በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Admin

ጾመ ፍልሰታ/ጾመ ማርያም/

ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፤ተሰደደ፤ተጓዘ፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ «ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ፤ ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ከምድር ሕይወት ወደ ሰማያዊ ሕይወት፣ ተሻገረች» በማለት ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጓሜ አመሥጥሮ ገልጾታል፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የዕረፍት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እመቤታችን በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመታትን በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጌታችን የእናቱን ተድላ ነፍሷን እንጂ ተድላ ሥጋዋን አይወድምና ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓመተ ምሕርት አረፈች፡፡ ዕረፍቷም እንደሌላው ሰው በሕማምና በድካም አይደለም፡፡ በገነት ዕፀዋት መዓዛ ተመስጣ ቅድስት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታለች፡፡ ታሪኩ በነገረ ማርያም እንደተጻፈው ሐዋርያት እመቤታችንን በአጎበር አድርገው አክብረው ወደጌቴሴማኒ መካነ መቃብር ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉም ነበርና ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩ ኖረዋል፤ እርሷን ደግሞ ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን ነውና «ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው» ብለው በምቀኝነት ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ ሄዶ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የታዘዘ መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፡፡ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ የምሕረት እናት የሆነችው ድንግል ማርያም ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ እጆቹን እንዲመልስለት ነግራው እንደነበረ አድርጎለታል፡፡ የእመቤታችን ሥጋዋን መላእክት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ወስደው አስቀምጠውታል፡፡ ሥጋዋ ያለበትን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እነርሱ ባለማየታቸው እመቤታችን ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ባለው መቃብር ቀብረውታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ ልጇ በ፫ኛው ቀን ተነሥታ መላእክት እየዘመሩላት ወደሰማያት ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሰ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ከደመናው ሊወድቅ ወደደ» ምክንያቱም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ፤ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ለማየት ብሎ ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጥታ አጽናንታ ሰደደችው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ ብሎ ጠየቃቸው፤እነርሱም አግኝተው እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ይህ እንዴት ይሆናል?»፤ ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ተደናግጠው ተያዩ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችን ተነሣች፤ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡ በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሐዋርያት በመንፈሰዊ ቅናት ተነሳስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው በ፲፮ኛው ቀን የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዔ ዲያቆን አድርጉ ቀድሶ አቅርቧቸዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ጾመ ፍልሰታ ተብሎ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾመዋል፡፡ የጾሙና የትንሣኤዋ በረከት ተካፋይ ያድረገን፤አሜን።

ጾመ ፍልሰታ/ጾመ ማርያም/ Read More »

