ኤክቱስ ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በዲላ ማረሚያ ቤት ከሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ጋር በመሆን በደመቀ ሁኔታ አክብረዋል። ይህ የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር በሀገረ ስብከቱ የምግባረ ሰናይ ኮሚቴ አስተባባሪነት ከወረዳ ቤተ ክህነቱ፣ ከማረሚያ ቤቱ ጊዜያዊ ኮሚቴ እና ከማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል የቀድሞ ዋና ግቢ ጉባኤ ጋር በመተባበር በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር የተዘጋጀ ነው።
በበዓሉ መርሃ ግብር ላይ ብፁዕነታቸውን ጨምሮ የማረሚያ ቤቱ የአስተዳደር አካላት፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና ጸሐፊ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል ሥራ አስፈጻሚዎችና የቀድሞ ዋና ግቢ ጉባኤ አባላት ተገኝተዋል።
በማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል የቀድሞ ዋና ግቢ ጉባኤ ዘማርያን ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ ግንዛቤ፤ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ተስፋ ሳይቆርጡ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ሕይወታቸውን እንዲመሩ አሳስበዋል። ብፁዕነታቸው አክለውም ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን እንድትወጣ መምህራን ገብተው መንፈሳዊ ትምህርት እንዲሰጡ ለፈቀዱት ለኢንስፔክተር ትዕግስት ሮቤና ለመላው የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ምስጋና አቅርበዋል።
ኢንስፔክተር ትዕግስት ሮቤ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታራሚዎችን በማጽናናትና በማስተማር እያደረገች ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል። በተለይም ብፁዕ አቡነ ገሪማ በቡሌና በረጴ ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ በደረሰበት ወቅት ሕዝቡን ለመርዳት ቀድመው መድረሳቸውን በማስታወስ፣ “እንዲህ ያሉ ለሕዝብ የሚደርሱ የሃይማኖት አባቶችን ያብዛልን” በማለት ምስክርነታቸውንና ምስጋናቸውን ሰጥተዋል።
በመጨረሻም በበጎ አድራጊ ምዕመናን ትብብር የተዘጋጀው የማዕድ ማጋራት ሥነ-ሥርዓት የተከናወነ ሲሆን፣ መርሃ ግብሩ በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቅቋል።
