በፋይናንስ አያያዝ ሂደት ግልጽነትን እና የሥራ ቅልጥፍናን ለማምጣት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተገልጿል። በውይይቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የሀገረ ስብከት የክፍል ኃላፊዎች፣ የመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና ጸሐፊ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የአስተዳደር አካላት ተገኝተዋል።
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሒሳብ አያያዝን ለማዘመን የሚያስችል ውይይት ከአስተዳደር አካላት ጋር አደረጉ! Read More »
ኤክቱስ ታኅሣሥ 5/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በቆቲ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቅድመ ጥምቀት መደበኛ ትምህርት ከተማሩ አንድ መቶ አርባ ዘጠኝ ንዑሰ ክርስቲያን መካከል ሰባ ስምንት ወንድ እና ስድሳ ሦስት ሴት በድምሩ አንድ መቶ ሠላሳ ሁለቱ በዛሬው ዕለት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል። ኢ-አማንያን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱና የሥላሴን ልጅነት እንዲያገኙ ማድረግ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ተልእኮ ከመሆኑ አንጻር ሀገረ ስብከቱ ይህንን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እያስፈጸመ ይገኛል። አዳዲስ አማንያንን የማስጠመቁን ሥራ የደብሩ ስብከተ ወንጌል ከደብሩና ከወረዳ ቤተ ክህነቱ ጋር በመናበብ የተሠራ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ አስራ ሰባት አዳዲስ አማንያንን ለማስጠመቅ ቅድመ ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውን ገልጸዋል። በዕለቱ የዕለቱን ትምህርት የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ በጌዴኡፋ ቋንቋ አስተምረዋል። በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በጌዴኡፋ እና በአፋን ኦሮሞ ዝማሬ ዘምረው እንዲሁም አዳዲስ የተጠመቁ ምዕመናንን ማጽናት እንደሚገባ ገልጸው በአፋን ኦሮሞ እና በአማርኛ ቋንቋዎች ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው በጸሎት ፈጽመዋል። በመርሃግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ የመንፈሳዊ ትምህርትና የካህናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን እሸቱ ማሞ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ምዕመናን ተገኝተዋል።
አንድ መቶ ሠላሳ ሁለት አዳዲስ አማንያን በብፁዕ አቡነ ገሪማ ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አገኙ!! Read More »
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ከዚህ በታች ባለው ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟላ ሠራተኛ አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል። ኤክቱስ ኅዳር 28/2018 ዓ.ም
ኤክቱስ ኅዳር 2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ አስተባባሪነት ከ”ICIPE (INTERNATIONAL CENTRE OF INSECT PHYSIOLOGY AND ECOLOGY)” ከተባለ በንብ ማነብ፣ በሐር ትል፣ እና በታዳሽ ኃይል ዙርያ ከሚሰራ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር ሊሠሩ በታሰቡ የግብርና ፕሮጀክቶች ዙርያ ውይይት እና ፕሮጀክቱ በሚሠራባቸው ቦታዎች ጉብኝት ተደርጓል። ጉብኝቱ መነሻውን ያደረገው በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ በአንዲዳ መድኃኔዓለም የሚገኘው የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት፣ የዳማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እና በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ እየተሠራ በሚገኘው የዶሮ እርባታ ሥፍራ፣ የንብ ማነብ ሥራ እንዲሁም የሚሠሩ በርካታ የግብርና ሥራዎች ጉብኝትና ወደፊት በሚሠሩ ሥራዎች ዙርያ ጥናት ተደርጓል። ጉብኝቱ የድርጅቱ ሠራተኞች ከሆኑት ከዶክተር ወርቅነህ አያሌው እና አቶ ልዑል ሰገድ በላይይሁን እንዲሁም ከደቡብ አስተባባሪ ዲያቆን አሳሳኸኝ ጋር