በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Public Relation

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት በመጽሐፍ መምህርነት መደብ ሠራተኛ ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት የተመዘገባችሁ የሥራ ልምድና የድጋፍ ደብዳቤ በመያዝ ሰኞ ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም ከረዳዱ 5:00 ሰዓት በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ለፈተና እንድትገኙ እየገለጽን በማስታወቂያው የተገለጸውን መሥፈርት የማያሟላ ተመዝጋቢ ለፈተና የማይቀመጥ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን።

ኤክቱስ ታኅሣሥ 1/2018 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት በመጽሐፍ መምህርነት መደብ ሠራተኛ ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት የተመዘገባችሁ የሥራ ልምድና የድጋፍ ደብዳቤ በመያዝ ሰኞ ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም ከረዳዱ 5:00 ሰዓት በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ለፈተና እንድትገኙ እየገለጽን በማስታወቂያው የተገለጸውን መሥፈርት የማያሟላ ተመዝጋቢ ለፈተና የማይቀመጥ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን። Read More »

በሀገረ ስብከቱ የተለያዩ የግብርና ፕሮጀክቶችን መሥራት የሚስችል ጉብኝትና ውይይት ተደረገ!!

ኤክቱስ ኅዳር 2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ አስተባባሪነት ከ”ICIPE (INTERNATIONAL CENTRE OF INSECT PHYSIOLOGY AND ECOLOGY)” ከተባለ በንብ ማነብ፣ በሐር ትል፣ እና በታዳሽ ኃይል ዙርያ ከሚሰራ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር ሊሠሩ በታሰቡ የግብርና ፕሮጀክቶች ዙርያ ውይይት እና ፕሮጀክቱ በሚሠራባቸው ቦታዎች ጉብኝት ተደርጓል። ጉብኝቱ መነሻውን ያደረገው በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ በአንዲዳ መድኃኔዓለም የሚገኘው የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት፣ የዳማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እና በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ እየተሠራ በሚገኘው የዶሮ እርባታ ሥፍራ፣ የንብ ማነብ ሥራ እንዲሁም የሚሠሩ በርካታ የግብርና ሥራዎች ጉብኝትና ወደፊት በሚሠሩ ሥራዎች ዙርያ ጥናት ተደርጓል። ጉብኝቱ የድርጅቱ ሠራተኞች ከሆኑት ከዶክተር ወርቅነህ አያሌው እና አቶ ልዑል ሰገድ በላይይሁን እንዲሁም ከደቡብ አስተባባሪ ዲያቆን አሳሳኸኝ ጋር ተደርጓል። በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጽሕፈት ቤት ስለአጠቃላይ ሥራዎችና ወደፊት በምን አይነት መንገድ በጋራ መሥራት እንደሚቻል ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በዕለቱ በአራቱም ቦታዎች የነበረው ጉብኝት እንዲሁም ወደፊት ሊሠሩ ስለታሰቡ ሥራዎች የተደረገው ውይይት ውጤታማ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ከዚህም በኋላ ሀገረ ስብከቱ ከድርጅቱ ጋር በጋራ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው እንዲሁም ይህንን ሥራ በጋራ ለመሥራት ለመጡት ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበው በጸሎት ፈጽመዋል።

በሀገረ ስብከቱ የተለያዩ የግብርና ፕሮጀክቶችን መሥራት የሚስችል ጉብኝትና ውይይት ተደረገ!! Read More »

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በቀን 26/02/2018 ዓ.ም በወጣው የሒሳብ ባለሙያ ክፍት የሥራ መደብ አመልካቾችን ለመቀበል ማስታወቂያ ማውጣታችን ይታወቃል። በዚሁ መሠረት መስፈርቱን አሟልታችሁ ለውድድር የቀረባችሁ አመልካቾች ጠቅላላ ውጤት ከዚህ በታች በሰንጠረዥ ባስቀመጥነው ውጤታችሁን ለመግለጽ እንወዳለን።

