የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከዚህ በታች ባለው ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟላ ሠራተኛ አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል።
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከዚህ በታች ባለው ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟላ ሠራተኛ አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል። Read More »
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት
“ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ውሰድ” (ማቴ 2:13፣ 19-20) ሕዳር 6 የመልአኩን ቃል በመስማት ወደ ግብፅ የተሰደዱትን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የልጇን የኢየሱስ ክርስቶስን፣ የአረጋዊ ዮሴፍን እና የሰሎሜን ጉዞ የምናስታውስበት ዕለት ነው። ንጉሥ ሄሮድስ የጌታችንን ሕይወት በፈለገ ጊዜ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ “ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ” (ማቴ 2፡13) አለው። እመቤታችንና ታዛዥና ታማኝ ቅዱስ ዮሴፍ ተነስተው በሌሊት ሄዱ፤ ለሦስት ዓመታት ያህልም እንግዳ ሆነው ኖረዋል። ጊዜው ሲፈጸም መልአኩ እንደገና ተገለጦ “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ሂድ” (ማቴ 2፡19-20) የሚል መልእክት ነገረው። ከዓመታት ስደትና መከራ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዮሴፍ እና ሰሎሜን በደቡብ ግብፅ በሚገኘው የቁስቋም ተራራ ደረሱ። እግዚአብሔር ለሙሴ “የቆምክበት ስፍራ የተቀደሰ ምድር ነውና ጫማህን አውልቅ” (ዘጸአት 3፡5) ብሎ እንደተናገረው ክርስቶስ በዚያ ስላደረ ተራራው የተቀደሰ ቦታ ሆነ፤ የፍርሃት ቦታን ወደ በረከት ማደሪያ ለወጠው። እስራኤላውያንን በምድረ በዳ የመራቸው አምላክ ልጁን ወደ ግብፅ መራው፡፡ ይህም ማዳኑ ትውልድን እንደሚሸፍንና ፈተናዎችን ሁሉ ወደ መዳን መንገድ እንደሚቀይር አሳይቷል። የክርስቶስ መገኘት ምድርን ቀደሰ፣ በአንድ ወቅት በጨለማና በጣዖታት የተሞላ ቦታን አበራ በዚህም እሱን ለሚያምኑት ሁሉ ተስፋን ሰጥቷል። የእመቤታችንና የልጇ ጉዞ የነቢያትን ትንቢት ፈጽሟል። ኢሳይያስ፣ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፣ የግብፅም ጣዖታት በፊቱ ይንቀጠቀጣሉ” ኢሳይያስ 19፥1 በማለት ትንቢት ተናግሯል። ሆሴዕም “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” ሆሴዕ 11፥1፤ ማቴዎስ 2፥15 ብሏል። ሙሴ በአንድ ወቅት እስራኤላውያንን በእግዚአብሔር ቸርነት ከግብፅ ባርነት ወደ ነፃነት እንደመራቸው ኢየሱስ ክርስቶስም የሰው ልጆችን ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለማውጣት ወደ ግብፅ ገባ። የመጀመርያው ስደት ሀገርን ነጻ አወጣ፤ ሁለተኛው ስደት ለሰው ልጆች ሁሉ ድኅነትን አቀረበ። ሁለቱም ጉዞዎች የእግዚአብሔርን ኃይል፣ ምሕረቱንና የማይለወጥ የማዳን እቅዱን ያሳያሉ። የቁስቋም ተራራ የቅድስናና የመሸሸጊያ ምልክት በመሆን ክርስቶስ የሚኖርበት ቦታ ሁሉ የተቀደሰ እንደሚሆንና ምእመናን በሚያምኑበት ቦታ ሁሉ “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እኔ በመካከላቸው እገኛለሁ።” ማቴ 18:20 ባለው አምላካዊ ቃሉ በመካከላቸው እንደሚገኝ ያስታውሰናል። