በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Admin

የወልቂጤ ቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለ 3 ተከታታይ ዓመታት ሲያስተምራቸው የነበሩ ደቀ መዛሙርትን አስመረቀ።

የወልቂጤ ቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለተከታታይ 3 ዓመታት ሲያስተምራቸው የነበሩ 22 ደቀ መዛሙርትን በዲፕሎማ እንዲሁም ለአንድ ወር ሲሰለጥኑ የነበሩ 38 ካህናትን በሰርተፊኬት በዛሬው ዕለት አስመርቋል። በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይጨብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የኮሌጁ መሥራችና የበላይ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ የአማሮ እና ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ፕሮፌሰር አባ ኃይለ ገብርኤል የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፣ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰቦች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱ ከምርቃት መርሐ ግብሩ በፊት በብፁዕ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለዋል። ሰኔ ፳፱/፳፻፲፯ ዓ/ም ኤክቱስ ©ሳሌም የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

የወልቂጤ ቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለ 3 ተከታታይ ዓመታት ሲያስተምራቸው የነበሩ ደቀ መዛሙርትን አስመረቀ። Read More »

“ምእመናን በሃይማኖት እንዲጸኑ ሰላምን፣ፍቅርን እና አንድነትን ስበኩ!” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዛሬው ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣የደቡብ ምሥራቅ ትግራይና የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ሕዝቄል የከፋና ሸካ፣ቤንች ሸኮ እና ምዕራብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኀላፊ እና ሌሎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እግዶች በተገኙበት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በትርጓሜ መጻሕፍትና በነገረ መለኮት የትምህርት ዘርፍ በቀን እና በማታ ያስተማራቸውን 769 ደቀ መዛሙርትን አስመርቋል። ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት ምእመናን ትእዛዘ እግዚአብሔርን እንዲጠብቁ፣በምግባር እንዲጎለብቱና በሃይማኖት እንዲጸኑ ሰላምን፣ፍቅርን እና አንድነትን በመስበክ የማስተማር ኃላፊነታችሁን ተወጡ ሲሉ ተመራቂዎችን አሳስበዋል፡፡ አክለውም ጌታችን ሐዋርያትን ሂዱና አስተምሩ ብሎ እንደላካቸው ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን መሠረት አድርጋ በየዓመቱ ተማሪዎችን እያስመረቀች ትገኛለች ያሉ ሲሆን ሰላም ከሌለ ምንም አይኖርም ስለዚህም መቻቻል እንዲኖር፣አንድነት እንዲሰፍን እንዲሁም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግብ እንዲሳካ ድርሻችሁን መወጣት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ የኮሌጁ የበላይ ኀላፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቄል በበኩላቸው ነፍስን እና ሥጋን የሚጠግን፣የሚያለመልምና የሕይወት ውኃ ትምህርት በመሆኑ ደቀ መዛሙርቱ በተማሩት ትምህርት መሠረት በሚሄዱበት ሁሉ የዓለሙን ፈተና ተቋቁመው ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንዳለባቸው ተናግረዋል። በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ በተመራቂዎች ወረብና ቅኔ የቀረበ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱ ስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በሚል ስያሜ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትንና መምህራንን ማሠልጠኛ እንዲሆን በ1930 ዓ.ም ተመሥርቶ በአሁኑ ወቅት ከ82 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡

“ምእመናን በሃይማኖት እንዲጸኑ ሰላምን፣ፍቅርን እና አንድነትን ስበኩ!” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ Read More »

በሀገረ ስብከቱ ከስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ ለቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ከማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ጋር በመተባበር ለሁለት የሚቆይ ሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ!!

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከሚገኙ ስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ የቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ወደ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከመግባታቸው በፊት ለሁለት ቀን የሚቆይ ሥልጠና ለመስጠት ከማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ጋር በመተባበር በተዘጋጀው መድረክ ላይ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተገኝተው አባታዊ መልዕክት እና ለአገልግሎት ዝግጁ በመሆን በቀጣይ ስለሚያከናውኑት አገልግሎት ትምህርት ሰጥተዋል። በመልዕክታቸው በቀጣይ ወደ መጡት አካባቢ ሲሰማሩ ፈተናዎችን አልፈው በማገልገል አዲስ የሚጠመቁ አማኒያን አስተምሮ በማምጣት ፣ክርስቲያኖች በእምነታቸው እንዲጸኑ በማድረግ ንሰሐ የሚገቡ ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበሉ ቤተክርስቲያን ባለችበት ሆነ በተገኘው ቦታ ሁሉ በመዘዋወር ወንጌልን ማስተማርና ለሰማያዊ ፀጋ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል ። በቀጣይም አዳዲስ የስብከት ኬላዎችን በማቋቋም በነባሮዎቹ በማስተማር በሚታይና በሚመዘን አገልግሎት ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበው የሁለት ቀን የሥልጠና ቋይታ መልካም እንዲሆን በመመኘት ማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል የሥልጠና ሙሉ ወጪውን በመሸፈን መምህራንን በመመደብ ለሥልጠናው ስኬት ላበረከቱት ምስጋና አቅርበዋል ። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች የማህበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል አመራሮችና የሥልጠናው አስተባባሪዎች አሰልጣኝ መምህራን ተገኝተዋል። ኤክቱስ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም

በሀገረ ስብከቱ ከስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ ለቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ከማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ጋር በመተባበር ለሁለት የሚቆይ ሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ!! Read More »

የአቋም መግለጫ

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ጋር በመሆን ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ የአቋም መግለጫ አውጥቷል የአቋም መግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፦ “ዘአዘዞሙ ለአበዊነ፡፡ ከመ ይንግሩ ለደቂቆሙ፡፡ ወከመ ያእምር ካልእ ትውልድ፡፡ ደቂቅ እለ ይትወለዱ ወይትነሥኡ፡፡ ወይዜንው ለደቂቆሙ፡፡” ለልጆቻቸው ያስታወቁ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን….የሚመጣ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ” መዝ 77 ቁ 5-6 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት ታሪካዊትና ሐዋርያዊት እንደመሆንዋ የዕለት ከዕለት ሥራዋንና አስተዳደርዋን የምታራምደው ቅዱሳን አበው ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወሰኑት ፍትሕ መንፈሳዊ ነው፡፡ እምነትዋን የምታስፋፋበት፣የምታስተምርበትና የምታጸናበትን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ተሰብስቦ በመምከር የጠመመውን በማቅናት የቀናውን በማጽናት በሚሰጠው ውሳኔና በሚያወጣው የሥራ መመሪያ መሠረት ነው፡፡ ይህን ውሳኔና መመሪያ አስፈጻሚው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሥሩ በሚመራቸው መምሪያዎችና የሥራ ክፍሎች አማካኝነት፡- የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልና በሁሉም ዘንድ እንዲታወቅና እንዲከበር ያደርጋል፣ ቤተ ክርስቲያን ባላት መብት መሠረት ሕልውናዋን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይሠራል፣ ሕጓና ሥርዓትዋ እንዲከበር፣በአንድነትዋና በአላማዋ ጸንታ እምነቷ እንዲስፋፋ የሥራ ዕድገቷ ተፋጥኖ ግቡን ይመታ ዘንድ ዕለት በዕለት ይሠራል፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ማግኘት የሚገባውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማሟላት በሚቻልበት ጉዳይ በማተኮር ጉዳዮችን እየመረመረ በሥራ የሚተረጎሙበትን የሥራ አፈጻጸም መመሪያ ከሚሰጥባቸው መምሪያዎች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና የትምህርት ማሰልጠኛ መምሪያ በጋራ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት” በሚል ርዕስ መምሪያዎቹ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሥራ መዋቅር የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ የጉባኤውን ተሳታፊዎች በሙሉ ደስ ያሰኘ ትልቅ ሥራ ከሰኔ 24 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዕለታት ሠርተዋል፡፡ የመርሐ ግብሩም አፈጻጸም በሚገባ ከዋናው መ/ቤት ከየአህረ ሰብከቱ ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዩኒቨርሲቲዎች፣ኮሌጆች፣ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፤ከአዲስ አበባ ክፍላተ ከተሞች ከገዳማትና አድባራት የተመደቡ ሊቃውንት የአብነት ትምህርት መምህራን፣ሰባክያነ ወንጌል (ላዕካነ ወንጌል) በአጠቃላይ በምክክር ጉባኤው የተሳተፉ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት የሚያስገነዝብ ትምህርታዊ ጥናትና መወያያ ርእሶች ተቀርጸው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ከሥልጠና እስከ ተልዕኮ ማስፈጸም ድረስ ያለውን ሐዋርያዊ ግልጋሎት ውስጣዊውን ገጽታ በዳሰሰ መልኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ መስክ በቂ ግንዛቤ ዕውቀትና ችሎታ ባላቸው ሊቃውተ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የቆየውን ልምዳቸውና ዕውቀታቸውን አሁን ላይ ካለው አካሄዳችንና አገልግሎታችን አንጻር የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለሆነው ሁሉ እኔ ማነኝ ብሎ መጠየቅ እስኪያስችል ድረስ በጥናታዊ ጽሑፍ የተደገፈ ትምህርት ተሰጥቷል፤በችግሩም ዙሪያ ያተኮሩ መጠይቆች ተነስተዋል፤ በመምህራኑም በቂ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶናል፡፡ ውይይቱም ሰፊና ጠቃሚ ሐሳብ ማሰባሰብ ያስቻለ ስለሆነና የምክክር ጉባኤው ተካፋዮችም በቅዱስነታቸው የተሰጠንን መመሪያና ቃለ ምእዳን ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተላለፈውን የሥራ አፈጻጸማዊ መመሪያ የጉባኤውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሲመሩት ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ የጉባኤ አመራርና ማብራሪያዎች ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች ከሆኑት ምሁራነ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠንን መመሪያና ከምክክር ጉባኤው ባገኘነው ጠቃሚ ትምህርት መሠረት የሚከተለውን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡ ጉባኤያችን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት የተላለፈውን የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን፣ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተሰጠውን የሥራ መመሪያና ጥናት አቅራቢዎች ያቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፎች በሥራ ለማዋል ቃል እንገባለን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከዋናው መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚወጡት ሕጎችና መመሪያዎች፣እንዲሁም ስለ ስብከተ ወንጌልና ትምህርትና ሥልጠና የሚተላለፉትን ትዕዛዞች በየአህጉረ ስብከቱና በቤተ ክርስቲያኗ ተቅዋማት ሁሉ በተግባር እንዲውሉ ቃል እንገባለን፣ እነዚህ መምሪያዎች የቤተ ክርስቲያኗን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ለማሟላት የወሰዱትን የሥራ ተነሳሽነትና ኃላፊነትን በጋራ የመወጣት ልምዳቸው የሚበረታታ ስለሆነ በዚሁ መልኩ ተቀራራቢ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ የሥራ መዋቅር ክፍሎች በጥምር የሚያስፈጽሙበት አሠራር መዘርጋት የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ስለሚያማክልና የጉባኤው ተሳታፊዎችም የምንደግፈው ስለሆነ በአፈጻጸም ረገድ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁነታችንን እንገልጻለን፡፡ የአብነት ት/ቤቶች እየተስፋፉ መሆናቸው ግልጽ ነው፤እነሱን ያግዙ ዘንድ የተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆችም በንባብ፣በቅዳሴ፣በዜማና በመጻሕፍት የትምህርት ዘርፍ እያደጉ የሚገኝበት ወቅት ስለሆነ ተመርቀው የወጡት ደቀ መዛሙርትም ከዋናው ማእከል ጀምሮ በየአህጉረ ስብከቱና ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቅዋማት በአገልግሎትና በኃላፊነት የሚገኙበት ወቅት ላይ መድረሳችን የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገቷን የሚያሳይ በመሆኑ አሁንም በየጊዜው በጥናት የተደገፈ ሥልጠና በመስጠት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችን አስተዋጽኦ ለመወጣት ዝግጁነታችንን እንገልጻለን፡፡ ቋሚ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት ለማጠናከር፤የመምህራንና የደቀ መዛሙርትን ኑሮ ለመደገፍ በየአካባቢው በየአህጉረ ስብከቱ በቂ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ዘገባዎች ቢያመለክቱም በውስጣዊ የአመራርና ውጫዊ ሁኔታዎች አንዳንድ ችግሮች የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መምህራንን ለፍልሰት እያደረጉ ስላሉ ለወደፊቱ መምህራኑ በየአካቢያቸው ወንበራቸውን አጽንተው ደቀ መዛሙርቶቻቸውን በሁለንተናዊ ስብእና ክብር አስታጥቀው እንዲያወጡ በመሥራት የበኩላችንን አደራና ኃላፊነት እንወጣለን፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ትምህርት ዜማ፣ቅዳሴና ቅኔና ትርጓሜ መጻሕፍት የሚማሩ ደቀ መዛሙርት ለትምህርተ ወንጌልበአርያነት ለሚጠቀስ ለመንፈሳዊ አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ጊዜውን የዋጀ መምህራን ለማግኘት የሥርዓተ ትምህርት ዳሰሳዊ ጥናት የቤተ ክርስቲያኗን ባለሙያዎችና ሌሎች አጋዥ ኃይሎች በማሳተፍ እንዲቀርብ በተደጋጋሚ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነ ስለሆነ እነዚህ ሁለቱም መምሪያዎች ሆኑ ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ተባብረውበት ማኅደረ ጉዳዮች ታይተው የቀሩትን ተግባራት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ምንጊዜም ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ያላቋረጠች መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷም በውጭው ዓለም በሚገኙ ክፍላተ ዓለማት ጭምር መስፋፋቷ በእግዚአብሔር ረድኤት እየቀጠለ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያኗ ወገኖች የሆን ውሉደ ክህነትና ውሉደ ክርስቲያን ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋ መፋጠን የእምነት ተከታዮቿንም ምእመናን ለመጠበቅ የጋራ አሠራር በያዘ መልኩ በውስጣዊና ውጫዊ አሠራራችንና ግንኙነታችን ሁሉ ከመምሪያዎቹም የሚተላለፉ የሥራ መርሐ ግብሮችን ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት የሰጠውን ታላቁን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተቀብላ በሐዋርያት አሠረ ፍኖት ተገብታ በባለቤትነት ታስፈጽማለች። ነገር ግን ከእኛ ከአገልጋዮች የእውቀት እና የቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም ከአንዳንዶቻችን ጥቅም ተኮር እንቅስቃሴ የተነሳ ይህንን ታላቅ ተልእኮ ለመፈጸም የተቸገርን ቢሆንም ከዚህ በኋላ በተቻለን መጠን ለመማር፣የተማርነውን ለማስተማር ፣ለማሳመን፣ ከመንጋው ለመቀላቀልና ለመንከባከብ በሚደረገው ማንኛውም ጥረት ከቤተክርስቲያን ጎን ለመቆም ቃል እንገባለን። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገራችን ለዘመናት ሃይማኖትንና ታሪክን ስታስተምርና ስትዘግብ ብራና ዳምጣ፣ቀለም በጥብጣ፣የራሷን ፊደል ቀርጻ፣ የራሷን ቀመር ቀምራ ለቁጥር የሚያዳግቱ መጻሕፍትን ጽፋለች፤ እየጻፈችም ነው። ነገር ግን አባቶቻችን የጻፏቸው መጻሕፍት በየገዳማቱ ግምጃ ቤት ሆነው ለጉብኝት አገልግሎት ከመዋል ባሻገር ለጥናትና ምርምር ክፍት ተደርገው ለማኅበረሰቡ መድረስ ባለመቻላቻው በዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ወገኖች ቤተክርስቲያንን መጻሕፍት አልባ ከማስመሰሉም በላይ የትምህርት ተቋማቶቻችን የአባቶቻችን ወዝ ባልካቸው መጻሕፍትና ታሪክ አልባ ተሞልተዋል የሚል ስሞታ እንዳለ ተገልጿል፤በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው ጥረት ጥናትና ምርምር በመሥራት በሁሉም ዘርፍ ከቤተክርስቲያን ጎን ለመቆም ቃል እንገባለን። ቅድስት ቤተክርስቲያን የሁሉ እናት እንደመሆኗ መጠን ዘር ቀለም ጎሳ ሳትለይ እናቴ ብሎ የመጣውን ሁሉ አቅፋ የያዘች፣ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ከመሆኗ ባሻገር የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምታቀብል መሆኗ የሚታወቅ ነው፤ነገር ግን ከላይ እስከታች የምንገኝ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በጠረፋማ ሥፍራ የሚኖሩ ሰዎችን ወንጌል ለማስተማር የምናደርገው ጥረት ጅምሩ የሚበረታታ ቢሆንም ፍጹም ሥራ መሥራትን፣ ለሌሎች ዓለማትም መትረፍን የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን በጉባኤው ከተሰጠው ዐውደ ጥናት ተረድተናል፤ በመሆኑም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሁሉ እናትነት መላልሶ ለማስተማርና ለመላላክ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ

የአቋም መግለጫ Read More »

“ራሳችንን ለወንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል” ሲሉ ‎ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ፡፡

“ራሳችንን ለወንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል” ሲሉ ‎ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ፡፡ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው በሁለተኛ ቀን የምክክር ጉባኤ ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “‎ይህ ሁሉ ሊቃውንት እያለ ቤተክርስቲያን መቸገር የለባትም ለዚህም ራሳችንን ማዘጋጅት ይጠብቅብናል፡፡ በዘር፣ በጎሣ መከፋፈል ለቤተክርስቲያን አይጠቅማትም፣ ራሳችንን ለውንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል ቀናነት እና ታዛዥነት የመጀመሪያ ተግባራችን መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ ‎የመቄዶንያን የበጎ አደራጎት ማኅበር መሥራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ስለ ማኅበሩ አሁናዊ ሁኔታ ገልጸዉ ሁሉም ሰው የአቅሙን ርዳታ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‎ክቡር ዶ/ር ቢኒያም በለጠ አያይዘውም እንዳሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የአየር ሰዓት በመስጠት እያገዝን ስለሆነ በድርጅታችን ስም ምስጋና እናቀርባለን ብልዋል፡፡ መርሐ ግብሩ ላይ ‌‎የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከገዳማትና ከአድባራት የተወጣጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተገኝተዋል፡፡ ©EOTCTV