ኤክቱስ ኅዳር 24/2018 ዓ.ም

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በቀን 26/02/2018 ዓ.ም በወጣው የሒሳብ ባለሙያ ክፍት የሥራ መደብ አመልካቾችን ለመቀበል ማስታወቂያ ማውጣታችን ይታወቃል። በዚሁ መሠረት መስፈርቱን አሟልታችሁ ለውድድር የቀረባችሁ አመልካቾች ጠቅላላ ውጤት ከዚህ በታች በሰንጠረዥ ባስቀመጥነው ውጤታችሁን ለመግለጽ እንወዳለን። Read More »

ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ ኢሳ 6÷6

ቃሉን የተናገረው ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስ ነውየስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ ሆሴዕ፣ ኢያሱ፣ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት እንደኾነ መድኃኒት መባሉ ግን እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ 13ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ ተልእኮውን የሚገልጥ ነው እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ ሊመጣ ያለው መሲሕ ማለትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግልና ተፀንሶ፣ በድንግልና ተወልዶ፣ ቀስ በቀስ አድጎ፣ የደቂቀ አዳምን ሕማም ተሸክሞ አጠቃላይ የሰው ልጆችን በአስደናቂ መጎብኘትን ጎብኝቶ እንደሚያድናቸው ስለሚናገር “ኢሳይያስ – መድኃኒት” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡አባቱ አሞጽ እናቱ ደግሞ ሶፍያ ይባላሉ።ነቢዩ ኢሳይያስ በኢየሩሳሌም ሲኖር በአካዝና በሕዝያስ ዘመነ መንግሥት የቤተ መንግሥት አማካሪ ነበር፡፡ በራሱ መጽሐፍ እንደነገረንም በዘመኑ የነበሩ የይሁዳ ነገሥታት ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ ይባላሉ /ኢሳ.1÷1/የነቢይነትን ሥራ የዠመረውም ወዳጁ ዖዝያን በሞተ በዓመቱ ነው፡፡ ይኸውም በ740 ዓ.ዓ. አከባቢ ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ “ዖዝያንን ገስጽ” ሲባል ወዳጁ ስለኾነ ይሉኝታ ይዞት እምቢ ብሎ ነበር፡፡ ከዚኽም የተነሣ ከአፉ ላይ ለምፅ ወጣበት፡፡ ጌታም ተገልጦ፡- “የምትወደውና የምታከብረው ዖዝያን ሞተ፤ መንግሥቱም አለፈ፡፡ ሞት፣ ኅልፈት፣ በመንግሥቴም ሽረት የሌለብኝ እኔ አምላክኽ ብቻ ነኝ” አለው፡፡ ኢሳይያስ ይኽን ሲሰማ እጅግ ደነገጠ፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር፡- “ወደዚኽ ሕዝብ ማንን ልላክ?” አለው፡፡ ኢሳይያስም፡- “እኔ እሔድ ነበር፤ ግን በአፌ ለምፅ አለብኝ” ሲል መልአኩ በጉጠት አፉን ቀባውና ለምፁ ድኖለት ትንቢት ተናግሯል ። “ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ” ኢሳ 6÷6  ያለውም ለዚህ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ሃያ አራት ሊቃነ መላእክትን መርጦ በመንበረ መንግሥት ዙሪያ ክንፍ ለክንፍ አያይዞ አቁሟቸዋል፡፡ የብርሃን ዘውድ (አክሊል) ደፍቶላቸዋል፡፡ የብርሃን መስቀልና ማዕጠንተ ወርቅ አስይዟቸዋል፡፡ እንደዚህ አድርጎ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ እንዲያመሰግኑት አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህም ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ይባላሉ፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እንደምናገኘው በየዓመቱ ኅዳር 24 ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው ሰማያዊ አገልግሎት የሚሰጡ የካህናተ ሰማይ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ስለ ካህናተ ሰማይ አገልግሎት የሚያስገነዝብ አጭር ትምህርት እንማማራለን። ሱራፊ ማለት መልአክ፣ ከካህናተ ሰማይ አንዱ ማለት ነው፡፡ ሱራፌን፣ ሱራፌል፣ ሱራፌም (በፅርዕ ሴራፊም፣ በዕብራይስጥ ስራፊም) ማለት የነገድ ስም፣ ልዑላን መላእክት፣ ሊቃናት፣ የሚያጥኑ፣ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ቀዳሾች ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፰፻፹፮/፡፡ ከዚህ ላይ ሱራፊ ነጠላ ቍጥርን፤ ሱራፌል ደግሞ ብዙ ቍጥርን ያመለክታል፡፡ ሱራፌል ለቅዱሳን በሰው አምሳል በመገለጣቸው ሽማግሌዎች ተብለው ተጠርተዋል /ኢሳ.24፥23፤ መሳ.13፥2 ፤ ዳን.10፥18/፡፡ በግእዝ ቋንቋ ደግሞ ካህናተ ሰማይ ይባላሉ፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆመው የሚሰጡትን ሰማያዊ አገልግሎት የሚያመለክት ስም ነው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በዙሪያውም ሃያ ዐራት ካህናት አሉ፡፡ በፊታቸው የበጉን ሥዕል፣ ደምን የተረጨች ልብስንም፣ የታተመ መጽሐፍንም ያያሉ፡፡ መንበሩን በዞሩ ቍጥር ለዚያ ለበጉ ሥዕልና በደም ለታለለችዋ ልብስ፣ ለታተመው መጽሐፍም ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› /ራእ. 4፥6 ፤5፥8/ በማለት ስለ ሱራፌል ሰማያዊ አገልግሎት የተናገረ ሲኾን፣ ‹‹በፊታቸው የበጉን ሥዕል ያያሉ›› ማለቱ የክርስቶስን ትስብእት በጌትነት ያዩታል ለማለት ነው፡፡ ‹‹ወደቁ›› ሲልም መስገዳቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹በግ›› የተባለውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹ደምን የተረጨች ልብስ›› ማለቱም ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ መቀበሉን፤ የታተመ መጽሐፍ የክርስቶስ ትስብእት የማይመረመር መኾኑን፤ ‹‹ለበጉ ሥዕል፣ ለታለለችው ልብስና ለታለለው መጽሐፍ ሦስት ጊዜ ይሰግዳሉ›› ሲልም ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነትም በሦስትነትም ለሚመለከው ለክርስቶስ ደግመው ደጋግመው ምስጋና ማቅረባቸውንና መገዛታቸውን ያመለክታል /የሠለስቱ ምእት ቅዳሴ አንድምታ ትርጓሜ፣ 3፥7-9/፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤልም ካህናተ ሰማይ ያለ ዘር መገኘታቸውን ሲያመለክት ‹‹በመንበሩ ዙሪያ ቁመው ያሉ ካህናት ኅብራቸው መረግድ የሚባል ዕንቍን ይመስላል›› በማለት ተናግሯል፡፡ ጸጋቸውን ሲገልጽ ደግሞ ‹‹ብሩህ ልብስ ለብሰዋል፤›› ክብራቸውን ሲመሰክርም ‹‹በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተዋል›› ብሏል፡፡ ነጭ ልብስ ለብሰው መታየታቸው የንጽሕናቸውና የቅድስናቸው መገለጫ ሲኾን፣ በራሳቸው ላይ የተቀዳጁት ዘውድ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ዘለዓለማዊ ክብር ያሳያል፡፡ ቍጥራቸው በሃያ አራት መገለጹም ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ኾኗቸው ለሃያ አራት ሰዓታት ሳያቋርጡ ጸሎትና ምስጋናን ለእግዚአብሔር ማቅረባቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡ ካህናተ ሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ሲያቀርቡ አክሊሎቻቸውን ከራሳቸው ላይ አውርደው ያለማቋረጥ ይሰግዳሉ፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ይህንን ሰማያዊ ሥርዓት እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤ ‹‹ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ፤ ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) በመንበሩ ዙሪያ ቆመው በፊቱ ሲሰግዱ የመለኮት እሳት ሲበርቅ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ፤›› /መጽሐፈ ሰዓታት/፡፡ ይህም ምስጋና በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ የጸሎት ክፍሎች ይገኛል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ አለ ፤ ቅዱሳን መላእክት  ለመራዳት፣ ለመጠበቅ፣ ለመታደግ ፣ ከተፍገመገምንበት ለማንሳት ፈጥነው ደራሽ መሆናቸውን ሲነግረን ነው ። እለ ስድስቱ ክነፊሆሙ ይላቸዋል ። ልዑል እግዚአብሔር የሰጣቸው ፀጋ ብዙ መሆኑን ሲያሰረዳን ነው ።በእውነት ከሱራፌል አንዱ እየበረረ መጥቶ በጦርነት ለምጽ የተመታችውን ሀገራችነን ይፈውስልን ። የ24ቱ ከህናተ ሰማይ በረከታቸው ረድኤታቸው ይደርብን ይዋልብን ። መልአከ ሰላም አምሳሉ ሳለየዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪኅዳር 24/2018 ዓ.ም

