በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ቀዳሚ ገጽ ዜና

የሀዋሳ ታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እና የቅዱስ ሲኖስ ዋና ጸሐፊው በተገኙበት አስመረቀ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ፲፭ ደቀ መዛሙርትን ቅዳሜ ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ዓ/ም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትየ፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዌ በደማቅ ሥነሥርዓት አስመርቋል። ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከትና የሀዋሳ ታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ በዚሁ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት በዛሬው ዕለት የተመረቃችሁ ደቀ መዛሙርት በምትሰማሩበት ሁሉ ማስተዋልና ጥበብን በመከተል ወደ ዓለም ዳስቻ ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ስበኩ የሚለውን የወንጌሉን ቃል በመከተልና በመተግበር እንድታገለግሉ አደራ በማለት አገልግሎታችሁ ሁሉ ውጤታማና የተሳካ ይሆን ዘንድ አምላካችን እግዚአብሔርን እንለምናለን ብለዋል። በማያያዝም ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን የትምህርት እድል እንዲመቻች ያደረገችው ዶግማ፣ቀኖናዋና ትውፊቷ ተጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ነው። ያሉት ብፁዕነታቸው ዛሬ ለምረቃ የበቃችሁ ደቀ መዛሙርትም ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀትና በየትኛውም ስፍራና ሁኔታ ውስጥ ሁሉ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ ለመወጣት የተዘጋጃችሁ መሆን ይኖርባችኋል። ብለዋል። ወደ ኮሌጃችን ለመማር ስትመጡ የገባችሁትን ቃል እንዲሁም ዛሬም በዚህ የምረቃ መርሐ ግብር ቤተክርስቲያንን እና ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል የገባችሁት ቃል ኪዳን ባገኛችሁት ዕውቀትና ክህሎት በትጋት እንደ ምትፈጽሙት እምነታችን ጽኑዕ ነው።ያሉት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የኮሌጃችን የመጀመሪያ ምሩቃን ደቀ መዛሙርት ልጆቻችን! በሥራችሁ ሁሉ የምታሳዩት ጥረትና ትጋት እንዲሁም ለሁሉ አርዓያና ምሳሌ በመሆን በምትሰጡት አገልግሎት ቤተ ክርስቲያንን እና የተማራችሁበትን ኮሌጅ የምታስመሰግኑ እንደ ምትሆኑ እምነታችን ነው። መጪው የሥራና የአገልግሎት ዘመናችሁ ሁሉ የተቃና እንዲሆን ዘወትር ጸሎታችን ነው በማለት መልዕክታቸውን አጠናቀዋል። በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ደቀ መዛሙርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል። በኮሌጁ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩትና በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት ደቀ መዛሙርት በሲዳምኛ፣በኦሮምኛ፣በዳውሮኛ፣ በከምባትኛ፣በሃድይኛ፣በጋሞኛ፣በኮይሬኛ፣በጌዲኦኛ፣በከፋኛና በወላይትኛ ቋንቋዎች ማስተማር የሚችሉ በመሆናቸው በቤተክርስቲያን አገልግሎት ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይታመናል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት የእንኳን ደስ አላችሁ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈው መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል። ©የኢኦተቤክ ህዝብ ግንኙነት

የሀዋሳ ታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እና የቅዱስ ሲኖስ ዋና ጸሐፊው በተገኙበት አስመረቀ። Read More »

ብፁዕ አቡነ ገሪማ በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት የመስክ ጉብኝት!!

