ኤክቱስ ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል የንዋየ ቅድሳት እጥረት ላለባቸው አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር ለሚገኘው ለኤላ ጠነቻ ቅዱስ ዑራኤል፣ በቡሌና ረጴ ወረዳዎች ቤተ ክህነት ሥር ለሚገኘው ለላባ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኮሬ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር ለሚገኘው ለቆሬ ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት የሚውል የንዋየ ቅድሳት ድጋፍ አስረክቧል። ማዕከሉ ከበጎ አድራጊ ምዕመናን ያስተባበረው ይህ ድጋፍ በገንዘብ ሲሰላ በድምሩ 178,230 (አንድ መቶ ሰባ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ሠላሳ) ብር የሚያወጣ መሆኑ ተገልጿል።
በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምንላርግህ የትዋለ እና የማዕከሉ ሙያ፣ ገዳማት እና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ለዓለም ድብቁ ተገኝተው ድጋፉን ለሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለሆኑት ለብፁዕ አቡነ ገሪማ አስረክበዋል።
ብፁዕነታቸውም ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሳለጥ ይህንን ተግባር ለፈጸሙ ምዕመናን ጸሎትና ቡራኬ ያደረጉ ሲሆን ይህንን መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አባታዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው ከማዕከሉ ኃላፊዎች የተረከቧቸውን ንዋየ ቅድሳትና አልባሳት በአገልግሎት እጥረት ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እንዲደርስ አስረክበዋል።
በዚህም መሠረት ብፁዕነታቸው በይርጋጨፌ ወረዳ ለሚገኘው ኤላ ጠነቻ ቅዱስ ዑራኤል፣ በቡሌና ረጴ ወረዳዎች ለሚገኘው ለላባ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም በኮሬ ወረዳ ለሚገኙት ለጂጆላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ለኬሬዳ ቅድስት ሥላሴ፣ ለጉልቤ ቅድስት ማርያም እና ለጉሙሬ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት ተደራሽ እንዲሆኑ ለየወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጆችና ጸሐፊዎች ተረክበዋል።
ይህ በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት የተከናወነው ተግባር ሀገረ ስብከቱ ከዚህ ቀደም የሚተገብረው ተግባር ሲሆን በገጠር አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓተ አምልኮንና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ንዋየ ቅድሳት ችግር በተሟላ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑ ተጠቁሟል።