“ራሳችንን ለወንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል” ሲሉ ‎ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ፡፡ Read More »

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመሆን የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ።

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመሆን የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ። በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋህዶ አዳራሽ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመቀናጀት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ። ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል። መርሐ ግብሩም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን ቅዱስነታቸውም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ቤተ ክርስቲያን የምትጠበቀው በካህናትና በምዕመናን ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም ቤተ ክርስቲያንን እና ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ እየተሰበሰቡ መመካከር አስፈላጊ ነው ብለዋል። ወቅታዊውን የበሀገራችንን ሁኔታንም በማስታወስ አሳሳቢነቱን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ለዚህም ቤተክርስቲያንን ጠንክረን መጠበቅ አለብንም ሲሉ መክረዋል። ይህችን ቤተ ክርክቲያን የሚቃረኗት ብዙ መሆናቸውንም ጠቅሰው ለዚህም ሁላችሁም ኃላፊነታችሁን ለመወጣት መሰል ጉባኤያት አስፈላጊም ኃላፊነትም ነው ሲሉ ቤተ ክርስቲያንን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚያሻ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ሐዋርያትን በዓለም ዞረው ወንጌልን መስበካቸውን ጠቅሰው የሐዋርያትን ፈለግ የተከተለችው ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ ከመናፍቃን ጋር ያደረገችውን ተጋድሎም አንስተዋል።ለዚህም በዋቢነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጉባኤያትን አንስተው አርዮስን፣መቅዶንዮስ እና ንስጥሮስን አውግዛ መለየትዋን ገልጸዋል። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋ ወንጌልን ተደራሽ ማድረግ እና ተልዕኮዋን እንዳትወጣ የሚያደርጓትን ችግሮችን መቅረፍ እና አውግዞ መለየት ነውም ሲሉ አክለዋል። “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ የስብከተ ወንጌልን እና የአብነት ትምህርትን ለማስፋፋት ያለመ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ዋና ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚ አሰፋ ሲሆኑ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ መርሐ ግብሩ በጥምረት መዘጋጀቱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንስተዋል። ሁለቱም መምሪያዎች ቀደምት መሆናቸውንም ጠቅሰው ምንም እንኳ የተለያየ የሥራ ዘርፍ ቢኖራቸውም በስብከተ ወንጌል ረገድ ያላቸውን አንድነትም አብራርተዋል። በመሆኑም ከወርሐ መጋቢት ጀምረው በጥምረት መስራት መጀመራቸውን ገልፀው ሊሰሩ ያሰቧቸውንም ዘርፈ ብዙ የሥራ መስኮችም በዝርዝርና በቁጥር አቅርበዋል። መላከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለ ፅድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያም በበኩላቸው ጉባኤው ውጪያዊውን ችግሮች ለመፍታት የተዘጋጀ ሳይሆን ውስጣዊ ችግሮችን ለማየት እና ለመፈተሽ የተዘጋጀ ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል። መላከ ሰላም “መንፈሳዊነት ለሁለንተናዊ አገልግሎት” በሚል ርዕስም ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናታዊ ጽሑፋቸውም የመንፈሳዊነትን ምንነት ዳሰዋል። ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ትምህርት ትውፊታዊ መሆኑንም የጠቀሱ ሲሆን ያ ወንጌል ቀለም ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነትንም የያዘ እና እኛም የወረስነው ነው ሲሉ መንፈሳዊነትን በተለያየ መልክ አብራርተዋል። በመጨረሻም በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፍ ዙሪያ ሰፊ ሀሳብ እና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን በዋናነት በመምህራን ረገድ ያለው የእውቀት ክፍተት እና የመንፈሳዊነት ዝለት ተነስቷል። መርሐ ግብሩ በቀጣይም በየዓመቱ የሚዘጋጅ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በከሰዓቱም ውሎም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት ሲሆን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤተ መጽሐፍትና ወመዘክር ጉብኝት የሚቋጭ መሆኑ ታውቋል። በዕለቱም ብፁዓን አበው ላቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፤የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። መርሐ ግብሩ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ ሲሆን በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል። ©EOTC TV

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመሆን የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ። Read More »

ሦስተኛው ዙር ወርሃዊ የወንጌል ጉባኤ በዲላ ደ/ገ/ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተደረገ!!

