ኤክቱስ ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በጪጩ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለሚከበረው ዓመታዊ የታኅሣሥ 19 የቅዱስ ገብርኤል የንግሥ በዓል እየተደረጉ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የሀገረ ስብከቱ የፕሮጀክት ማናጀር ቀሲስ ጤናው እንዳላማው፣ የጪጩ ቀበሌ የኢንዱስትሪ ቀጠና አስተዳደር አቶ ብርሃኑ፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጠበብት መሪጌታ መሰረት፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ኃይል ሀብቴ ገብረ ሕይወት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸው በጉብኝታቸው በደብሩ እየተከናወኑ ያሉ የጽዳት ሥራዎችን የተመለከቱ ሲሆን በተለይም ደብሩ ራሱን በራሱ ለመቻል እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል። በደብሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ የለሙትና የአካባቢው መገለጫ የሆኑት የቡና እና የእንሰት ተከላ ሥራዎች፣ እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን ያጠናቀቀውን የወፍጮ ቤት እንቅስቃሴ በብፁዕነታቸው ተጎብኝቷል።
በሌላ በኩል የደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለበዓሉ የሚመጡ ምዕመናን የሚጠቀሙባቸውን የጧፍ ምርቶች በስፋት በማዘጋጀት ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህም የወጣቶች በቤተክርስቲያን አገልግሎትና ልማት ላይ ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
የደብሩ አስተዳዳሪ በበኩላቸው በደብሩ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የግብርና እና የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ልማቶች ያሉበትን ደረጃ ለብፁዕነታቸው አስረድተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የተገኙት የጪጩ ቀበሌ የኢንዱስትሪ ቀጠና አስተዳደር አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው በዓሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ ሁሉ በጉጉት የሚጠብቀው ታላቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ከጸጥታና ከጽዳት አንጻር በርካታ ሥራዎች በኅብረት እየተከናወኑ መሆኑን ለብፁዕነታቸው አስረድተዋል።
ብፁዕ አቡነ ገሪማ በጉብኝታቸው ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ደብሩ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በልማትና በአካባቢ ጥበቃ ረገድ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ከአካባቢው አስተዳደርና ከነዋሪው ማኅበረሰብ ጋር ያለው ጠንካራ ትብብር ለበዓሉ ስኬታማነትና ለደብርይ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ ለዝግጅቱ ስኬት ለደከሙ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው በጸሎት ፈጽመዋል።