ከሱራፌል አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ ኢሳ 6÷6 Read More »

ታላቅ መንፈሳዊ በዓለ ንግሥና መንፈሳዊ ጉባኤ በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር በሚገኘው በዲላ ዳግማዊት ጌቴሴማኒ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ከታህሳስ 2 እስከ 5 ድረስ ስለተዘጋጀ ሁላችሁም እንድትገኙ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጥሪዋን ታስተላልፋለች።

ኤክቱስ ኅዳር 22/2018 ዓ.ም

ታላቅ መንፈሳዊ በዓለ ንግሥና መንፈሳዊ ጉባኤ በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር በሚገኘው በዲላ ዳግማዊት ጌቴሴማኒ በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ከታህሳስ 2 እስከ 5 ድረስ ስለተዘጋጀ ሁላችሁም እንድትገኙ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ጥሪዋን ታስተላልፋለች። Read More »

ሀገረ ስብከቱ የሚስገነባው መንበረ ጵጵስና ተጎበኘ!!

ኤክቱስ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት አዲስ የሚያስገነባውን መንበረ ጵጵስና ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ከፍተኛ አመራሮችና የዲላ ማዕከል ሥራ አስፈጻሚዎች ጎብኝተዋል። የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አስፈጻሚ የሆኑት መምህር ዋስይሁን በተመለከቱት ነገር ከመደሰታቸው በተጨማሪ “ሀገረ ስብከቱ ለብዙዎች አርአያ የሚሆን ነው” ያሉ ሲሆን በብፁዕነታቸው መደነቃቸውን ገልጸዋል።

ሀገረ ስብከቱ የሚስገነባው መንበረ ጵጵስና ተጎበኘ!! Read More »

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ተወያየ!!

ኤክቱስ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ከፍተኛ አመራሮችና ከዲላ ማዕከል ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት አድርጓል። ውይይቱ ትኩረቱን ያደረገው ሀገረ ስብከቱ ከማኅበሩ ጋር በጋራ ለመሥራት በተፈራረመው ውል ላይ ሲሆን በቀጣይ ከማኅበሩ ጋር በጋራ ለመሥራት ባሰባቸው ሥራዎች ላይ ግልጽ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መምህር ዋስይሁን፣ የማኅበሩ ደቡብ ማስተባበርያ ኃላፊ ቀሲስ አሰፋ ቦረና፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከልና ዲላ ማዕከል ሥራ አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል።

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ተወያየ!! Read More »

የአብነት ትምህርት ቤት ለመሥራት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ!!