ሦስተኛው ዙር ወርሃዊ የወንጌል ጉባኤ በዲላ ደ/ገ/ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተደረገ!! ለጥምቀት በዓል መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ ጥምቀትን በዲላ በሚል መጠሪያ ስም የተመሠረቱ የወጣቶች መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኀበር በብፁዕ አባታችን አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መልካም ፈቃድ በወር መጨረሻ እሁድ የሚደረገው የወንጌል አገልግሎት የሦስተኛ ወሩን አገልግሎት በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተካሄደ። በዕለቱ ሊቀ ሊቃውንት ስሙር አላምረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የትምህርትና የካህናት አስተዳደር ክፍል ኃላፊ የሆኑት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ጉባኤው በሚቀጥለው ወር በመጨረሻ እሁድ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በስልክ በዚያ ለተሰበሰቡ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው በአገልግሎት ምክንያት በመርሃግብሩ መገኘት እንዳልቻሉ ገልጸው ቃለ ምህዳን እና ቡራኬ ሰጥተው መርሃግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል።

ሦስተኛው ዙር ወርሃዊ የወንጌል ጉባኤ በዲላ ደ/ገ/ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተደረገ!! Read More »

ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ የትንሣኤን በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር ተከናወነ!!

ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ የትንሣኤን በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር ተከናወነ!! ለብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረስዎ መርሐግብር ተናውኗል። በዕለቱ የሃገረ ስብከቱ የሥራ ሃላፊዎች፣ የመንበረ ጵጵስና እና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና ጸሐፊ፣ የአድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ የካህናት ተወካዮች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እና የምዕመናን ተወካዮች በተገኙበት ተከናውኗል። በዕለቱ መርሐ ግብሩ በሀገረ ስብከቱ ጳጳስ የተመራ ጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን የአድባራቱ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ዝማሬ ካቀረቡ በኋላ ያሬዳዊ ዝማሬ ከአድባራቱ በተውጣጡ ሊቃውንት ቀርቧል። በመቀጠልም ከጪጩ የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንና እና የበዓታ ዳግማዊት ጌቴሴማኒ ቤተክርስቲያን የመጽሐፈ ሐዲሳት መምህራን ቅኔ የቀረበ ሲሆን ከመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቷል። በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ቃለ ምህዳንና ቡራኬ ሰጥተው መርሐግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል።

ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ የትንሣኤን በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር ተከናወነ!! Read More »

