በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የልደተ ክርስቶስን በዓል በማስመልከት የአንዲዳ አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርትን ጎበኙ!

ኤክቱስ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ በዲላ ማረሚያ ቤት የነበራቸውን የበዓል መርሃግብር ካጠናቀቁ በኋላ በቀጥታ ወደ አንዲዳ አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት በማቅናት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዓሉን አክብረዋል።

መርሃ ግብሩ በጸሎት ከተጀመረ በኋላ ብፁዕነታቸው በትምህርት ጊዜያቸው የነበራቸውን የበዓል ቆይታና ልምድ ለደቀ መዛሙርቱ አካፍለዋል።

በበዓሉ ላይ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር አካላት፣ መምህራን እና ሠራተኞች በተገኙበት ለዕለቱ የተዘጋጀው ማዕድ በጋራ ተካፍለዋል።

ከማዕድ በኋላ በተካሄደው መንፈሳዊ መርሃግብር ዝማሬዎችና በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ግጥሞች ቀርበዋል። ብፁዕነታቸውም በአማርኛ፣ በጌዴኡፋ፣ በኮሪቴ፣ በቡርጂ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ዝማሬዎችን በማቅረብ ለደቀ መዛሙርቱ ያላቸውን ቅርበት አሳይተዋል።

ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ደቀ መዛሙርቱ በትምህርት ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ርቀው በዓሉን በማክበራቸው እንዳይከፋቸውና ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም እናት ሆና ከጎናቸው መሆኗን በቃልም በተግባርም አረጋግጠዋል።

የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብም ብፁዕነታቸው በበዓሉ ዕለት ጊዜ ሰጥተው በመካከላቸው በመገኘታቸውና አባታዊ ፍቅራቸውን በመግለጻቸው ታላቅ ደስታና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Scroll to Top