ኤክቱስ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በአንዲዳ መድኃኔዓለም ለሚያስገነባው የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጸሎትና ቡራኬ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል። ዝማሬ፣ ትምህርተ ወንጌልና በደቀመዛሙርት ቅኔ ቀርቧል። የአንዲዳ መድኃኔዓለም የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ሁለት የመጻሕፍት ደቀ መዛሙርት ቅኔ ቀርቧል። መምህር ዋስይሁን በላይ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ኃላፊነት መሠረት የማኅበሩን አባላትና መላው ምዕመናንን በማስተባበር ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች በሁለንተናዊ አገልግሎት ራሳቸውን እንዲችሉና ተተኪ ሊቃውንትን እንዲያፈሩ 1991 ዓ.ም ጀምሮ ከአንድ መቶ ሰባ በላይ የገቢ ማስገኛና የአገልግሎት መስጫ ፕሮጀክቶችን ሠርቶ ማስረከቡን ገልጸዋል። በተጨማሪም ማኅበሩ በ2018 ዓ.ም ለመተግበር ከያዘው ዕቅድ መካከል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማስተባበር በአንዲዳ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ለመገንባት መዘጋጀቱንና ግንባታውም 14 ወራትን እንደሚቆይ ገልጸዋል። በተጨማሪም ማኅበሩ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በጋራ መሥራት የሚስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ ጋባዥነት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን እጅግ በጣም ብዙ ገዳማትን ከመበተን ከማዳኑ በተጨማሪ በርካታ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑን ከመግለጻቸው በተጨማሪም ከማኅበሩ ጋር በርካታ ሥራዎችን በጋራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በመጨረሻም ግንባታ ለመጀመር የታሰበበት ቦታ እንዲሁም ላለፈው አንድ ዓመት የአብነት ትምህርት ቤቱ መንፈሳዊ ትምህርት ሲሰጥበት የነበረው የተማሪዎች ማደርያ፣ ጽሕፈት ቤት፣ የመማርያና የመመገቢያ ክፍሎች በተጨማሪም ወደፊት የተለያዩ ልማቶችን ለመሥራት የታሰበበት ቦታ ጉብኝት ተደርጎ የመርሃግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

የአብነት ትምህርት ቤት ለመሥራት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ!! Read More »