ከትንሣኤ በኋላ ያሉ ዕለታት ስያሜዎች

ከትንሣኤ በኋላ ያሉ ዕለታት ስያሜዎች ከትንሣኤ ሌሊት ፩ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያለው ሳምንት የፉሲካ ምሥጢር የተገለጠበት፤ ከግብፅ ወደ ምድረርስት ከሲኦል ወደ ገነት መሻገርን የሚያመላክት ሳምንት ነው። ለፉሲካ የሚታረደውም በግ ፉሲካ ይባላል (ዘዳ. ፲፮÷፪:፭÷፮)፤ ፉሲካ ማለት ደግሞ ማለፍ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትም ሳምንት የፉሲካ ሳምንት ነበር፤ (ሉቃ. ፳፪፥፲፬-፲፮፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፰-፵)። እርሱም ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን ፉሲካችን ክርስቶስ ተባለ፤ ብሉይ ደግሞ የሐዲስ አምሳል ነው። ይኸውም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ካሻገራቸው በኋላ ወደ ምድረ ርስት፤ ነፍሳት ደግሞ በክርስቶስ መሪነት ከሲኦል ወደ ገነት መግባታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕለቱም ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፤ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ፤ግብፅ የሲኦል፤ የገሃነመ እሳት፤ የፈርዖን የዲያብሎስ፤ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፤ እስራኤል የምእመናንና ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል ምሳሌ ነው፡፡ ሰኞ– ማዕዶት (ፀአተ ሲኦል) ማዕዶት የቃሉ ትርጓሜ መሻገር ሲሆን፤ በዚህ ቀን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሐሳር ወደ ክብር፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውንና ፉሲካችን ክርስቶስ መሆኑን ታስባለች። ማክሰኞ– ቶማስ ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፤ በቀኖት የተቸነከረው እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን» ብሎታል። ቶማስም «ጌታዬ አምላኬም»፤ ብሎ በመለሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስም «ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓንስ ናቸው» አለው (ዮሐ ፳፥፳፯-፳፱)፤ ቶማስ የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች። ዲዲሞስ የተባለ ከአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙር አንዱ ቶማስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ባላቸው ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልነበረም»። ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ (ማቴ. ፲፥፪-፫) ቶማስ በአራማይክ ዲዲሞስ በግሪክ መንታ ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፳፥፳፬)፡፡ ቶማስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በፋርስና በሕንድ ወንጌልን እንዳስተማረ ይነገራል። ለቶማስ ጎኑን እንዲዳስስ የፈቀደው ለሌሎችም ቅዱሳን ሐዋርያት የተቸነከረውን እጅና እግሩን ያሳየው ካህናት ሥጋውና ደሙን እንዲፈትቱ ነው፤ ዮሐንስም በእጃችን ዳሰስነው ብሏል፤ (ሉቃ. ፳፬፥፴፱)፡፡ ለማርያም መግደላዊት ግን የተነሣ ዕለት አትንኪኝ ማለቱ ለሴቶች ሥጋውን ደሙን መፈተት አልተፈቀደም ሲል ነው ብለው ሊቃውንት ያትታሉ፤ «አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጅና፡- ወደ አባቴ÷ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ÷ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው» አላት፤ (ዮሐ. ፳፥፲፯)። ገቦ መለኮቱን የዳሰሰች እጁ በሕይወት ትኖራለች፤ በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር በመንበር ላይ ትኖራለች። በየዓመቱ በእመቤታችን በዓል በአስተርእዮ ሊያጥኑ ሲገቡ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፤ ዓመት አገልግሎ ያርፋል። ረቡዕ –አልዓዛር አልዓዛር ክርስቶስ ያስነሣው የማርያምና የማርታ ወንድም ነው፤ የስሙም ትርጓሜ እግዚአብሔር ረድቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፲፩፥፯-፵፰)፤ አልዓዛር የሞተው መጋቢት ፲፯ ነበር፡፡ እህቶቹም ክርስቶስ እንዲመጣ መልእክት ልከውበት ነበር፤ ክርስቶስ ግን በ፬ኛው ቀን ማለትም መጋቢት ፳ መጥቶ ከሞት አስነሥቶታል፤(ዮሐ.፲፩፥፵፬)፡፡ ፋሲካውንም በወዳጁ በአልዓዛር ቤት ያከብር ዘንድ ከቀደ መዛሙርቱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አስቀድሞ ላከ፤ ከዚያም በአልዓዛር ቤት ሆኖ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዓት ምሥጢረ ቁርባንን ሰርቶ ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው፤ አልዓዛር ከተነሣ በኋላ በሐዋርያት ኤጲስ ቆጶስነት ተሸሞ ፵ ዓመት አገልግሎ ግንቦት ፳፯ ቀን ዐርፏል (ስንክሳር ግንቦት ፳፯)፡፡ አዳም ሐሙስ አዳም የመጀመሪያ ሰውና የሰው ሁሉ አባት ነው፤ በ፮ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ፤ (ዘፍ. ፫÷፲፭) አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል፡፡ ክርስቶስ በተነሳበት በአምስተኛው ቀን ሐሙስ አዳም ይባላል፤ ጌታችን አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት እንደነበር በቀሌምንጦስ ተጽፏል፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት አስወጣቸው (ኩፋ.፬፥፲፮፤ዘፍ.፫፥፳፫) «ብዙ ተባዙ» ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ ወርደው ልጆችን ወለዱ ይላል፡፡ የተወለዱትም ልጆችም በቁጥር ፷ እንደሆኑ (፩መቃ. ፳፰፥፮) የተወለዱት ልጆች ደጎችና ክፉዎች እንደ ነበሩ በአቤልና በቃየል ታውቋል፤ (ዘፍ. ፬፥፰)፤ አዳም በዚህ ዓለም ፱፻፴ ዓመት ኑሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፵፻፭፻፸ ሚያዚያ ፮ ዐርፏል፡፡ ዐርብ– ቤተ ክርስቲያን ዐርብ የእግዚአብሔር ቅድስት ማደሪያ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ተሰይማለች፤ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፤ ዕለተ ዐርብ፤ የሥራ መከተቻ፤ ምዕራብና መግቢያ በሚሉት ስያሜዎችም ትጠራለች፡፡ በዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምር በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንጻዋ መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፤(ኤፍ.፪፥፲፱፤ራዕ.፩፥፮-፰)፡፡ ቅዳሜ– ቅዱሳት አንስት ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፤ ይህም ስያሜ በስቅለት ዕለት በልቅሶና በዋይታ የሸኙትን፤(ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፤«ከሳንምንቱ በመጀመሪያዩቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩ )፡፡ እሑድ– ዳግም ትንሣኤ «ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና÷«ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው፤ ማቴ.፳፥፲፱፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተሰውሮ ከሰነበተ በኋላ በዕለተ እሑድ በዝግ ቤት እንዳሉ ዳግም ተገለጸላቸው፤ስለዚህም ዳግም ትንሣኤ ተባለ፡፡ (ምንጭ:-መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ፤ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ፤ ምዕ. ፳፥፳፬)