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ስም ስደት፣ መከራና ሞት ይደርስባቸዋል። ሆኖም ልጁን በግብፅ የጠበቀው አምላክ ሕዝቡን መጠበቁን ቀጥሏል። ፈተናዎች በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑትን አያሸንፉም፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ዮሴፍ እና ሰሎሜን እንደመራው፣ እያንዳንዱን አማኝ በሕይወት ፈተናዎች ውስጥ ይመራል፣ ፍርሃትን ወደ እምነት እና አደጋን ወደ መንፈሳዊ እድገት ይለውጣል። እግዚአብሔር ስደትን ወደ መመለስ፣ መከራን ወደ ቅድስና፣ ምድረ በዳንም ወደ አምልኮ ቦታ ይለውጣል። እኛም እንደ ቅዱስ ዮሴፍ በመታዘዝ እንነሳ፤ ቅዱስ ስሙን “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፣ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” (ሉቃስ 1፥46-47) ብላ እመቤታችን እንዳመሰገነች እናክብረው። ፈተናዎች ቢከብቡንም እግዚአብሔር መጠጊያችን ነው። ክርስቶስ በሚኖርበት ቦታ ሁሉ ሰላም አለ፤ እናቱ በምትማልድበት ስፍራ ሁሉ ድል አለ። ምሕረቱን አጥብቀን እንያዝ፣ በመግቦቱ እንታመን፣ በማዳኑም ደስ ይበለን። እግዚአብሔር አምላካችን ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤ ለሀገራችን ሰላምን፣ ለሕዝባችን ፍቅርን አንድነትን ያድለን፡፡ የእመቤታችን አማላጅነት አይለይን፡፡ አሜን፡፡ ኅዳር 6/2018 ዓ.ም ቀሲስ ጤናው እንዳላማውየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከትየፕሮጀክት ማናጀር
“ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ውሰድ” (ማቴ 2:13፣ 19-20) Read More »
ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ‼️ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያና ወንጌላዊ እንዲሁም ሰማዕት ነው፡፡ ከዚህም ጋር የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን መሥራች አባት ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ኢየሩሳሌም ውስጥ ክርስቲያኖች በቤቷ ለጸሎትና ለትምህርት ይሰበሰቡ የነበረችው የማርያም ልጅ ሲሆን አባቱ አርስጦሎስ አጎቱ በርናባስ ነበሩ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ሁል ጊዜ በእናቱ ቤት እየተሰበሰቡ ጸሎት በማድረግ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑ ነበር፡፡ « ማርቆስ በተባለ ዮሐንስ ቤት ሐዋርያት ይጸልዩ ነበር፡፡ »(የሐዋ 12፡12) እናቱ ማርያም እጅግ የከበረች ባለጸጋ እንደነበረችም በመጸሐፈ ስንክሳር ተገልጿል፡፡ቅዱስ ማርቆስ በትውልዱ ዕብራዊ ሲሆን ቤተሰቦቹ ግን ይኖሩ የነበሩት ሲረኒካ በተባለችውና በዛሬዋ ሊቢያ ምዕራባዊ ጠረፍ በተቆረቆረችው ከተማ ነበር። ነገር ግን የሰሜን አፍሪቃ ዘላን ጎሳዎች በየጊዜው በከተማው ጥቃት እየሰነዘሩ ቤተሰቦቹን አላስቀምጥ ስላሏቸው ወደ ትውልድ ሀገራችው ኢየሩሳሌም በመመለስ ቤት ሰርተው ተቀመጡ።