በባለፈው ዓመት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እያንዳንዱ መሬት ጾም ማደር እንደሌለበት ባስተላለፉት መመሪያ መሰረት በሀገረ ስብከቱ ባሉ አጥብያ አቢያተ ክርስቲያናት የተሰሩ በርካታ የግብርና የልማት ሥራዎት እየተጎበኙ ይገኛሉ። በዚሁ መሰረት የዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አንድ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ፓፓያ ፣ ማንጎ፣ የጓሮ አትክልት ፣ ብርቱካን፣ ሸንኮራ እና የንብ እርባታ ተጎብኝቷል። ኤክቱስ ሐምሌ 04/2017

ብፁዕ አቡነ ገሪማ በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት የመስክ ጉብኝት!! Read More »

በ አረጋዊዉ አባት ርዕሠ ደብር ለገሠ በለጠ አስተባባሪነት ለገጠር አብያተክርስቲያናት የንዋየ ቅድሳትና የቅዱሳት መጽሐፍት ድጋፍ ተደረገ !!

በጌዴኦ በኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ደብረ ገነት ለብዙ ዓመታት ያገለገሉትና አሁን በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የሚገኙት ርዕሰ ደብር ለገሠ በለጠ የንሰሐ ልጆቻቸውን በማስተባበር በሀገረ ስብከቱ ለሚገኙ በንዋየ ቅድሳት አለመኖር ምክንያት አገልግሎት ለማይሰጡ አብያተክርስቲያን የሚሆን ንዋየ ቅድሳት ቅዱሳትና መጽሐፍትን ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ለሀገረ ስብከቱ ጳጳስ አስረክበዋል ። በተለይ ርዕሰ ደብር ለገሰ በለጠ ድጋፍ የተደረጉትን መጽሐፍቱን በግል ገንዘባቸው እንዳስደጎሱ ታውቋል። ድጋፍ የተደረጉ የንዋየ ቅድሳት አይነት፦ ፩. የአምስት ሰሞነኛ ሙሉ ልብሰ ተክህኖ ፪. ወንጌል አዲስ ኪዳን በግዕዝ እና በአማርኛ-ተአምረ ማርያም-መጽሐፈ ቅዳሴ በግዕዝና በአማርኛ -መዝሙረ ዳዊት-መጽሐፈ ሰዓታት-ማህሌተ ጽጌ-ፀሎተ ዕጣን-መጽሐፈ ግጻዌ-መጽሐፈ ግንዘት-መጽሐፈ ክርስትና ሲሆን ይህን የንዋየ ቅድሳትና የመጽሐፍት ስጦታ ያበረከቱት ወልደ ሚካኤል፣ ኅይለ ገብርኤል፣ወልደ ገብርኤል ፣ ወልደ አረጋዊ፣ ፍቅረ አማኑኤል፣ ኃይለ ማሪያም ናቸው። ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ የተበረከቱትን ንዋየ ቅድሳትና የመጽሐፍት ስጦታ ተረክበው መልዕክት ምስጋና አረጋዊ አባት ርዕሰ ደብር ለገሰ በለጠንና በገንዘባቸው የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል ። ኤክቱስ ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም

በ አረጋዊዉ አባት ርዕሠ ደብር ለገሠ በለጠ አስተባባሪነት ለገጠር አብያተክርስቲያናት የንዋየ ቅድሳትና የቅዱሳት መጽሐፍት ድጋፍ ተደረገ !! Read More »

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የልደት በዓል በወናጎ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ተከበረ!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ሰኔ ፴ ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ክብር የሚከበረው ዓመታዊ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የልደት በዓል በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተክህነት የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ የመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ጸሐፊ ሊቀኅሩያን ቀሲስ እሸቱ ዋለ የወናጎ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያምና ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን ግሩም በቀለ ሊቃውንት ካህናትና የወናጎና የአካባቢው ምዕመናን በተገኙበት በወናጎ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተከብረ። መርሃግብሩ በደብሩ ዋና ጸሐፊ በሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምሕረቴ ገብረ ሥላሴ የተመራ ሲሆን ለዕለቱ የሚስማማ ወረብ በደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ቀርቧል። ትምህርተ ወንጌል የመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን እሸቱ ዋለ የሰጡ ሲሆን በዕድሳት ላይ ለሚገኘው ለደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር በሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ በሊቀ ትጉሃን ሀብታሙ አበበ ተሰጥቶ መርሃግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል። ኤክቱስ ሰኔ 30/2017