ከትንሣኤ በኋላ ያሉ ዕለታት ስያሜዎች Read More »

ከአራቱ ወረዳ ለተውጣጡ ከቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ጋር ውይይት ተደረገ!!

ከአራቱ ወረዳ ለተውጣጡ ከቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ጋር ውይይት ተደረገ!! በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከአራት ወረዳ ቤተክህነት ማለትም ከመንበረ ጵጵስናና ወናጎ፣ ከይርጋጨፌ፣ከኮቸሬና ገደብ ፣ከቡሌና ረጴ ወረዳዎች ከተውጣጡ በጌዴኡፋ ቋንቋ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከሚሰጡ ሰባኪያነ ወንጌል ጋር ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ጋር ውይይት ተደረገ። ውይይቱ ከቤተክርስቲያን ካህናት ማሰልጠኛ ተመርቀው ወጥተው ምን አከናወኑ፣የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲሰጡ የገጠማቸው ተግዳድሮት ነበረ፣ለገጠማቸው ችግር የወሰዱት የመፍትሔ ሃሳብ ምን ነበር፣በአገልግሎት የተገኘው ውጤት ምን ነበር፣ያሉትን ለማጽናት የጠፉትን ለመመለስ አዳዲስ ኢአማንያንን ለማምጣት ምን አከናወኑ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን። ሰባኪያነ ወንጌሉ በአገልግሎት ላይ የገጠማቸውን ችግር ያነሱ ሲሆን መስዋዕትነት እስኪከፍሉ ድረስ ዋጋ መክፈላቸው ሰንበት ት/ቤት ማደራጀት ባዕድ አምልኮ ማጥፋት ብዙ ኢአማኒያን ማስጠመቅ ኮርስ መስጠት በማኀበራዊ ሕይወት መሳተፍ በሀዘንና በደስታ ስብከተ ወንጌል መስጠት የሚሉ የአገልግሎት ተግባራትን የዘረዘሩ ሲሆን። በቀጣይ ከተከናወነው ያልተሰራው ስለሚበዛ በቁጭት በቋንቋ ለማስተማር ቃል ገብተዋል። የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ በሰጡት አስተያየት ለተጠራንበት አገልግሎት ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ ከጠባቂነት መውጣትና በዕቅድና በዓላማ ማገልገል አገልግሎታቸው ሁሉ በውጤት የታጀበ መሆን እንዳለት በተለይ ያሉትን በማጽናትና መጠበቅ የጠፉትን ማምጣት አዳዲስ አማኒያንን ወደ ክርስትና በማምጣት ላይ አገልግሎታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል። በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በማጠቃለያው የስብከተ ወንጌል በሚገባ አገልግሎት አልተፈጸም የቤተክርስቲያንን ተልዕኮ በአግባቡ አውቆ ያለመፈጸም ሰባኪ ከጠባቂነት መውጣት ለዚህ አገልግሎት የተጠራን ባለዕዳዎች መሆንናችንን አንስተው የማሳመኑን የማስተማሩን ሥራ በአግባቡ መወጣት አለብን ብለዋል። በየመንደሩ የስብከተ ወንጌል ኬላ ማቋቋምና አገልግሎትን መፈጸም በማኀበራዊ ሁነቶች ላይ መሳተፍ በቁርጠኝነት ወንጌልን ማገልገል እንደሚያስፈልግ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት መክፈል እንደሚገባ አሳስበው በቀጣይ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክት የተወጋጀና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሥምሪት እንደሚሰጥ በማሳሰብ ውይይቱ ተጠናቋል ።

ከአራቱ ወረዳ ለተውጣጡ ከቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ጋር ውይይት ተደረገ!! Read More »

Scroll to Top