ቅዱስ ማርቆስ በመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራ ነበር እናቱም ልጇን ማርቆስን የዕብራይስጥና የዮናናውያን ቋንቋ አስተምራው ነበር ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በወጣትነት ዘመኑ የጌታን ትምህርት ሰምቶ ልቡ ስለተነካ ሁሉን ነገር ትቶ የክርስቶስን ወንጌለ መንግስት ሰማያት ለመስበክ ቆርጦ ተነሳ ጌታ ካረገ በኋላ ቅዱስ ማርቆስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመሆን ወንጌልን በማስተማሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ልጄ እያለ ይጠራዋል፡፡(1ኛ ጴጥ 5፡12) ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ ታላቅ ወንጌላዊ ተጋድሎ ሲመሰክር እንዲህ ብሏል ፡- « ወአንተሰ ትልወኒ በትምህርትየ ወበግዕዝከ ዘመሀርኩከ አስተፋጥን ትሬሲ ርእስከ ኅሩየ ለእግዚአበሔር ማርቆስ ክቡር ወንጌላዊ ዐቃቢሁ አንተ ለልዑል ድርገተ ኮንከ እንተ ላዕለ ኀይል ብእሴ እግዚአብሔር አንተ ግን በትምህርቴና በጠባይህ ተከተለኝ ያስተማርኩህን አፋጥን ለእግዚአብሔር ራስህን የተመረጥክ ታደርጋለህ ክቡር ወንጌላዊ ሆይ አንተ የልዑል ጠባቂ (አገልጋይ) ነህ የእግዚአብሔር ሰው ማርቆስ ሆይ በኀይል ላይ አንድነትን የያዝክ ሆንከ » በማለት መስክሮለታል፡፡ማርቆስ ማለት ንህብ ማለት ነው፡፡ ንህብ ሁሉን እንደሚቀስም እሱም ቀድሞ ከክርስቶስ ኋላ ከሐዋርያት ተምሯልና፡፡ አንድም ልዑክ ማለት ነው፡፡ ለስብከተ ወነንጌል ይፋጠናልና፡፡ ማርቆስ አንበሳ ማለት ነው፡፡ አንበሳ ለላም ጌታው ነው ይሰብረዋል እሱም በግብጽ አምልኮተ ጣዖትን አጥፍቷልና፡፡ሐዋርያት ይህን ዓለም ዕጣ በጣ ብለው ተካፍለው ለማስተማር በሚወጡበት ጊዜ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሮም በዕጣ ደርሳዋለች በተደራቢነትም ግብጽም ደርሳዋለች፡፡ ለአርእድት ግን ዕጣ የላቸውም አንዱም ሁለቱም እየሆኑ አንዱን ሐዋርያ አንዱም ሁለቱም አንዱን ሐዋርያ ተከትለው ሄዷል ግብጽን ለማርቆስ ሰጥቶት እሱም ሮም ወርዷል፡፡ማርቆም ከዚህ ገብቶ ጌታ ከጽንስ ጀምሮ ያደረገውን ታምራት ያስተማረውን ትምህርት የሠራውን ትሩፋት ቢነግራቸው ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመለሱ አመኑ ተጠመቁ፡፡“ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር ጎበዛዝቱም ያዙት እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።” (የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 14፡51) በአራቱ ወንጌል ላይ ስለ ቅዱስ ማርቆስ የተነገረው ቃል ይህ እንደሆነ በብዙዎች ሊቃውንት ዘንድ ይታመናል፡፡ቅዱስ ማርቆስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀመዝሙር እንደነበረ በኋላም ከአጎቱ ከበርናባስ ጋር እንዳገለገለ ቅዱሳት መጽሐፍት ይመሰክራሉ፡፡ ” በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤” (የሐዋርያት ሥራ 15:37)ቅዱስ ማርቆስ በአንጾኪያ በርናባስን እያገለገለ አስተምሯል፡፡ (የሐዋርያት ሥራ 12:25) በርናባስ ካረፈ በኋላ ወደ ሮሜ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘንድ ሄዶ ለእርሱ ደቀመዝሙር ሆነ፡፡ ጴጥሮስ የተረጎመለትን ወንጌል በሮሜ አስተመምሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከፍጹምነት መብቃቱን አውቆ ጵጵስና ሾሞ ከሀገረ ስብከቱ ግብጽን ከፍሎ አስተምር ብሎ ሰጥቶታል ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ታሪኩን በዜማ ሲገልጠው እንዲህ ብሏል ፡-« ወረደ ጴጥሮስ ሐቂፎ መንበሮ ለቅዱስ ማርቆስ ወይቤሎ አባ አባ ባርከኒ ብእሲ ወንጌላዊ ዘኩልነ አብ ውስተ ኩሉ ግብፅ አድሚያሃ በስብከትከ ወንጌላዊ ፡፡» ጵጥሮስ የቅዱስ ማርቆስን ዙፋን አቅፎ ወረደ አባት ሆይ የሁላችን ወንጌላዊ ሰው ባርከኝ በስብከትህ በግብፅ በአውራጃዋ ሁሉ ላይ አሰማሁ፡፡ቅዱስ ማርቆስ በስሙ የሚጠራ ወንጌል ጽፏል ቁጥሩም ከ72ቱ አርዕድት ነው፡፡ ወንጌል የሰበከውም