የዶሮ ልማት ፕሮጀክትን አስመልክቶ የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብር ተካሄደ!
ኤክቱስ ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የተጀመረው የዶሮ ልማት ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን የደብሩ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርና የልማት ኮሚቴ አባላት ለሥራው ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብር ተካሄደ። ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብር የተካሄደው የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው። የመርሃግብሩ ዋና ዓላማ የደብሩ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደርና የልማት ኮሚቴው ለፕሮጀክቱ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉና ለሥራው መፋጠን በትጋት እንዲነሳሱ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በውይይቱ ወቅት የልማት ኮሚቴውና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት በፕሮጀክቱ አፈጻጸም፣ በሚጠበቁ ውጤቶችና ሊያጋጥሙ በሚችሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ የበኩላቸውን ገንቢ ሃሳቦችን አቅርበዋል። የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ ከብፁዕነታቸው በሚሰጣቸው አባታዊ መመሪያ መሰረት በፕሮጀክቱ ዙርያ ሰፊ ሥራ እንደተሠራ እንዲሁም ከዚህም በኋላ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ቅድመ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው የቀረቡትን ሃሳቦች መነሻ በማድረግ በሰጡት አባታዊ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንግግር፤ ቤተ ክርስቲያን ያሏትን ሀብቶች ተጠቅማ ሙዳየ ምጽዋትን ለዓላማው ማዋልና ራሷን በኢኮኖሚ መቻል እንዳለባት አስገንዝበዋል። የዶሮ ልማት ፕሮጀክቱ የደብሩን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ፣ ለሌሎች አድባራትና ገዳማት ተምሳሌት የሚሆን ሥራ መሆኑን ገልጸው፤ የሰበካ ጉባኤውና የልማት ኮሚቴው በኃላፊነት ስሜትና በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ መመሪያ ሰጥተው በጸሎት ፈጽመዋል።
የዶሮ ልማት ፕሮጀክትን አስመልክቶ የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃግብር ተካሄደ! Read More »