በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን!
በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት፤ በሀገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምዕመናን ወምዕመናት በቸርነቱ እና በረድዔቱ ብዛት በዕድሜያችን ላይ ይህችን ዓመት ጨምሮ ለ2017 ዓ.ም ለጾመ ማርያም እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!
ጾመ ፍልሰታ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከ፯ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት ከእመቤታችን መለየታቸው እጅግ አሳዝኗቸው በነበረበት ጊዜ የጾሙት ጾም ነው። በጾማቸው እመቤታችንን አግኝተውበታል።
ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ጾመ ፍልሰታ ሕጻኑም አረጋዊውም ጠንካራውም ደካማውም ወንዱም ሴቱም ሁሉም የሚጾሙት ጾም እንደሆነና ከሌላው ጊዜ በተለየ የሱባኤ ወቅት መሆኑ ይታወቃል። ይኸውም ምዕመናን በጾሙ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድዔት በረከት እንደሚገኝበት እመቤታችን የልባችንን መሻት እንድትፈጽምልን የምንማጸንበት ወቅት መሆኑን በመረዳት ነው። “ጾም ቅድስት ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ተመጠወ ሙሴ ሕገ እግዚአብሔር ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ኤልያስ ዓርገ ውስተ ሰማያት ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ዳንኤል ድኅነ እምአፈ አናብስት ጾም ቅድስት ሶስና ድኅነት እምዕደ ረበናት ጾም ቅድስት ዓቀመ ኢያሱ ፀሐየ በገባዖን ጾም ቅድስት ጳውሉስኒ ይቤ ትግሁ እንከ አኃውየ በጾም ወበጸሎት ዛቲ ጾም ቅድስት ወበይእቲ ጾም ጾም ቅድስት ትሚህሮሙ ለወራዙት ጽሙና። ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች፡፡ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት በዚህች የተቀደሰችዋ ጾም ሙሴ የአምላኩን ሕግ ተቀበለባት፤ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት: በዚህች ቅድስት ጾም ኤልያስ ወደ ሰማይ ዐረገባት በዚህች ቅድስት ጾም ዳንኤል ከአንበሶች አፍ ዳነባት፣ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት:: በዚህች ቅድስት ጾም ሶስና ከመምህራኑ ክስ ተርፋለች፣ በዚህች ቅድስት ጾም ኢያሱ በገባዖን ፀሐይን አቆመ ። ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት! ጳውሎስ እንዲህ አለ “እንግዲህ ወንደረሞቼ በጾምና በጸሎት ትጉ”፣ ጾም የተለየችና የተቀደሰች ናት። በዚህች በተቀደሰችዋ ጾም … ቅድስት ጾም ለወጣቶች እርጋታ ዝምታን ታስተምራቸዋለች” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ፍትሐ ነገስት በአንቀጽ 15፣598 ላይ “ወአኮ ጾም እምኀብስት ወማይ አላ ጾምሰ ዘውኩፍ ቅድመ እግዚአብሔር ንጽሐ ልብ – ጾም ከእህል ከውሃ መከልከል ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሚቀበለው ጾም የልብ ንጸሕና ናት” እንደሚለን እኛም ይህንን ጾም ጾመን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድዔት በረከት ለማግኘት የልብ ንጽህናን ገንዘብ ማድረግ ዋናው ቅድመ ሁኔታ ነው።
በዚህ ጾም በቤተ ክርስቲያናችን በተለየ መልኩ ሶርያዊ ለብሐዊ የተባለ ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው የእመቤታችን ውዳሴዋ (ውዳሴ ማርያም) እንዲሁም የብሕንሳው ኤጴስ ቆፅስ አባ ሕርያቆስ የደረሰው የእመቤታችን ቅዳሴ (ቅዳሴ ማርያም) ይተረጎማል። በዚህ ጊዜ እንዲሁም በሌሎቹም በቤተ ክርስቲያን በሚሰጡ መንፈሳዊ አገልግሉቶች በሰዓታት፤ በኪዳን፤ በቅዳሴ፤- በሚሰጠው የስብከተ- ወንጌል አገልግሎት ላይ እየተገኘን አገልግሎቱን እየተሳተፍን ቸሩ አምላካችን ለሀገራችን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ፍጹም ሰላምን እንዲሰጣት እና ከእመቤታችን በረከት ረድዔት እንዲያሳትፈን ልንጸልይ ይገባል እያልን አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም በቅድስና በንጽሕና በተሰበረ ልብ ሆነን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት፤ የልቡናችን መልካም መሻት የሚፈጸምበት፤ ኃይለ አጋንንት ወድቆልን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ የሚቀርብን የበረከት ጾም ያድርግልን። ጾሙን የሰላም የፍቅር የበረከት ጾም አምሳካችን ልዑል እግዚአብሔር ያድርግልን።
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክልን!!!
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