ተደርጓል። በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጽሕፈት ቤት ስለአጠቃላይ ሥራዎችና ወደፊት በምን አይነት መንገድ በጋራ መሥራት እንደሚቻል ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በዕለቱ በአራቱም ቦታዎች የነበረው ጉብኝት እንዲሁም ወደፊት ሊሠሩ ስለታሰቡ ሥራዎች የተደረገው ውይይት ውጤታማ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ከዚህም በኋላ ሀገረ ስብከቱ ከድርጅቱ ጋር በጋራ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው እንዲሁም ይህንን ሥራ በጋራ ለመሥራት ለመጡት ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበው በጸሎት ፈጽመዋል።
በሀገረ ስብከቱ የተለያዩ የግብርና ፕሮጀክቶችን መሥራት የሚስችል ጉብኝትና ውይይት ተደረገ!! Read More »
ቃሉን የተናገረው ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስ ነውየስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ ሆሴዕ፣ ኢያሱ፣ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት እንደኾነ መድኃኒት መባሉ ግን እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ 13ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ ተልእኮውን የሚገልጥ ነው እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሊመጣ ያለው መሲሕ ማለትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ፣ ቀስ በቀስ አድጎ፣ የደቂቀ አዳምን ሕማም ተሸክሞ አጠቃላይ የሰው ልጆችን በአስደናቂ መጎብኘትን ጎብኝቶ እንደሚያድናቸው ስለሚናገር “ኢሳይያስ – መድኃኒት” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡አባቱ አሞጽ እናቱ ደግሞ ሶፍያ ይባላሉ።ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲኖር በአካዝና በሕዝያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥት አማካሪ ነበር፡፡ በራሱ መጽሐፍ እንደነገረንም በዘመኑ የነበሩ የይሁዳ ነገሥታት ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ ይባላሉ /ኢሳ.1÷1/የነቢይነትን ሥራ የዠመረውም ወዳጁ ዖዝያን በሞተ በዓመቱ ነው፡፡ ይኸውም በ740 ዓ.ዓ. አከባቢ ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ዖዝያንን ገስጽ” ሲባል ወዳጁ ስለኾነ ይሉኝታ ይዞት እምቢ ብሎ ነበር፡፡ ከዚኽም የተነሣ ከአፉ ላይ ለምፅ ወጣበት፡፡ ጌታም ተገልጦ፡- “የምትወደውና የምታከብረው ዖዝያን ሞተ፤ መንግሥቱም አለፈ፡፡ ሞት፣ ኅልፈት፣ በመንግሥቴም ሽረት የሌለብኝ እኔ አምላክኽ ብቻ ነኝ” አለው፡፡ ኢሳይያስ ይኽን ሲሰማ እጅግ ደነገጠ፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር፡- “ወደዚኽ ሕዝብ ማንን ልላክ?” አለው፡፡ ኢሳይያስም፡- “እኔ እሔድ ነበር፤ ግን በአፌ ለምፅ አለብኝ” ሲል መልአኩ በጉጠት አፉን ቀባውና ለምፁ ድኖለት ትንቢት ተናግሯል ። “ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ” ኢሳ 6÷6 ያለውም ለዚህ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ሃያ አራት ሊቃነ መላእክትን መርጦ በመንበረ መንግሥት ዙሪያ ክንፍ ለክንፍ አያይዞ አቁሟቸዋል፡፡ የብርሃን ዘውድ (አክሊል) ደፍቶላቸዋል፡፡ የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ አስይዟቸዋል፡፡ እንደዚህ አድርጎ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህም ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ይባላሉ፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እንደምናገኘው በየዓመቱ ኅዳር 24 ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሰማያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የካህናተ ሰማይ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ካህናተ ሰማይ አገልግሎት የሚያስገነዝብ አጭር ትምህርት እንማማራለን። ሱራፊ ማለት መልአክ፣ ከካህናተ ሰማይ አንዱ ማለት ነው፡፡ ሱራፌን፣ ሱራፌል፣ ሱራፌም (በፅርዕ ሴራፊም፣ በዕብራይስጥ ስራፊም) ማለት የነገድ ስም፣ ልዑላን መላእክት፣ ሊቃናት፣ የሚያጥኑ፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ቀዳሾች ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፰፻፹፮/፡፡ ከዚህ ላይ ሱራፊ ነጠላ ቍጥርን፤ ሱራፌል ደግሞ ብዙ ቍጥርን ያመለክታል፡፡ ሱራፌል ለቅዱሳን በሰው አምሳል በመገለጣቸው ሽማግሌዎች ተብለው ተጠርተዋል /ኢሳ.24፥23፤ መሳ.13፥2 ፤ ዳን.10፥18/፡፡ በግእዝ ቋንቋ ደግሞ ካህናተ ሰማይ ይባላሉ፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው የሚሰጡትን ሰማያዊ አገልግሎት የሚያመለክት ስም ነው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በዙሪያውም ሃያ ዐራት ካህናት አሉ፡፡ በፊታቸው የበጉን ሥዕል፣ ደምን የተረጨች ልብስንም፣ የታተመ መጽሐፍንም ያያሉ፡፡ መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› /ራእ. 4፥6 ፤5፥8/ በማለት ስለ ሱራፌል ሰማያዊ አገልግሎት የተናገረ ሲኾን፣ ‹‹በፊታቸው የበጉን ሥዕል ያያሉ›› ማለቱ የክርስቶስን ትስብእት በጌትነት ያዩታል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ወደቁ›› ሲልም መስገዳቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹በግ›› የተባለውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ደምን የተረጨች ልብስ›› ማለቱም ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ መቀበሉን፤ የታተመ መጽሐፍ የክርስቶስ ትስብእት የማይመረመር መኾኑን፤ ‹‹ለበጉ ሥዕል፣ ለታለለችው ልብስና ለታለለው መጽሐፍ ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› ሲልም ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትም በሦስትነትም ለሚመለከው ለክርስቶስ ደግመው ደጋግመው ምስጋና ማቅረባቸውንና መገዛታቸውን ያመለክታል /የሠለስቱ ምእት ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ፣ 3፥7-9/፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤልም ካህናተ ሰማይ ያለ ዘር መገኘታቸውን ሲያመለክት ‹‹በመንበሩ ዙሪያ ቁመው ያሉ ካህናት ኅብራቸው መረግድ የሚባል ዕንቍን ይመስላል›› በማለት ተናግሯል፡፡ ጸጋቸውን ሲገልጽ ደግሞ ‹‹ብሩህ ልብስ ለብሰዋል፤›› ክብራቸውን ሲመሰክርም ‹‹በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተዋል›› ብሏል፡፡ ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የንጽሕናቸውና የቅድስናቸው መገለጫ ሲኾን፣ በራሳቸው ላይ የተቀዳጁት ዘውድ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ዘለዓለማዊ ክብር ያሳያል፡፡ ቍጥራቸው በሃያ አራት መገለጹም ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ኾኗቸው ለሃያ አራት ሰዓታት ሳያቋርጡ ጸሎትና ምስጋናን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡ ካህናተ ሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሲያቀርቡ አክሊሎቻቸውን ከራሳቸው ላይ አውርደው ያለማቋረጥ ይሰግዳሉ፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ይህንን ሰማያዊ ሥርዓት እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ ‹‹ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ፤ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) በመንበሩ ዙሪያ ቆመው በፊቱ ሲሰግዱ የመለኮት እሳት ሲበርቅ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ፤›› /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡ ይህም ምስጋና በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ የጸሎት ክፍሎች ይገኛል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ አለ ፤ ቅዱሳን መላእክት ለመራዳት፣ ለመጠበቅ፣ ለመታደግ ፣ ከተፍገመገምንበት ለማንሳት ፈጥነው ደራሽ መሆናቸውን ሲነግረን ነው ። እለ ስድስቱ ክነፊሆሙ ይላቸዋል ። ልዑል እግዚአብሔር የሰጣቸው ፀጋ ብዙ መሆኑን ሲያሰረዳን ነው ።በእውነት ከሱራፌል አንዱ እየበረረ መጥቶ በጦርነት ለምጽ የተመታችውን ሀገራችነን ይፈውስልን ። የ24ቱ ከህናተ ሰማይ በረከታቸው ረድኤታቸው ይደርብን ይዋልብን ። መልአከ ሰላም አምሳሉ ሳለየዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪኅዳር 24/2018 ዓ.ም
ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ ኢሳ 6÷6 Read More »