ሰጠቀ ባሕረ ወአኅለፎሙ (ባሕርን ከፍሎ አሻገራቸው።) መዝ ፸፷፥፲፫

ኅዳር ፲፪ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት በሙሴ መሪነት እግዚአብሔር እስራኤልን ከግበፅ ባርነት ነጻ ማውጣቱን የምናከብርበት በዓል ነው ። ይኸውም ወጡ ለማለት ወረዱ ማለት ይቅድማልና በምን ምክንያት እንደወረዱ እንመልከት።እስራኤል ማለት ሕዝበ እግዚአብሔር ማለት ሲሆን ሥርዎ ሃይማኖት በመባል የሚታወቀው የአብርሃም የልጅ ልጅ ለያዕቆብ የተሰጠ ስም ነው ። ይህ ሕዝብ በታላቁ በአባቱ በአብርሃም በኩል ዘርህን እንደ ሰማይ ኮከብ አበዛዋለሁ የተስፋይቱንም ምድር አወርሰዋለሁ ተብሎ የተነገረለት እግዚአብሔርም የማዳን ሥራውን ለመስራት ያቀደበት ቢሆንም ቅሉ ዘፍ ፲፭ ፥፭-፲፪ በተቃራኒው ደግሞ ከዚሁ ምዕራፍ ሳንወጣ ዘፍ ፲፭ ፥፲፫ ላይ ስንመለከት“ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል።ተብሎ ትዕቢት ተነግሮበት የነበረ ሕዝብ ነው። በጣም የሚገርመው ይህ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆን የተስፋይቱን ምድር (ከነዓንን) እንደሚወርስ እግዚአብሔር ወልድም ከእርሱ ተወልዶ እንደሚያድነው ተስፋ ቢኖረውም በሌላ በኩል ደግሞ ለ፬፻ ዓመት በስደት ፣በባርነት ፣ በሰቆቃና በኀዘን እንደሚኖር ተነግሮበት ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውና ይህ ትንቢት በተነገረ በ፪፻ ወ ፲፭ ዓመት እስራኤል የተባለው ያዕቆብ እርሱና ቤተሰቦቹ ፸ ሆነው ወደግብፅ መሰደዳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ለጊዜው በሀገራቸው የተከሰተውን የረሀብ ዘመን በወንድማቸው በዮሴፍ አማካኝነት በጥጋብ ቢያልፉትም በኋላ ግን በተለይም የወንድማቸው የዮሴፍን ሞት ተከትሎ የመጣባቸው መከራ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አልነበረም። (በዘጸ ፩፥፰ በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ )ተበሎ እንደተጻፈው ይህ ንጉሥ የዮሴፍን ደግነት ፣ ጥበብ ፣ ክብር እና መጋቢነት ያላወቀ፣ ልቡ በክፋት የጸና፣ አንደበቱ በበቀል የተመላ፣ የሰይጣን ግብር አስፈጻሚ ነበር ማለት ብቻ ሳይሆን እርሱም ሥጋ የለበሰ ሰይጣን ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ከዚህ ሰው ንግሥና በኋላ በእስራኤል ላይ ፅኑዕ የሆነ መከራ መጣባቸው ። በደስታቸው ላይ ኀዘን፣ በእረፍታቸው ላይ ስቃይ፣ በልተው በማደራቸው ፋንታ ረሀብ፣በክብራቸው ፋንታ ውርደት መጣባቸው በእስራኤላውያን መብዛት እረፍት ያጣው ፈርዖን ዘጸ፩፥፲ ስንመለከት (እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው፡” አለ) ይለናል። ፈርዖን እስራኤላውያንን ለማጥፋት ጥበብን ይሻ ነበር እግዚአብሔር ያበዛውን ማጥፍት ባይቻልም ፈርዖን ግን ፍላጎቱን ለማሟላት የጥፋት ጥበብን ፈለገ። ሰው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲወጣ ሀሳቡ የጥፋት፣ ጥበቡ የጥፋት፣ ግብሩ የጥፋት አመለካከቱ ሁሉ የጥፋት ይሆንበታል ። ፈርዖን ሀሳቡን እውን ለማደረግ በእስራኤላውያን ላይ በዙ ግፍ የፈጸመ ሲሆን የተወሰኑት፦ጡብ ማስጣልኖራ ማስወቀጥጭቃ ማስረገጥፈርዖን እስራኤላውያንን በእነዚህና በመሳሰሉት ስራዎች እያሰቃየ ፌቶም ፣ ራምሴና ዖን የሚባሉ ሦስት ከተሞችን በእነሱ ላብ ፣ ጉልበትና ደም አስገንብቷል ።