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የልደት በዓል በወናጎ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ተከበረ!! Read More »

የወልቂጤ ቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለ 3 ተከታታይ ዓመታት ሲያስተምራቸው የነበሩ ደቀ መዛሙርትን አስመረቀ።

የወልቂጤ ቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለተከታታይ 3 ዓመታት ሲያስተምራቸው የነበሩ 22 ደቀ መዛሙርትን በዲፕሎማ እንዲሁም ለአንድ ወር ሲሰለጥኑ የነበሩ 38 ካህናትን በሰርተፊኬት በዛሬው ዕለት አስመርቋል። በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይጨብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የኮሌጁ መሥራችና የበላይ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ የአማሮ እና ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ፕሮፌሰር አባ ኃይለ ገብርኤል የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ፣ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰቦች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱ ከምርቃት መርሐ ግብሩ በፊት በብፁዕ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለዋል። ሰኔ ፳፱/፳፻፲፯ ዓ/ም ኤክቱስ ©ሳሌም የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

የወልቂጤ ቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለ 3 ተከታታይ ዓመታት ሲያስተምራቸው የነበሩ ደቀ መዛሙርትን አስመረቀ። Read More »

“ምእመናን በሃይማኖት እንዲጸኑ ሰላምን፣ፍቅርን እና አንድነትን ስበኩ!” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዛሬው ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የበላይ ኃላፊ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣የደቡብ ምሥራቅ ትግራይና የራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ሕዝቄል የከፋና ሸካ፣ቤንች ሸኮ እና ምዕራብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኀላፊ እና ሌሎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እግዶች በተገኙበት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በትርጓሜ መጻሕፍትና በነገረ መለኮት የትምህርት ዘርፍ በቀን እና በማታ ያስተማራቸውን 769 ደቀ መዛሙርትን አስመርቋል። ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት ምእመናን ትእዛዘ እግዚአብሔርን እንዲጠብቁ፣በምግባር እንዲጎለብቱና በሃይማኖት እንዲጸኑ ሰላምን፣ፍቅርን እና አንድነትን በመስበክ የማስተማር ኃላፊነታችሁን ተወጡ ሲሉ ተመራቂዎችን አሳስበዋል፡፡ አክለውም ጌታችን ሐዋርያትን ሂዱና አስተምሩ ብሎ እንደላካቸው ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን መሠረት አድርጋ በየዓመቱ ተማሪዎችን እያስመረቀች ትገኛለች ያሉ ሲሆን ሰላም ከሌለ ምንም አይኖርም ስለዚህም መቻቻል እንዲኖር፣አንድነት እንዲሰፍን እንዲሁም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግብ እንዲሳካ ድርሻችሁን መወጣት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ የኮሌጁ የበላይ ኀላፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቄል በበኩላቸው ነፍስን እና ሥጋን የሚጠግን፣የሚያለመልምና የሕይወት ውኃ ትምህርት በመሆኑ ደቀ መዛሙርቱ በተማሩት ትምህርት መሠረት በሚሄዱበት ሁሉ የዓለሙን ፈተና ተቋቁመው ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል እንዳለባቸው ተናግረዋል። በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ በተመራቂዎች ወረብና ቅኔ የቀረበ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱ ስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በሚል ስያሜ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትንና መምህራንን ማሠልጠኛ እንዲሆን በ1930 ዓ.ም ተመሥርቶ በአሁኑ ወቅት ከ82 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡

“ምእመናን በሃይማኖት እንዲጸኑ ሰላምን፣ፍቅርን እና አንድነትን ስበኩ!” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ Read More »

በሀገረ ስብከቱ ከስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ ለቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ከማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ጋር በመተባበር ለሁለት የሚቆይ ሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ!!