የአባ ገሪማ መልዕክት  

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን! በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፤ በሀገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምዕመናን ወምዕመናት በቸርነቱ እና በረድዔቱ ብዛት በዕድሜያችን ላይ ይህችን ዓመት ጨምሮ ለ2017 ዓ.ም ለጾመ ማርያም እንኳን በሰላም አደረሳችሁ! ጾመ ፍልሰታ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከ፯ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት ከእመቤታችን መለየታቸው እጅግ አሳዝኗቸው በነበረበት ጊዜ የጾሙት ጾም ነው። በጾማቸው እመቤታችንን አግኝተውበታል። ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ጾመ ፍልሰታ ሕጻኑም አረጋዊውም ጠንካራውም ደካማውም ወንዱም ሴቱም ሁሉም የሚጾሙት ጾም እንደሆነና ከሌላው ጊዜ በተለየ የሱባኤ ወቅት መሆኑ ይታወቃል። ይኸውም ምዕመናን በጾሙ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድዔት በረከት እንደሚገኝበት እመቤታችን የልባችንን መሻት እንድትፈጽምልን የምንማጸንበት ወቅት መሆኑን በመረዳት ነው። “ጾም ቅድስት ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ተመጠወ ሙሴ ሕገ እግዚአብሔር ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ኤልያስ ዓርገ ውስተ ሰማያት ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ዳንኤል ድኅነ እምአፈ አናብስት ጾም ቅድስት ሶስና ድኅነት እምዕደ ረበናት ጾም ቅድስት ዓቀመ ኢያሱ ፀሐየ በገባዖን ጾም ቅድስት ጳውሉስኒ ይቤ ትግሁ እንከ አኃውየ በጾም ወበጸሎት ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ጾም ቅድስት ትሚህሮሙ ለወራዙት ጽሙና። ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች፡፡ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት በዚህች የተቀደሰችዋ ጾም ሙሴ የአምላኩን ሕግ ተቀበለባት፤ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት:  በዚህች ቅድስት ጾም ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገባት በዚህች ቅድስት ጾም ዳንኤል ከአንበሶች አፍ ዳነባት፣ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት:: በዚህች ቅድስት ጾም ሶስና ከመምህራኑ ክስ ተርፋለች፣ በዚህች ቅድስት ጾም ኢያሱ በገባዖን ፀሐይን አቆመ ። ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት! ጳውሎስ እንዲህ አለ “እንግዲህ ወንደረሞቼ በጾምና በጸሎት ትጉ”፣ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት። በዚህች በተቀደሰችዋ ጾም … ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ፍትሐ ነገስት በአንቀጽ 15፣598 ላይ “ወአኮ ጾም እምኀብስት ወማይ አላ ጾምሰ ዘውኩፍ ቅድመ እግዚአብሔር ንጽሐ ልብ – ጾም ከእህል ከውሃ መከልከል ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሚቀበለው ጾም የልብ ንጸሕና ናት” እንደሚለን እኛም ይህንን ጾም ጾመን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድዔት በረከት ለማግኘት የልብ ንጽህናን ገንዘብ ማድረግ ዋናው ቅድመ ሁኔታ ነው። በዚህ ጾም በቤተ ክርስቲያናችን በተለየ መልኩ ሶርያዊ ለብሐዊ የተባለ ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው የእመቤታችን ውዳሴዋ (ውዳሴ ማርያም) እንዲሁም የብሕንሳው ኤጴስ ቆፅስ አባ ሕርያቆስ የደረሰው የእመቤታችን ቅዳሴ (ቅዳሴ ማርያም) ይተረጎማል። በዚህ ጊዜ እንዲሁም በሌሎቹም በቤተ ክርስቲያን በሚሰጡ መንፈሳዊ አገልግሉቶች በሰዓታት፤ በኪዳን፤ በቅዳሴ፤- በሚሰጠው  የስብከተ- ወንጌል አገልግሎት ላይ እየተገኘን አገልግሎቱን እየተሳተፍን ቸሩ አምላካችን ለሀገራችን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ፍጹም ሰላምን እንዲሰጣት እና ከእመቤታችን በረከት ረድዔት እንዲያሳትፈን ልንጸልይ ይገባል እያልን አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። በመጨረሻም በቅድስና በንጽሕና በተሰበረ ልብ ሆነን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት፤ የልቡናችን መልካም መሻት የሚፈጸምበት፤ ኃይለ አጋንንት ወድቆልን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ የሚቀርብን የበረከት ጾም ያድርግልን። ጾሙን የሰላም የፍቅር የበረከት ጾም አምሳካችን ልዑል እግዚአብሔር ያድርግልን። እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክልን!!! አባ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ

የአባ ገሪማ መልዕክት   Read More »

ለገጠር አብያተክርስቲያናት የንዋየ ቅድሳት ድጋፍ ተደረገ!!

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ለሚገኙ፦ #ለቡርጂ ወረዳ ቤተክህነት #ለኮሬ ወረዳ ቤተክህነት #ለቡሌና ረጴ ወረዳ ቤተክህነት #ለይርጋጨፌ ወረዳ ቤተክህነት ለሚገኙ ገጠር አብያተክርስቲያናት የሚሆን የተለያዩ ንዋየ ቅድሳት መቀደሻ አልባሳት፣ ዣንጥላ፣ ዕጣን፣ ጧፍ ፣ቅዱሳት መጽሐፍት፣ መጎናጸፊያ ፣መጋረጃ፣ ጽና፣ መስቀል ፣ጽዋ ለአራቱም ወረዳ ቤተክህነት ኃላፊዎች ከሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤና የሰ/ት/ቤት ማደራጃ ክፍል ኃላፊ ከመልአከ ብርሃን ዳንኤል ነቢዩ ተረክበዋል። የየወረዳ ኃላፊዎችም የተረከቡትን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አብያተክርስቲያናት የሚያደርሱ ይሆናል። በቀጣይም በሀገረ ስብከቱ ለሚገኙ ገጠር አብያተክርስቲያናት የሚያስፈልጉ ንዋየ ቅድሳትን ለማሟላት ድጋፋችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንጠይቃለን ።

ለገጠር አብያተክርስቲያናት የንዋየ ቅድሳት ድጋፍ ተደረገ!! Read More »

ስድስተኛው ዙር የወጣቶች መርሃግብር ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ በተገኙበት ተካሄደ!!