ፈርዖን ከዕብራውያን ስዎች አንድም ሰው ለቅጽበት ስንኳ እረፍት ማግኘት እንደሌለበት ትእዛዝ ሰጥቷል ።ይህንም ያደረገው በሁለት ምክንያት ነው ፦ ፩ኛ በስራ ተጠምደው ከዋሉ የጦር ልምድ አይኖራቸውም ከጠላቶቻችንም ጋር ተባብረው አያጠፋንም ብሎ ነው ። ፪ኛ ወንዶች ጭቃ ሲረግጡ ሴቶችም ኖራ ሲወቅጡ ከዋሉ ወንዶችም ወደ ሴቶች ፣ ሴቶችም ወደ ወንዶች አይደርሱም በዚህ ምክንያት ዕብራውያን እንዳይወልዱና እንዳይበዙ ለማድረግ ነበር። እውነት ለመናገር በዕብራውያን ላይ የደረሰው ግፍ መጠን የሌለው ነው ፣ ምጥ የተያዘች እናት ስንኳ ያለእረፍት እያማጠች ጭቃ የረገጠችበት ዘመን ነው ። በዚያ ዘመን አንዲት ራሔል የምትባል ፣ውድ ባለቤቷ ሮቤልን በሞት ያጣችና መንታ የጸነሰች እናት ነበረች። በባለቤቷ ፋንታ ጭቃ እንደትረግጥ ተገደደች፣ በዚያን ሰዓት ምጥ መጣ ፣አምጣ ለመውለድ እኳን ፈቃድ ብትጠይቅ አልተፈቀደላትም ።እያማጠችም ጭቃ እየረገጠችም በነበረችበት ሰዓት ወለደች። ሆኖም ራሔል የነበረችው አልጋላይ ሳይሆን ጭቃ ላይ ስለሆነ መንተኞች ልጆቿ ከወደ ጭቃው ተቀላቀሉ ።የልጅ ፍቅር ያንገበገባት ራሔል ምጧን ረስታ ልጆቿን ለማንሳት ብትሞክሮም ከጭቃው ጋር አብራ እንድትረግጣቸው ተገደደች።የሰው ደም ግንብ ያጸናል ተብሎ ተነገረ ።ዛሬም በሀገራችን የሰው ደም ግንብ ያጸናል የተባለው የግብፅ አዋጅ የታወጀ ይመስላል ምን አልባት ፈርዖን ወደኢትዮጵያ መጥቶ ይሆን? እናም ራሔል እንባዋን ወደ ሰማይ ረጨች የራሔል እንባ የዕብራውያንን እንባ ቅድመ እግዚአብሔር አደረሰች እግዚአብሔርም ሰማቸው። ሙሴንም ከግብፅ እንዲያወጣቸው ላከላቸው ። ዕብራውያንን ነፃ ለማውጣት እግዚአብሔር ሙሴን አስነሳ።ከሚቀበሉት መከራ አንዱ የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች መገደል ነበር።በዘጸ ፩፣፲፮ እንደምናነበው ፎሀ እና ሲፓራ የተባሉ የግብፃውያን ሴቶች የዕብራውያንን ሴቶች አንዲያዋልዱ እና ወንድ ከተወለደ ደግሞ እንዲገድሉ ከፈርዖን ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነብር።በዚህ መሠረት ከእስራኤል ወንድ ልጅ ሲወለድ ይሞት ነበር ከዚህ የተረፈውም በባሕር ይጣል ነባር ። ሙሴን ግን እግዚአብሔር ጠበቀው።በንጉሡም ቤት ለ፵ ዓመት አኖረው ።እስራኤልን ይታደግ ዘንድ እግዚአብሔር መርጦታልና።በኋላም ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር ሙሴን በ፹ ዓመቱ ወደግብፅ ላከው ።ሙሴ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ተአምር ለፈርዖን ካሳየ በኋል ሕዝቤን ልቀቅ ይልሀል እግዚአብሔር አለው ።ፈርዖንም እግዚአብሔርን አላውቅም ሕዝቤንም አለቅም በማለት ልቡን በክፋት አጸናው።