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከሚገኙ ስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ የቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ወደ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከመግባታቸው በፊት ለሁለት ቀን የሚቆይ ሥልጠና ለመስጠት ከማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ጋር በመተባበር በተዘጋጀው መድረክ ላይ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተገኝተው አባታዊ መልዕክት እና ለአገልግሎት ዝግጁ በመሆን በቀጣይ ስለሚያከናውኑት አገልግሎት ትምህርት ሰጥተዋል። በመልዕክታቸው በቀጣይ ወደ መጡት አካባቢ ሲሰማሩ ፈተናዎችን አልፈው በማገልገል አዲስ የሚጠመቁ አማኒያን አስተምሮ በማምጣት ፣ክርስቲያኖች በእምነታቸው እንዲጸኑ በማድረግ ንሰሐ የሚገቡ ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበሉ ቤተክርስቲያን ባለችበት ሆነ በተገኘው ቦታ ሁሉ በመዘዋወር ወንጌልን ማስተማርና ለሰማያዊ ፀጋ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል ። በቀጣይም አዳዲስ የስብከት ኬላዎችን በማቋቋም በነባሮዎቹ በማስተማር በሚታይና በሚመዘን አገልግሎት ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበው የሁለት ቀን የሥልጠና ቋይታ መልካም እንዲሆን በመመኘት ማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል የሥልጠና ሙሉ ወጪውን በመሸፈን መምህራንን በመመደብ ለሥልጠናው ስኬት ላበረከቱት ምስጋና አቅርበዋል ። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች የማህበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል አመራሮችና የሥልጠናው አስተባባሪዎች አሰልጣኝ መምህራን ተገኝተዋል። ኤክቱስ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም

በሀገረ ስብከቱ ከስድስቱ ወረዳ ቤተክህነት ለተውጣጡ ለቋንቋ ሰባኪያነ ወንጌል ከማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ጋር በመተባበር ለሁለት የሚቆይ ሥልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ!! Read More »

የአቋም መግለጫ

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ጋር በመሆን ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ የአቋም መግለጫ አውጥቷል የአቋም መግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፦ “ዘአዘዞሙ ለአበዊነ፡፡ ከመ ይንግሩ ለደቂቆሙ፡፡ ወከመ ያእምር ካልእ ትውልድ፡፡ ደቂቅ እለ ይትወለዱ ወይትነሥኡ፡፡ ወይዜንው ለደቂቆሙ፡፡” ለልጆቻቸው ያስታወቁ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን….የሚመጣ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ” መዝ 77 ቁ 5-6 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት ታሪካዊትና ሐዋርያዊት እንደመሆንዋ የዕለት ከዕለት ሥራዋንና አስተዳደርዋን የምታራምደው ቅዱሳን አበው ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወሰኑት ፍትሕ መንፈሳዊ ነው፡፡ እምነትዋን የምታስፋፋበት፣የምታስተምርበትና የምታጸናበትን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ተሰብስቦ በመምከር የጠመመውን በማቅናት የቀናውን በማጽናት በሚሰጠው ውሳኔና በሚያወጣው የሥራ መመሪያ መሠረት ነው፡፡ ይህን ውሳኔና መመሪያ አስፈጻሚው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሥሩ በሚመራቸው መምሪያዎችና የሥራ ክፍሎች አማካኝነት፡- የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልና በሁሉም ዘንድ እንዲታወቅና እንዲከበር ያደርጋል፣ ቤተ ክርስቲያን ባላት መብት መሠረት ሕልውናዋን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይሠራል፣ ሕጓና ሥርዓትዋ እንዲከበር፣በአንድነትዋና በአላማዋ ጸንታ እምነቷ እንዲስፋፋ የሥራ ዕድገቷ ተፋጥኖ ግቡን ይመታ ዘንድ ዕለት በዕለት ይሠራል፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ማግኘት የሚገባውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማሟላት በሚቻልበት ጉዳይ በማተኮር ጉዳዮችን እየመረመረ በሥራ የሚተረጎሙበትን የሥራ አፈጻጸም መመሪያ ከሚሰጥባቸው መምሪያዎች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና የትምህርት ማሰልጠኛ መምሪያ በጋራ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት” በሚል ርዕስ መምሪያዎቹ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሥራ መዋቅር የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ የጉባኤውን ተሳታፊዎች በሙሉ ደስ ያሰኘ ትልቅ ሥራ ከሰኔ 24 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዕለታት ሠርተዋል፡፡ የመርሐ ግብሩም አፈጻጸም በሚገባ ከዋናው መ/ቤት ከየአህረ ሰብከቱ ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዩኒቨርሲቲዎች፣ኮሌጆች፣ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፤ከአዲስ አበባ ክፍላተ ከተሞች ከገዳማትና አድባራት የተመደቡ ሊቃውንት የአብነት ትምህርት መምህራን፣ሰባክያነ ወንጌል (ላዕካነ ወንጌል) በአጠቃላይ በምክክር ጉባኤው የተሳተፉ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት የሚያስገነዝብ ትምህርታዊ ጥናትና መወያያ ርእሶች ተቀርጸው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ከሥልጠና እስከ ተልዕኮ ማስፈጸም ድረስ ያለውን ሐዋርያዊ ግልጋሎት ውስጣዊውን ገጽታ በዳሰሰ መልኩ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ መስክ በቂ ግንዛቤ ዕውቀትና ችሎታ ባላቸው ሊቃውተ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የቆየውን ልምዳቸውና ዕውቀታቸውን አሁን ላይ ካለው አካሄዳችንና አገልግሎታችን አንጻር የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለሆነው ሁሉ እኔ ማነኝ ብሎ መጠየቅ እስኪያስችል ድረስ በጥናታዊ ጽሑፍ የተደገፈ ትምህርት ተሰጥቷል፤በችግሩም ዙሪያ ያተኮሩ መጠይቆች ተነስተዋል፤ በመምህራኑም በቂ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶናል፡፡ ውይይቱም ሰፊና ጠቃሚ ሐሳብ ማሰባሰብ ያስቻለ ስለሆነና የምክክር ጉባኤው ተካፋዮችም በቅዱስነታቸው የተሰጠንን መመሪያና ቃለ ምእዳን ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተላለፈውን የሥራ አፈጻጸማዊ መመሪያ የጉባኤውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሲመሩት ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ የጉባኤ አመራርና ማብራሪያዎች ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች ከሆኑት ምሁራነ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠንን መመሪያና ከምክክር ጉባኤው ባገኘነው ጠቃሚ ትምህርት መሠረት የሚከተለውን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡ ጉባኤያችን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት የተላለፈውን የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን፣ከብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተሰጠውን የሥራ መመሪያና ጥናት አቅራቢዎች ያቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፎች በሥራ ለማዋል ቃል እንገባለን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከዋናው መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚወጡት ሕጎችና መመሪያዎች፣እንዲሁም ስለ ስብከተ ወንጌልና ትምህርትና ሥልጠና የሚተላለፉትን ትዕዛዞች በየአህጉረ ስብከቱና በቤተ ክርስቲያኗ ተቅዋማት ሁሉ በተግባር እንዲውሉ ቃል እንገባለን፣ እነዚህ መምሪያዎች የቤተ ክርስቲያኗን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ለማሟላት የወሰዱትን የሥራ ተነሳሽነትና