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ከተማ በብፁዕ አቡነ ገሪማ በሀገረ ስብከቱ ጳጳስና በቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሚመራው ወርሃዊው የወጣቶች መርሃግብር ስድስተኛ ዙር ብፁዕነታቸው በተገኙበት ተካሂዷል። መርሃግብሩ የተመራው መምህር በላይ ሁንደራ ሲሆን ዝማሬ በዘማሪት ሰላም ዘሪሁን እና በዘማሪት ሰላም ሀብታሙ ቀርቧል። እንዲሁም በወጣት ኪሩቤል አሰፋ እና በወጣት እርቅይሁን ደመላሽ ግጥም ቀርቧል። መጋቤ ሀዲስ መልአክ አማረ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል የመጻሕፍት መምህር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈው በሁለተኛው መልእክቱ ፪ኛ ጢሞ ፫፥፲፬ ላይ የሚገኘውን “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና” የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ወጣቶች ውሏቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው፣ በቤተ ክርስቲያን በተማሩበት ትምህርት በአሚነ ሥላሴ ጸንተው መኖር እንዳለባቸው በሰፊው አስተምረዋል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ ወጣቶቹ ወደዚህ መርሃግብር (ወደ ቤተ ክርስቲያን) ሲመጡ ሌሎቹንም በመጋበዝ፣ ወጣቶች በማይመጥናቸው በአልባሌ ሥፍራ ላይ መገኘት እንደሌለባቸው እንዲሁም ራሳቸውን ከሱስ መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸው ስለሱስ አስከፊነት በሰፊው ተናግረው በቀጣይ ሊሰሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮች አባታዊ መመሪያ ሰጥተው መርሃግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል። የሚቀጥለው ወር የሚውለው ነሐሴ 25/2017 ዓ.ም ነው።

ስድስተኛው ዙር የወጣቶች መርሃግብር ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ በተገኙበት ተካሄደ!! Read More »

ለስምንት ወራት የተማሩ ደቀመዛሙርት በብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ ተመረቁ!!

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በሀገረ ስብከቱ በተቋቋመው በአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የተማሩ የአብነት እና የተለያዩ መሠረታዊ ትምህርትና ሥልጠና የወሰዱ ከ5ት ወረዳ ቤተክህነት የተወጣጡ 5ት ደቀመዛሙርት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተመረቁ። በምርቃ መርሐ ግብር ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ደቀመዛሙርት የተሸለሙ ሲሆን የተለያዩ መጻሕፍት ከማህበረ ቅዱሳን ተሰጥቷቸዋል።በተጨማሪ ያለ ምንም ክፍያ ለስምንት ወራት ያስተማሩ መምህራን በብፁዕነታቸው ተመስግነዋል ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። የደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት መዘምራን መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ተመራቂ ደቀመዛሙርትም ያሬዳዊ ወረብና ግጥም አቅርበዋል ። ስለ ተመራቂ ደቀመዛሙርት አጠቃላይ ቆይታ በቀሲስ ጤናው እንዳለማው ቀርቧል። አጠቃላይ አጭር ስለ አብነት ት/ቤቱ ሪፖርት በመልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ የሀገረ ስብከቱ የትምህርትና የካህናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ገልጸዋል ። በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ቃለምዕዳን ያስተላለፉ ሲሆን ደቀመዛሙርት የተሰጣቸውን ተልዕኮ መወጣት ማስተማር እንዳለባቸው አሳስበዋል ።

ለስምንት ወራት የተማሩ ደቀመዛሙርት በብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ ተመረቁ!! Read More »

ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረቴ ገ/ሥላሴ የሻራ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዲሆኑ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተሹመዋል።

በዕለቱም የማስተዋወቅ መርሐ ግብሩን ያከናወኑት የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በሆኑት በመልአከ ብርሃን ቀሲስ አጥናፉ ማሞ የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኗል። በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በመልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ መልካም የሥራና የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸው በመመኘት በጸሎት ተፈጽሟል።

ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረቴ ገ/ሥላሴ የሻራ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዲሆኑ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተሹመዋል። Read More »

በግንባታ ላይ የሚገኘው የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ ጉብኝት ተደረገ!!

