#ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንኳን ለ፪ኛ ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሰላምና በጤና አደረስዎ !!
ለመላው ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን በሙሉ ለብፁዕ አባታችን አቡነ ገሪማ ጳጳስ የ፪ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በዓል እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን። በኢትዮጵያ ኦርቶዶከክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የብፁዕ አቡነ ገሪማ የ፪ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና የየክፍል ኃላፊዎች የወረዳ ቤተክህነት ኃላፊዎች እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት ይከበራል። ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሀገረ ስብከት ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ከ 70 በላይ አብያተክርስቲያናት የጎበኙ፣ አባታዊ ምክርና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሰጡና ከዚህ በፊት በጳጳሳት ያልተጎበኙና ያልተባረኩ ምዕመናን በመጎብኘታቸው ልዩ አባት ያደርጋቸዋል። ብፁዕ አቡነ ገሪማ የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት እንዲስፋፋ፣ ለሰበካ ጉባኤ አባላት ስልጠና በመስጠት አዳዲስ አማኒያንን በማጥመቅ የሀገረ ስብከቱን የ፲ ዓመት መሪ ዕቅ እንዲዘጋጅ በማድረግ ፣የመንበረ ጵጵስና መኖሪያ ግንባታ እንዲጀመር በማድረግ ፣ አዲስ የተሠሩ አብያተክርስቲያናትን ባርከው ለአገልግሎት እንዲበቁ፣በሀገረ ስብከቱ ዘመናዊ አሠራርን በመዘርጋት፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፣ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ሁሉም አብያተክርስቲያናት በይዞታቸው አቅደው ተገቢውን ልማት እንዲያለሙ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እንዲያደርግ መመሪያ በመስጠት የመጎብኘትና የማበረታታት ተግባርን አከናውነዋል። በገጠሪቱ አብያተክርስቲያናት የእግር ጉዞ በማድረግ ወንጌል ሰብከዋል። በታላላቅ በዓላት በመገኘት ቀድሶ በማቁረብ ወንጌልን በማስተማር በሀገረ ስብከቱ በሚነገሩ ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረጉ እንዲገለገልበት መመሪያን የሰጡ ፣የገጠሪቷ ቤተክርስቲያን የጎበኙ ፤ ሀገረ ስብከቱ ዘመኑን ያማከለ ዘመናዊ አሰራርን እንዲያከናውን ያደረጉ፤ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ የሚሰጡ፤ወደ ገጠር ቤተክርስቲያን የእግር ጉዞ እንዲደረግ በማድረግ አብያተክርስቲያናት እንዲረዱና እንዲተዋወቁ አድርገዋል። በተለይ በቅርቡ አዲስ ቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለትን የቂሻ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ጉዞ እንዲደረግ በማድረግ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለቤተክርስቲያን መታነጽ ከፍተኛ ገቢ እንዲገባ ተደርጓል ። በጸሎታቸው በመንፈሳዊ አገልግሎታቸው የመልካም አሰተዳደርና የልማት አባት መሆናቸውን በተግባር ያሳዩ ፤ሐዋርያዊ አባትነታቸው ዘወትር የሚነገርላቸው ፤ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ከሠራተኞች ጀምሮ ካህናት ዲያቆናት በሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች በምዕመናን ከልብ የሚወደዱ አባት ናቸው። ለሀገራችንና ለሕዝቦቿ ፍቅር ፣ሰላም ፣አንድነት እንዲኖር አብዝተው የሚጸልዩ አባታችን፤ እንኳን ለ ፪ኛ ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሰላምና በጤና አደረስዎ ! ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም ዲላ ኢትዮጵያ የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ብፁዕነትዎ ለረጅም ዘመናት በሰላምና በጤና በሀገረ ስብከትዎ ያቆይልን !!!! #የብፁዕነታቸው_ቡራኬ_አይለየን!!








