የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ፲፭ ደቀ መዛሙርትን ቅዳሜ ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ዓ/ም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትየ፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዌ በደማቅ ሥነሥርዓት አስመርቋል።
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከትና የሀዋሳ ታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ በዚሁ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት በዛሬው ዕለት የተመረቃችሁ ደቀ መዛሙርት በምትሰማሩበት ሁሉ ማስተዋልና ጥበብን በመከተል ወደ ዓለም ዳስቻ ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ስበኩ የሚለውን የወንጌሉን ቃል በመከተልና በመተግበር እንድታገለግሉ አደራ በማለት አገልግሎታችሁ ሁሉ ውጤታማና የተሳካ ይሆን ዘንድ አምላካችን እግዚአብሔርን እንለምናለን ብለዋል።
በማያያዝም ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን የትምህርት እድል እንዲመቻች ያደረገችው ዶግማ፣ቀኖናዋና ትውፊቷ ተጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ነው። ያሉት ብፁዕነታቸው ዛሬ ለምረቃ የበቃችሁ ደቀ መዛሙርትም ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀትና በየትኛውም ስፍራና ሁኔታ ውስጥ ሁሉ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ ለመወጣት የተዘጋጃችሁ መሆን ይኖርባችኋል። ብለዋል።
ወደ ኮሌጃችን ለመማር ስትመጡ የገባችሁትን ቃል እንዲሁም ዛሬም በዚህ የምረቃ መርሐ ግብር ቤተክርስቲያንን እና ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል የገባችሁት ቃል ኪዳን ባገኛችሁት ዕውቀትና ክህሎት በትጋት እንደ ምትፈጽሙት እምነታችን ጽኑዕ ነው።ያሉት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የኮሌጃችን የመጀመሪያ ምሩቃን ደቀ መዛሙርት ልጆቻችን! በሥራችሁ ሁሉ የምታሳዩት ጥረትና ትጋት እንዲሁም ለሁሉ አርዓያና ምሳሌ በመሆን በምትሰጡት አገልግሎት ቤተ ክርስቲያንን እና የተማራችሁበትን ኮሌጅ የምታስመሰግኑ እንደ ምትሆኑ እምነታችን ነው። መጪው የሥራና የአገልግሎት ዘመናችሁ ሁሉ የተቃና እንዲሆን ዘወትር ጸሎታችን ነው በማለት መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ደቀ መዛሙርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
በኮሌጁ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩትና በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት ደቀ መዛሙርት በሲዳምኛ፣በኦሮምኛ፣በዳውሮኛ፣
በከምባትኛ፣በሃድይኛ፣በጋሞኛ፣በኮይሬኛ፣በጌዲኦኛ፣በከፋኛና በወላይትኛ ቋንቋዎች ማስተማር የሚችሉ በመሆናቸው በቤተክርስቲያን አገልግሎት ዙሪያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይታመናል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት የእንኳን ደስ አላችሁ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈው መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጠናቋል።




©የኢኦተቤክ ህዝብ ግንኙነት