በሰማዕትነት ያለፈው በግብፅ ነው፡፡ ክርስትናን በግብፅ የሰበከ ብዙ ተጋድሎ ያደረገ ድንቅ አባት ነው። ቅዱስ ማርቆስም በቤቱ የጌታን ትምህርት ሰምቶ ልቡ ስለተነካ ሁሉንም ነገር ትቶ የክርስቶስን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት ለመስበክ ቆርጦ ተነሳ፡፡ በተጨማሪም የአባቱን እህት ቅዱስ ጴጥሮስ ስላገባት ከእርሱ ጋር በቀላሉ ለመተዋወቅ ችሏል። ጌታ ካረገ በኋላ ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ ተከፋፍለው ሲወጡ ከሐዋርያው ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር በመጀመሪያው ጉዞ በ46 ዓ.ም ለስብከተ ወንጌል ወጥቶ ነበር። ነገር ግን እናቴ ናፈቀችኝ ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ከዚያም ከሐዋርያው ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር መኖር ጀመረ። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በመሆን በታናሿ እስያ አድርገው እስከ ሮም ድረስ ወንጌልን አስተምረዋል።
በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ እንደተከበረ ከዚህ በፊት በነበረ ዘገባ መግለጻችን ይታወቃል። በመርሃግብሩ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በኦርቶዶክሳውያን ላይ በተደረገው ጥቃት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መመሪያ ሰጪነት እግዚአብሔር አምላክ የሞቱትን ነፍስ እንዲምርና በሀገሪቱ ላይ የመጣውን መቅሰፍት በምሕረቱ እንዲመልስ ጸሎተ ምሕላ ተደርጓል። በተጨማሪም ብፁዕነታቸው በአከባቢው የሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት የአከባቢውን ሰላም ማስከበር ቀዳሚ ተግባራቸው እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸዋል።
በአርሲ ለተገደሉ ምዕመናን ጸሎተ ምሕላ ተደረገ!! Read More »
እንኳን ለመድኃኔዓለም ጥንተ ስቅለት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ! Your Attractive Heading Your Attractive Heading የዛሬው በዓላችንን የምናከብርበት ምክንያት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጠው አንድያ ልጁን ወደ ምድር ልኮ በተቀበላቸው ጸዋትወ መከራን በማሰብ ነው። የመጨረሻ ፍቅሩንም ያሳየው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቶ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን መከራን ተቀበለ? እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከመፍጠሩ በፊት ለሰው የሚያስፈልገውን እንዳይቸገር ሁሉን አመቻችቶ (አዘጋጅቶ) በስድስተኛው ቀን ዐርብ ዕለት በእርሱ መልክና አርአያ ፈጠረው በምድርም ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ገዢ አድርጎ ከጎኑም አጥንትን ወስዶ ሔዋንን ፈጠረለት። አዳምና ሔዋን በገነት መካከል ያሉትን ፍሬዎች እንዲበሉ ፈቀደላቸው ነገር ግን ዕፀ በለስ የተባለችውን ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው ከዚህች ፍሬ ብትበሉ የሞት ሞትን እንደሚሞቱ አስጠነቀቃቸው። አዳምና ሔዋን ግን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አክብረው መኖር የቻሉት ለሰባት ዓመታት ብቻ ነበር ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ ገላ አድሮ ወደሔዋን በመሄድ ከንቱ የሆነ ውዳሴን ለሔዋን በማቅረብ “ዕፀ በለሱን አትብሉ ያላችሁ እግዚአብሔር አምላክ እንዳትሆኑ ብሎ ነው ስለዚህ ከዕፀ በለሱ ብትበሉ አምላክ ትሆናላችሁ” ብሎ ሔዋንን ዕፀ በለሱን እንድትበላ የሐሰት ስብከትን ሰበካት ሔዋንም ቀጥፋ የዲያብሎስን ምክር ሰምታ ከአዳም ጋር በሉ። በበሉም ጊዜ ጸጋቸው ተገፈፈ ፍርሃትም ወደቀባቸው እግዚአብሔርም ከእነርሱ ተለየአዳምና ሔዋንም በእግረ አጋንት በኃጢአት ወድቀው ከክብር ተዋርደው በለስን በልተው ሞትን ሸምተው ለብዙ ዘመናት በጨለማ፣በፍርሃት፣የብርሃን ጸጋቸው ተገፎ በሐዘን ውስጥ ስንሰቃዩ እግዚአብሔርም ተመልክቶ ተገለጠላቸውና አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው ብሎ ቃል ኪዳን ለአዳም ገባለት።በዚህም ጌታችን ሞታችንን ወስዶ ሕይወት ሊሰጠን መድኃኒት ልጁን ላከልን። “ፈነወ ለነ መዝራእቶ ልዑለ – ልዑል ክንዱን ሰደደልን” እንዳለ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬምበተጨማሪም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደላከው እንመሰክራለን” 1ኛ ዮሐ 4፥14 በዚሁ መሠረት ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወረደ ተወለደ ይኸውም ለአዳም ልጆች በሙሉ ለበደልነው፣ ለወንጀለኞች፣ ሕጉን ለጣስነው፣ በጨለማ ውስጥ ላለነው ፣ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲዖል እንድንወርድ ተፈርዶብን ለነበረው ፣ በእግረ ዲያብሎስ ስንረገጥ ለነበርነው እና ምንም የሚወደድ ማንነት የሌለን ስንሆን “እግዚአብሔር አንዲያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዮሐ 3፥16 ለኛ ሲል ምን ምን መከራን ተቀበለ? “የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምን አንደበት ነው? የፍቁር የጌታ ሕማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያያል ሕሊናም ይመታል ነፍስም ትንቀጠቀጣለች ሥጋም ይደክማል” 1ኛ ከሊቶስትራ እስከ ቀራንዮ ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ቀያፋ ጊቢ በአይሁድ በሊቃነ ካሕናት እጅ ተሰቃየ፣ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ጊዜ በጅራፍ ተገረፈ፣ አንድ መቶ ሃያ ጊዜ በጥፊ ተመታ፣ ሰማንያ ጊዜ ጺሙን ነጩት፣ ሰባ ሁለት ጊዜ አፉን በጡጫ መቱት፣ ሦስት መቶ የሚሆኑ ረዣዥም የእሾህ አክሊል በራሱ ደፉበት፣ ምራቅ ተፉበት፣ መስቀል ተሸክሞ እየወደቀ እየተነሳ ተሰቃየ።“እርሱ ግን ስለመተላለፋችን ቆሰለ ስለበደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።” ኢሳ 53 ፥7 እንዲሁም ጌታችን ስድስት ሰዓት ሲሆን አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ የበሉት በዚህ ሰዓት ነበረና ይህንን ለመካስ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ። ጌታችን በመስቀል እያለ ተአምራት ተፈጽመዋል በሰማይና በምድር 1ኛ ጸሐይ ጨለመ2ኛ ጨረቃ ደም ለበሰች3ኛ ከዋክብት ረገፉ # በምድር1ኛ መቃብራት ተከፍተው ከ500 በላይ የሚሆኑ ሙታን ተነሱ2ኛ ድንጋዮች ተሰነጣጠቁ3ኛ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለ2 ተከፈለ4ኛ ዓለም ሁሉ ጨለማ ሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እያለ 13ቱን ህማማተ መስቀል ተቀብሏል። ጌታችን በመስቀል ላይ እያለ “ተጠማሁ “ሲል አንጀት የሚበጥስ ሀሞትና ከርቤ ቀላቅለው አጠጡት ሁሉን የሚያጠግበውን አጠጥቶ የሚያረካውን ተጠማሁ አለ። 