በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

ስድስተኛው ዙር የወጣቶች መርሃግብር ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ በተገኙበት ተካሄደ!!

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ከተማ በብፁዕ አቡነ ገሪማ በሀገረ ስብከቱ ጳጳስና በቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሚመራው ወርሃዊው የወጣቶች መርሃግብር ስድስተኛ ዙር ብፁዕነታቸው በተገኙበት ተካሂዷል።

መርሃግብሩ የተመራው መምህር በላይ ሁንደራ ሲሆን ዝማሬ በዘማሪት ሰላም ዘሪሁን እና በዘማሪት ሰላም ሀብታሙ ቀርቧል። እንዲሁም በወጣት ኪሩቤል አሰፋ እና በወጣት እርቅይሁን ደመላሽ ግጥም ቀርቧል።

መጋቤ ሀዲስ መልአክ አማረ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል የመጻሕፍት መምህር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈው በሁለተኛው መልእክቱ ፪ኛ ጢሞ ፫፥፲፬ ላይ የሚገኘውን “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና” የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ወጣቶች ውሏቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው፣ በቤተ ክርስቲያን በተማሩበት ትምህርት በአሚነ ሥላሴ ጸንተው መኖር እንዳለባቸው በሰፊው አስተምረዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ ጳጳስ ወጣቶቹ ወደዚህ መርሃግብር (ወደ ቤተ ክርስቲያን) ሲመጡ ሌሎቹንም በመጋበዝ፣ ወጣቶች በማይመጥናቸው በአልባሌ ሥፍራ ላይ መገኘት እንደሌለባቸው እንዲሁም ራሳቸውን ከሱስ መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸው ስለሱስ አስከፊነት በሰፊው ተናግረው በቀጣይ ሊሰሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮች አባታዊ መመሪያ ሰጥተው መርሃግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል።

የሚቀጥለው ወር የሚውለው ነሐሴ 25/2017 ዓ.ም ነው።

Scroll to Top