በፈርዖን የልቡና ክፋት ምክንያት እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ዘጠኝ መቅሰፍት አስረኛ ሞተ በኩርን አመጣባቸው።በተቃራኒው ዕብራውያንን ግን ከዚህ ሁሉ መቅሰፍት እየጠበቀ ያበዛቸው ነበር።የፈርዖን አመጽ ካመጣው መቅስፍት አንዱ የግብፅ ውሃዎች በሙሉ ደም መሆን ነበረ የግብፅ ሰዎችም ለሰባት ቀን የሚጠጡት ውሃ በማጣት አልቀዋል። በመጨረሻም ሞተ በኩር መጣ የግብፅ ምድርም ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ የበኩር የሆነውን (መጀመርያ የተወለደውን)በሞት አጣች ።ዘጸ ፲፪፣፲፪ ዕብራውያንን ግን ይህ ሁሉ እንዳያገኛቸው የአማናዊው በግ የክርስቶስ አምሳል የሆነውን የፋሲካውን በግ አርደው ስጋውን እንዲበሉ ደሙንም የቤታቸውን በር እንዲረጩት እግዚአብሔር ለሙሴ አዝዞት ስለነበር ሞተ በኩር ከበራቸው እደረሰ ተመልሷል።ከዚህ በኋላ የሚመራውን ሕዝብ በሞት ያጣ ፈርዖን ዕብራውያን የሶስት ቀን መንገድ ሄደው መስዋዕት ሰውተው እንዲመለሱ ፈቀደላቸው ።እስራኤላውያን ግን ለብዙ ዘመን የተገዙበትን ወርቅና ብር በተውሶ ምክንያት ይዘው ወጥተዋል ። ውስጡ ግን ጥበበ እግዚአብሔር ነበር ።ፈርዖን ከመከራው ጽናት የተነሳ በፈቃዱ ቢለቃቸውም ተከትሎ ማሳደዱን ግን አልተወም ነበር።እግዚአብሔርም ዕብራውያንን በሰባት ደመና እየመራ ጠበቃቸው፩ኛው ከላይ የፀሐይን ሙቀት ይከላከላል፪ኛው ከስር እንቅፋት እንዳያገኛቸው፫ኛው በቀኝ ጠላት እንዳይጎዳቸው፬ኛው በግራ ከሚመጣ ጠላት ይጠብቃል፭ኛው በኋላ ከሚመጣ፮ኛው በፊት ከሚመጣ፯ኛው የሶስት የአራት ቀን መንገድ ሲጠርግላቸው ውሎ ማታ ያበራላቸው ነበር። ፈርዖንም ተከትሏቸው ባሕረ ኤርትራ ሲደርሱ ድምጻቸውን እየሰማ ሳያገኛቸው የቀረው በደመና ስለተከበቡ ነው ።እስራኤልን በፊታቸው የኤርትራ ባሕር በኋላቸው የፈርዖን ሰራዊት ሲያስጨንቃቸው አደረ ።አይ ያች ሌሊት ምን አይነት ሌሊት ናት? እነሱ ተጨነቁ እንጅ እግዚአብሔር ግን በደመና እየጠበቃቸው ነበር።ጎህ ሲቀድ እግዚአብሔር ተአምሩን ገለጠ ሙሴን ባሕሩን በተአምረኛው በትሩ እንዲመታው አዘዘው ሙሴም የታዘዘውን አደረገ ።እግዚአብሔርም ባሕሩን ከፈለ ዕብራውያንንም በሰላም ባሕርን ከፍሎ አሻገራቸው።ፈርዖንም እንደ ዕብራውያን እሻገራለሁ መስሎት ከነሠራዊቱ ወደባሕር መግባቱ አልቀረም።እግዚአብሔር ሁሉም እስኪገቡ ጠበቃቸው ።ዕብራውያን ከባሕር ሲወጡ ግብፃውያን ወደባሕር ሲገቡ ሙሴ ለሁለተኛ ጊዜ ባሕሩን በብትሩ መታ ባሕሩም ወደቀደመ ማንነቱ ተመለሰ ።ፈርዖንም ከነሰራዊቱ ውሃ ሆኖ ቀረ። የዕብራውያንን ልጆች በውሃ ያስጣለው ፈርዖን ራሱም በውሃ ሰጠመ ።ዕብራውያን በሰላም ተሻግረው አምላካቸውን አመሰገኑ ክፋተኞች ግን በክፋታቸው ሰጠሙ ።የክፋዎች መጨረሻቸው ስጥመት ነው ።የመልካሞች ግን ባሕርን ከፍሎ መሻገር ነው።እግዚአብሔር ሆይ እኛንም ከኀጢአት ባሕር ያሻግረን ዘንድ ሙሴን ላክልን። መምህር መልአክ መሠለየአንዲዳ መድኃኔዓለም የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤትየትርጓሜ መምህር

ሰጠቀ ባሕረ ወአኅለፎሙ (ባሕርን ከፍሎ አሻገራቸው።) መዝ ፸፷፥፲፫ Read More »

Scroll to Top