40 ቀንና 40ሌሊት በጌቴሴማኒ የጾመ ጌታ በአይሁድ እጅ 18 ሰዓታት ሳይሞላ ተጠማሁ ያላቸው ለምን ይሆን? ፍቅርን ሲገልጽ ነው አይሁድ ከታላቁ እስከ ታናሹ ድረስ በጠላትነት ተነስተውበታልና ለዚህም ነው ተጠማሁ ፍቅር ተራብኩ ሲል ነው። ይህን ፍቅር የሆነውን ጌታ እስከመስቀሉ ያልተለዩ ሁለቱ ብቻ ነበሩ 1ኛ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የሚደርስበትን መከራ እስከ ቀራንዮ እየተከተለ መከራውን ፣ስቃዩን፣ መንገላታቱን ግርፋቱን አይሁድን ሳይፈራ ያይ ነበር ወንጌላዊው ቅ/ዮሐንስ ጌታ ይወደው የተባለው ቁጽረ ገጽ (ፊቱ በሐዘን) የሞላ የተባለው ለዚህም ነው በመጨረሻም በመስቀል እያለ እናቱን እነኋት እናትህ ብሎ በአደራነት የሰጠው2ኛ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት እርሷም የአይሁድን ዛቻ ዱላ ሳትፈራ እስከ ቀራንዮ የተከተለች በውስጧ እያለቀሰች ያ ሁሉ ስቃይ ሲደርስበት መጨረሻውን ሳላይ የትም አልሄድም ብላ መስቀሉ ስር የተገኘች ለመዳናችን ምክንያት የሆነች ንጽሕት፣ቅድስት፣ድንግል ለሁላችን የተሰጠች እናት ናት። ስለዚህ የተከፈለልንን ውለታ በማሰብ በሕይወት ልንኖር ይገባል። 1ኛ በፍቅር ልንመላለስ ይገባል። እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት ዮሐ 15፥12ጠላቶቹ ሳለን ከወደደን 1ኛ 4፥16 እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል እግዚአብሔር ፍቅር ነው በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።2ኛ በትህትና ሕይወት ልንኖር ይገባልእርሱን ሲንቁት አልናቃቸውም ሲታበዩበት በትህትና ያያቸው ነበር። ሉቃ 23፥34 አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለእኛም ሰዎች ሲንቁን ሲታበዩብን በዝምታ በፍቅር ልናሳልፍ ይገባል። 3ኛ በትዕግስት ፦ እርሱ ሲሰድቡት አልተሳደበም፣ በፈጠራቸው ፍጥረታት ምራቅ ተተፋበት ምንም መልስ አይሰጣቸውም ነበር በትዕግስት ይመለከታቸው ነበር እንጂ 2ጴጥ 3፥15 የጌታችንም ትዕግስት መዳናችሁ እንደሆነ ቁጠሩ4ኛ ሮሜ6፥5 ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን ጌታችን ከቤተልሔም ጀምሮ ብርዱ፣ የግብጽ ስደቱ፣ረሃቡ ጥማቱ ከሐሙስ ማታ 3፡00 እስከ ዐርብ 9፡00 የተቀበላቸው መከራዎች ለሰው ልጅ ነውእኛም የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ስንሆን የሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራ አለ ነገር ግን የኛ አምላክ በመስቀል ተሰቅሎ በአዲስ መቃብር ተቀብሮ መቃብር ሊይዘው ሳይችል መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በራሱ ኃይልና ሥልጣን ሞትን ድል አድርጎ አሸንፎ ተነስቷል እኛም በእምነት ጸንተን ንስሐ ገብተን በመስቀል ላይ የቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መንግስቱን እንድንወርስ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም እንድንኖር አምላካችን ይርዳን። ስብሐት ለእግዚአብሔር! መምህር በየነ ክፍሌየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከትቁጥጥርና የምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ
“ሰፍሐ እደዊሁ ለሕማም – እጆቹን ለሕማም ዘረጋ” ቅዳሴ ሐዋርያት Read More »
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት የሒሳብ ክፍል ባለው ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟላ ሠራተኛ አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል።