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሀገረ ስብከት አቀፍ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች አዲስ ሀገረ ስብከቱ በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚያስገነባውን የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ ጉብኝት አደረጉ። በጉብኝቱ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ፣ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች እና ጸሐፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች በጠቅላላ ጉባኤው የተገኙ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በጉብኝት ስለሕንጻው አሁናዊ ሁኔታ ገለጻ የሰጡት ኢንጅነር አማኑኤል ሲሆኑ ሕንጻው በደረሰበት ደረጃ መደነቃቸውን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። በተጨማሪ በቅጥር ግቢ ውስጥ እየተሰሩ የሚገኙት የግብርና የልማት ሥራዎች የተጎበኙ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ ወደፊት ስለሚሰሩ ሥራዎች ገለጻ አድርገው እንዲሁም ለመጎብኘት ለመጡት እንግዶች ምስጋና አቅርበው ፍጻሜ ሆኗል።

በግንባታ ላይ የሚገኘው የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ ጉብኝት ተደረገ!! Read More »

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የሀገረ ስብከት አቀፍ ፪ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ በደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በማካሄድ ላይ ይገኛል። በመርሃግብሩ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ፣ የሀገረ ስብከቱ የየሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች እና ጸሐፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ሒሳብ ሹም፣ የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ተወካዮች፣ የመንበረ ጵጵስና የልማት ኮሚቴዎች እና የምዕመናን ተወካዮች ተገኝተዋል። መርሃግብሩን ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ ጸሎተ ወንጌል፣ ኪዳን በማድረስ በጸሎት የከፈቱ ሲሆን ቀጥለውም የመርሃ ግብሩን መጀመር በይፋ አብስረዋል። በመርሃግብሩ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ የአንድ ዓመት የሥራ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርታቸው በሀገረ ስብከቱ በአገልጋይ እጥረት ምክንያት የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት በማይሰጥባቸው አብያተ ክርስቲያናት ከምእመናን በተሰበሰበ 1,116,000 ገንዘብና እርዳታ ለአንድ ዓመት ለ፮ ካህናት ደሞዛቸውን ችሎ አብያተ ክርስቲያናቱ የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንዲሁም በስድስቱ ወረዳ ቤተ ክህነት በቋንቋ ተዘዋውረው የሚሰብኩ ለአንድ ዓመት 21 ደቀመዛሙርት ለ2018 ዓ/ም በጀት ዓመት እንዲሰማሩ ምልመላ ተደርጎ የስምሪት ስልጠና ወስደው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ሥልጣነ ክህነትን በተመለከተ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለ90 ደቀመዛሙርት የዲቁና 16 በአጠቃላይ 106 ሥልጣነ ክህነት መሰጠቱን እንዲሁም በርካታ ኢ-አማንያን በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት ማግኘታቸውን ገልጸዋል። በመርሃግብሩ የወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች የየወረዳ ቤተ ክህነቱን ዓመታዊ የ፩ ዓመት ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርታቸው በሁሉም ወረዳ ቤተ ክህነት 3372 ኢ-አማንያን መጠመቃቸውን ገልጸዋል። የመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በበጀት ዓመቱ 822 ኢ-አማንያን መጠመቃቸውን ገልጸው የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን በተመለከተ፣ መልካም አስተዳደርን፣ ሁለገብ ልማትን፣ የአብነት ትምህርት ቤት እና ዘመናዊ ትምህርት ቤትን፣ ሰንበት ትምህርት ቤትን በተመለከተ (የአንድነት ሰንበት ትምህርት ቤት)፣ የአደባባይ ክብረ በዓላት አከባበርን፣ የቤተ ክርስቲያን ምረቃ፣ የመሰረት ድንጋይ መቀመጥ፣ የጠበል አገልግሎት፣ የማረምያ ቤት፣ የፋይናንስ አያያዝ አስተዳደር፣ ፐርሰንት ክፍያ በተመለከተ እንዲሁም የተሀድሶን ሴራ ስለማጋለጥ የተሰሩ ሥራዎችን ገልጸዋል። የይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት 823 ኢ-አማንያን ማስጠመቃቸውን ገልጸው የብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ከአድባራት አስረዳዳሪዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶችን፣ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የተሰሩ ሥራዎችን፣ በአድባራቱ የተሰሩ ልማቶችን እንደአብነት የግብርና የልማት ሥራዎችን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት እንዲከተሉ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎችን በሰፊው ገልጸዋል። በኮቾሬና ገደብ ወረዳዎች ቤተ ክህነት 273 ኢ-አማንያን መጠመቃቸውን ገልጸው በዕቅድ ዙርያ የተደረገ ውይይት፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት የተሰሩ ሥራዎችን፣ የክህነት አሰጣጥን በተመለከተ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማቋቋም የተሰሩ ሥራዎችን፣ የስብከት ኬላ ማቋቋምን፣ የአቅም ማጎልመቻ ሥልጠናዎችን በተመለከተ፣ የተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናትን መለየትና ማቋቋምን በተመለከተ፣ የንግስ በዓላትን መምህራንን መመደብ መቆጣጠር የመሳሰሉትን ሥራዎች አቅርበዋል። የቡሌና ረጴ ወረዳ ቤተ ክህነት 127 ኢ-አማንያንን ማስጠመቃቸውን ገልጸው በስብከተ ወንጌል፣ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን፣ በሰንበት ትምህርት ቤት የተሰሩ ሥራዎችን፣ በፐርሰንት የተሰሩ ሥራዎችን፣ በአብነት ተማሪዎች ዙርያ የተሰሩ ሥራዎችን ገልጸዋል። የኮሬ ወረዳ ቤተ ክህነት 594 ኢ-አማንያንን ማስጠመቃቸውን ገልጸው የብፁዕ አባታችንን ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ የአገልጋይ እጥረት ያለባቸውን አብያተ ክርስቲያናትን አገልጋይ በመመደብ እንዲሁም ንዋየ ቅድሳትን ሟሟላት፣ ስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት የተሰሩ ሥራዎችን ገልጸዋል። የቡርጂ ወረዳ ቤተ ክህነት 733 ኢ-አማንያንን ማስጠመቃቸውን ገልጸው የብፁዕ ሊቀጳጳሱን ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ስብከተ ወንጌልን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተሰሩ ሥራዎች፣ ሥራዎችን ከማዘመን አንጻር የተሰሩ ሥራዎችን ሪፖርት አድርገዋል።

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል!! Read More »

የቅዱስ ዑራኤል ዓመታዊ በዓል በዲላ ዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ በተገኙበት ተከበረ!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ሐምሌ ሃያ ሁለት ቀን የሚከበረው የመልአኩ የቅዱስ ዑራኤል በዓለ ንግሥ በዲላ ዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። መርሃግብሩ በሀገረ ስብከቱ ትምህርት እና ካህናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ በመልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ የተመራ ሲሆን በደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘምርያን ያሬዳዊ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ ለዕለቱ የሚስማማ ትምህርት በደብሩ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ማእምራን መምህር ሰሎሞን ፈጠነ ተሰጥቷል። የደብሩ የግብርና የልማት ሥራ እንዲጠናከር ትልቅ ሥራ ላደረጉ ለአባ ገብረ አረጋዊ ረታ እና ለዲያቆን አምራች ገብረ ሥላሴ የምስጋና ስጦታ እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የደብሩ የልማት ሥራ እንዲፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ላደረጉ ሰዎች ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ሁሉም አድባራት የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ አብያተ ክርስቲያናቱ ወደ አምራችነት ለማሳደግ እየተሰራ ያለውን ሥራ ገልጸው እንዲሁም በዓለ ንግሡን በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት መርሃግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል።

የቅዱስ ዑራኤል ዓመታዊ በዓል በዲላ ዋለሜ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ በተገኙበት ተከበረ!! Read More »

Scroll to Top