ኃላፊነትን በጋራ የመወጣት ልምዳቸው የሚበረታታ ስለሆነ በዚሁ መልኩ ተቀራራቢ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ የሥራ መዋቅር ክፍሎች በጥምር የሚያስፈጽሙበት አሠራር መዘርጋት የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ተልዕኮ ስለሚያማክልና የጉባኤው ተሳታፊዎችም የምንደግፈው ስለሆነ በአፈጻጸም ረገድ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁነታችንን እንገልጻለን፡፡ የአብነት ት/ቤቶች እየተስፋፉ መሆናቸው ግልጽ ነው፤እነሱን ያግዙ ዘንድ የተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆችም በንባብ፣በቅዳሴ፣በዜማና በመጻሕፍት የትምህርት ዘርፍ እያደጉ የሚገኝበት ወቅት ስለሆነ ተመርቀው የወጡት ደቀ መዛሙርትም ከዋናው ማእከል ጀምሮ በየአህጉረ ስብከቱና ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቅዋማት በአገልግሎትና በኃላፊነት የሚገኙበት ወቅት ላይ መድረሳችን የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገቷን የሚያሳይ በመሆኑ አሁንም በየጊዜው በጥናት የተደገፈ ሥልጠና በመስጠት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችን አስተዋጽኦ ለመወጣት ዝግጁነታችንን እንገልጻለን፡፡ ቋሚ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት ለማጠናከር፤የመምህራንና የደቀ መዛሙርትን ኑሮ ለመደገፍ በየአካባቢው በየአህጉረ ስብከቱ በቂ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ዘገባዎች ቢያመለክቱም በውስጣዊ የአመራርና ውጫዊ ሁኔታዎች አንዳንድ ችግሮች የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መምህራንን ለፍልሰት እያደረጉ ስላሉ ለወደፊቱ መምህራኑ በየአካቢያቸው ወንበራቸውን አጽንተው ደቀ መዛሙርቶቻቸውን በሁለንተናዊ ስብእና ክብር አስታጥቀው እንዲያወጡ በመሥራት የበኩላችንን አደራና ኃላፊነት እንወጣለን፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ትምህርት ዜማ፣ቅዳሴና ቅኔና ትርጓሜ መጻሕፍት የሚማሩ ደቀ መዛሙርት ለትምህርተ ወንጌልበአርያነት ለሚጠቀስ ለመንፈሳዊ አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ጊዜውን የዋጀ መምህራን ለማግኘት የሥርዓተ ትምህርት ዳሰሳዊ ጥናት የቤተ ክርስቲያኗን ባለሙያዎችና ሌሎች አጋዥ ኃይሎች በማሳተፍ እንዲቀርብ በተደጋጋሚ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነ ስለሆነ እነዚህ ሁለቱም መምሪያዎች ሆኑ ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ተባብረውበት ማኅደረ ጉዳዮች ታይተው የቀሩትን ተግባራት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ምንጊዜም ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ያላቋረጠች መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷም በውጭው ዓለም በሚገኙ ክፍላተ ዓለማት ጭምር መስፋፋቷ በእግዚአብሔር ረድኤት እየቀጠለ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያኗ ወገኖች የሆን ውሉደ ክህነትና ውሉደ ክርስቲያን ለሐዋርያዊ ተልዕኮዋ መፋጠን የእምነት ተከታዮቿንም ምእመናን ለመጠበቅ የጋራ አሠራር በያዘ መልኩ በውስጣዊና ውጫዊ አሠራራችንና ግንኙነታችን ሁሉ ከመምሪያዎቹም የሚተላለፉ የሥራ መርሐ ግብሮችን ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት የሰጠውን ታላቁን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተቀብላ በሐዋርያት አሠረ ፍኖት ተገብታ በባለቤትነት ታስፈጽማለች። ነገር ግን ከእኛ ከአገልጋዮች የእውቀት እና የቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም ከአንዳንዶቻችን ጥቅም ተኮር እንቅስቃሴ የተነሳ ይህንን ታላቅ ተልእኮ ለመፈጸም የተቸገርን ቢሆንም ከዚህ በኋላ በተቻለን መጠን ለመማር፣የተማርነውን ለማስተማር ፣ለማሳመን፣ ከመንጋው ለመቀላቀልና ለመንከባከብ በሚደረገው ማንኛውም ጥረት ከቤተክርስቲያን ጎን ለመቆም ቃል እንገባለን። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገራችን ለዘመናት ሃይማኖትንና ታሪክን ስታስተምርና ስትዘግብ ብራና ዳምጣ፣ቀለም በጥብጣ፣የራሷን ፊደል ቀርጻ፣ የራሷን ቀመር ቀምራ ለቁጥር የሚያዳግቱ መጻሕፍትን ጽፋለች፤ እየጻፈችም ነው። ነገር ግን አባቶቻችን የጻፏቸው መጻሕፍት በየገዳማቱ ግምጃ ቤት ሆነው ለጉብኝት አገልግሎት ከመዋል ባሻገር ለጥናትና ምርምር ክፍት ተደርገው ለማኅበረሰቡ መድረስ ባለመቻላቻው በዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ወገኖች ቤተክርስቲያንን መጻሕፍት አልባ ከማስመሰሉም በላይ የትምህርት ተቋማቶቻችን የአባቶቻችን ወዝ ባልካቸው መጻሕፍትና ታሪክ አልባ ተሞልተዋል የሚል ስሞታ እንዳለ ተገልጿል፤በመሆኑም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያን ለምታደርገው ጥረት ጥናትና ምርምር በመሥራት በሁሉም ዘርፍ ከቤተክርስቲያን ጎን ለመቆም ቃል እንገባለን። ቅድስት ቤተክርስቲያን የሁሉ እናት እንደመሆኗ መጠን ዘር ቀለም ጎሳ ሳትለይ እናቴ ብሎ የመጣውን ሁሉ አቅፋ የያዘች፣ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ከመሆኗ ባሻገር የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምታቀብል መሆኗ የሚታወቅ ነው፤ነገር ግን ከላይ እስከታች የምንገኝ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በጠረፋማ ሥፍራ የሚኖሩ ሰዎችን ወንጌል ለማስተማር የምናደርገው ጥረት ጅምሩ የሚበረታታ ቢሆንም ፍጹም ሥራ መሥራትን፣ ለሌሎች ዓለማትም መትረፍን የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን በጉባኤው ከተሰጠው ዐውደ ጥናት ተረድተናል፤ በመሆኑም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሁሉ እናትነት መላልሶ ለማስተማርና ለመላላክ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል እንገባለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ

የአቋም መግለጫ Read More »

“ራሳችንን ለወንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል” ሲሉ ‎ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ፡፡

“ራሳችንን ለወንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል” ሲሉ ‎ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ፡፡ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው በሁለተኛ ቀን የምክክር ጉባኤ ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “‎ይህ ሁሉ ሊቃውንት እያለ ቤተክርስቲያን መቸገር የለባትም ለዚህም ራሳችንን ማዘጋጅት ይጠብቅብናል፡፡ በዘር፣ በጎሣ መከፋፈል ለቤተክርስቲያን አይጠቅማትም፣ ራሳችንን ለውንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል ቀናነት እና ታዛዥነት የመጀመሪያ ተግባራችን መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ ‎የመቄዶንያን የበጎ አደራጎት ማኅበር መሥራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ስለ ማኅበሩ አሁናዊ ሁኔታ ገልጸዉ ሁሉም ሰው የአቅሙን ርዳታ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‎ክቡር ዶ/ር ቢኒያም በለጠ አያይዘውም እንዳሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የአየር ሰዓት በመስጠት እያገዝን ስለሆነ በድርጅታችን ስም ምስጋና እናቀርባለን ብልዋል፡፡ መርሐ ግብሩ ላይ ‌‎የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከገዳማትና ከአድባራት የተወጣጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተገኝተዋል፡፡ ©EOTCTV

“ራሳችንን ለወንጌል አሳልፈን መስጠት ይገባናል” ሲሉ ‎ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ገለጹ፡፡ Read More »

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመሆን የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ።