ክፍት የሥራ መደብ ማስታወቂያ Read More »
ሉቃስ ማለት በላቲኑ ትርጓሜ ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ ማለት ነው፡፡ በትርጓሜ ወንጌል የተሰጠው ትርጉም ደግሞ ሉቃስ ማለት ዓቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት) ማለት ነው፣ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ነበር በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ ( መንፈሳዊ ሐኪም) ሆኗልና፡፡ አንድም ተንሣኢ (ፈጣን) ማለት ነው ለስብከተ ወንጌል ይፋጠናልና፣ አንድም መበሥር (ብሥራት ነጋሪ) ማለት ነው ብሥራተ መልአክን ይጽፋልና በማለት ይተረጉመዋል፡፡የተወለደው በሶርያ አንጾኪያ ነው፡፡አስቀድሞ ከ72ቱ አርድእት ወገን የተቆጠረ ሲሆን ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወርዶ ወንጌልን ሰብኳል ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎሰ ጋር የተገናኘውም በዚሁ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የሕክምና ሙያ የነበረው ሲሆን ያጠናውም ከአቴናና እስክንድርያ ሊቃውንት መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ሙያው በተጨማሪ የሥነ ሥዕል ችሎታም እንደነበረው ይነገራል፡፡ ይህንን ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ባለው ሥዕላዊ አገላለጥ ከማንጸባረቁም ሌላ በእጁ የተሳሉ ሥዕሎች በተለያዩ ሀገሮች ይገኛሉ፡፡የቅዱስ ሉቃስ ስዕሎች እመቤታችን ልጇን አቅፋ ( ምስለ ፍቁር ወልዳ) የሳላቸው ሲሆኑ በኢትዮጵያ በተድባበ ማርያም ፤ በደብረ ዘመዶ ፤ በዋሸራ ፤በጅበላ ሲገኙ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል ፡፡ የቅዱስ ሉቃስ ወንጌልየቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡፪. ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ የሚባለው ስለ መንፈስ ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልጿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከጌታችን ኢየሱስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡ የሐዋርያት ሥራየሐዋርያት ሥራን የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ከ1-34 ዓ.ም. ያለውን የክርስትና ታሪክ ካሰፈረ በኋላ ቀጣዩንና ከ34-58 ዓ.ም. ያለውን ደግሞ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ጽፏል፡፡ከምዕራፍ 1-8 ያለው የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በኢየሩሳሌም የሚያሳይ ሲሆን ከምዕራፍ 9-12 ያለው ታሪክ ደግሞ በእስጢፋኖስ ሰማኝትነት በተነሣው ስደት የተበተኑት የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ልጆች በአካባቢው ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡ ከምዕራፍ 13 ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ደግሞ የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞዎች ተከትሎ የጻፈውና ክርስተና በታናሿ እኪያር በአውሮፓ እንዴት እንደተሰበከ የሚያሳየው ክፍል ነው፡፡የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያው የሮም እሥራቱ በቁም እሥር ላይ ሆኖ ወንጌልን እንዲሰብክ ተፈቅዶለት በነበረ ሰዓት በሮም ከሚኖሩ አይሁድ ጋር በ58 ዓ.ም ስለሃይማኖት ያደረገውን ውይይት ተርኮ ያጠናቅቃል፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን የጻፈው በ58/በ59 ዓ.ም/ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ዓመተ ምሕረት በኋላ የተከናወኑትን ለምሳሌ በ60 ዓ.ም የቅዱስ ጳውሎስን መፈታት ዘግይቶም በ64 ዓ.ም. የደረሰውን የሮማ መቃጠልና የአይሁድን ዓመፅ በመጽሐፉ ስላልገለጠው ነው፡፡ቅዱስ ሉቃሰ ሐዋርያው ጳውሎስን ተከትሎ ታሪኩን ሲያሰባስብ ከኖረ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ ሲታሠር ዕረፍት በማግኘቱ አጠናቅሮ በመጽሐፍ መልክ በማዘጋጀት ለቴዎፍሎስ ልኮለታል፡፡ሉቃሰ ዘላሕም፡- አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቅዱስ ሉቃስ ለምን በላም እንሚመሰል ሲናገር፣ የመድኃኒታችንን መሥዋዕትነት ሐዲስዋ እምቦሳ በወለደች በንጹሕ ላም ፍሪዳ መስሎ ይናገራልና ይለዋል፡፡ እንዲሁም በከብቶች በረት መወለዱን ስለሚናገርና ታረኩም የላም ወተት ለሕፃን ልጅ ቀላል ምግብ እንደሆነ ሁሉ ለአዲሰ አማኝ ቀለል በሎ የቀረበ መሆኑን ያስገነዝባል ።ቅዱስ ሉቃሰ የድንግልና ሕይወት የነበረው ወንጌላዊ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሰማዕትነት እስካረፈበት ጊዜ ድረስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሎታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ67 ዓ.ም. በሮማ በሰማዕትነት ሲያርፍ ሉቃስ ወደ ድልማጥያ መጣ በዚያም በሽምግልና ዘመኑ ወንጌልን በመስበክ ላይ እያለ አይሁድና ካህናተ ጣዖት ተባብረው ትምህርቱን በመቃወም ተነሡበት መስከረም 20 ቀን 68 ዓ.ም. አይሁድና አረማውያን ጉባዔ አድርገው ነገር በመሥራት ለሮም ንጉሥ ከሰሱት፡፡ በዚያን ዘመን ኔሮን እብደቱ ያየለበት ጊዜ በመሆኑ የቅዱስ ሉቃስን ከሮሜ ማምለጥና ወደ ድልማጥያ መምጣት ሲሰማ 200 ወታደሮችን ላከበት ቅዱስ ሉቃስም የሰዎችን መምጣት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ያሰተምራቸው የነበሩትን ምእመናን ወደየቤታቸው ላከና በድልማጥያ አጠገብ ወደሚገኘው ባሕር ተጠጋ በባሕሩ አጠገብ አንድ ዓሣ አስጋሪ ቆሟል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዓሣ አስጋሪው ቀረበና ጨዋታ ጀመሩ ቀስ በቀስም ወንጌል ይሰብክለት ጀመር፡፡ ዓሣ አስጋሪውም ቅዱስ ሉቃሰ የሚነግረውን ሁሉ ሥራውን አቁሞ በደስታ ያዳምጠው ነበር በመጨረሻ እንካ እነዚህ የሕይወትን መገንድ ይመሩሃል አለና የያዛቸውን መጻሕፍት ሁሉ ሰጠው ያም ዓሣ አስጋሪ እጅግ ተደስቶ ዕቃ በሚያስቀምጥበት ቦታ በክብር አኖራቸው ቅዱስ ሉቃስ መጽሐፉን ሰጥቶት ዘወር ሲል የኔሮን ወታደሮች ተረባረቡና ያዙት ከዚያም ወደሮም ተወሰደና የኔሮን ፍርድ ቤት ቀረበ ።ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡ የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን! መልአከ ብርሃን ዳንኤል ነቢዩበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ፣ የዳግማዊት ጌቴሴማኒ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ
“የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ…ወንጌላዊ ።”ቆላስይስ 4፥14 Read More »