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመሆን የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ። በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋህዶ አዳራሽ “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመቀናጀት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ። ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል። መርሐ ግብሩም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎተ ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን ቅዱስነታቸውም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ቤተ ክርስቲያን የምትጠበቀው በካህናትና በምዕመናን ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም ቤተ ክርስቲያንን እና ሃይማኖታችንን ለመጠበቅ እየተሰበሰቡ መመካከር አስፈላጊ ነው ብለዋል። ወቅታዊውን የበሀገራችንን ሁኔታንም በማስታወስ አሳሳቢነቱን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ለዚህም ቤተክርስቲያንን ጠንክረን መጠበቅ አለብንም ሲሉ መክረዋል። ይህችን ቤተ ክርክቲያን የሚቃረኗት ብዙ መሆናቸውንም ጠቅሰው ለዚህም ሁላችሁም ኃላፊነታችሁን ለመወጣት መሰል ጉባኤያት አስፈላጊም ኃላፊነትም ነው ሲሉ ቤተ ክርስቲያንን ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚያሻ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ሐዋርያትን በዓለም ዞረው ወንጌልን መስበካቸውን ጠቅሰው የሐዋርያትን ፈለግ የተከተለችው ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ ከመናፍቃን ጋር ያደረገችውን ተጋድሎም አንስተዋል።ለዚህም በዋቢነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጉባኤያትን አንስተው አርዮስን፣መቅዶንዮስ እና ንስጥሮስን አውግዛ መለየትዋን ገልጸዋል። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋ ወንጌልን ተደራሽ ማድረግ እና ተልዕኮዋን እንዳትወጣ የሚያደርጓትን ችግሮችን መቅረፍ እና አውግዞ መለየት ነውም ሲሉ አክለዋል። “ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ የስብከተ ወንጌልን እና የአብነት ትምህርትን ለማስፋፋት ያለመ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ ዋና ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚ አሰፋ ሲሆኑ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ መርሐ ግብሩ በጥምረት መዘጋጀቱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንስተዋል። ሁለቱም መምሪያዎች ቀደምት መሆናቸውንም ጠቅሰው ምንም እንኳ የተለያየ የሥራ ዘርፍ ቢኖራቸውም በስብከተ ወንጌል ረገድ ያላቸውን አንድነትም አብራርተዋል። በመሆኑም ከወርሐ መጋቢት ጀምረው በጥምረት መስራት መጀመራቸውን ገልፀው ሊሰሩ ያሰቧቸውንም ዘርፈ ብዙ የሥራ መስኮችም በዝርዝርና በቁጥር አቅርበዋል። መላከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለ ፅድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያም በበኩላቸው ጉባኤው ውጪያዊውን ችግሮች ለመፍታት የተዘጋጀ ሳይሆን ውስጣዊ ችግሮችን ለማየት እና ለመፈተሽ የተዘጋጀ ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል። መላከ ሰላም “መንፈሳዊነት ለሁለንተናዊ አገልግሎት” በሚል ርዕስም ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናታዊ ጽሑፋቸውም የመንፈሳዊነትን ምንነት ዳሰዋል። ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠው ትምህርት ትውፊታዊ መሆኑንም የጠቀሱ ሲሆን ያ ወንጌል ቀለም ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊነትንም የያዘ እና እኛም የወረስነው ነው ሲሉ መንፈሳዊነትን በተለያየ መልክ አብራርተዋል። በመጨረሻም በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፍ ዙሪያ ሰፊ ሀሳብ እና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን በዋናነት በመምህራን ረገድ ያለው የእውቀት ክፍተት እና የመንፈሳዊነት ዝለት ተነስቷል። መርሐ ግብሩ በቀጣይም በየዓመቱ የሚዘጋጅ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በከሰዓቱም ውሎም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት ሲሆን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤተ መጽሐፍትና ወመዘክር ጉብኝት የሚቋጭ መሆኑ ታውቋል። በዕለቱም ብፁዓን አበው ላቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፤የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። መርሐ ግብሩ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ ሲሆን በነገው ዕለትም ቀጥሎ ይውላል። ©EOTC TV

“ዝክረ ወንጌል ወዝክረ ሊቃውንት”በሚል መሪ ቃል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ከትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያዎች ጋር በመሆን የሁለት ቀናት የምክክር ጉባኤ አዘጋጀ። Read More »

Scroll to Top