በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

Uncategorized

የሀገረ ስብከቱ የዳታቤዝ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ቀረበ!!

ኤክቱስ ሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬ እና ቡርጂ ሀገረ ስብከትን አስተዳደራዊ፣ ሐዋርያዊ እና የልማት ተግባራት በቴክኖሎጂ ለማገዝ እየተገነባ ያለው የዳታቤዝ ማኔጅመንት ሥርዓት እጅግ አበረታች በሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። ብፁዕነታቸው ከአዮ ቴክ (AYO TECH) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በመሆን ባከናወኑት የግምገማና የምክክር መርሐ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ መማክርት ጉባኤ አባላት እና የቴክኖሎጂ ድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ይህ የዳታቤዝ ግንባታ ፕሮጀክት በሀገረ ስብከቱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የአዮ ቴክ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን ቦጋለ ቢታኔ በገቡት ቃል መሠረትና ሥራውን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በነፃ አበልጽገው ለማስረከብ ቃል በገቡት መሠረት እየተከናወነ ያለ ሥራ ነው። ይሁን እንጂ ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ በሦስት ወራት ውስጥ ለውይይትና ለሙከራ ዝግጁ መሆኑ ተመልክቷል። የአዮ ቴክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን ቦጋለ ቢታኔ በበኩላቸው፤ ይህንን የዳታቤዝ ዝግጅት እንደ “አሥራት በኩራት” ለቤተ ክርስቲያን በነፃ ለማበርከት እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ በቀረቡት አስተያየቶች መሠረት አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ ቃል ገብተዋል። የጉባኤው ሰብሳቢ ቀሲስ ብሩክ እና የጉባኤው አባላት በበኩላቸው፣ የዳታቤዝ ግንባታው ሀገረ ስብከቱን እንደ አርአያ የሚያስቆጥር መሆኑን ጠቅሰው ለሥራው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። ብፁዕነታቸው እንደገለጹት፤ “የዳታቤዙ መበልጸግና አሁን የደረሰበት ደረጃ ለሀገረ ስብከቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ለቤተ ክርስቲያናችን ጭምር ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ ነው” በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። አክለውም ሥራው በፍጥነት መከናወኑን አድንቀው፣ በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ አባታዊ መመሪያና የአደራ ቃል አስተላልፈዋል። በመጨረሻም መርሃ ግብሩ በብፁዕነታቸው አባታዊ ቡራኬ ተጠናቋል።

የሀገረ ስብከቱ የዳታቤዝ ዝግጅት ሥራ ተጠናቆ ለብፁዕ አቡነ ገሪማ ቀረበ!! Read More »

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከዚህ በታች ባለው፡ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟሉ ካህናትን በብዛት መቅጠር ይፈልጋል!

ኤክቱስ የካቲት 24/2018 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ከዚህ በታች ባለው፡ክፍት የሥራ መደብ መስፈርቱን የሚያሟሉ ካህናትን በብዛት መቅጠር ይፈልጋል! Read More »

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለሰብአዊነት ድጋፍ የሚውል የገንዘብ ልገሳ አደረጉ!

ኤክቱስ የካቲት 24/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገሪማ ​የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለጀመረው “አንድ ብር ለሰብዓዊነት” የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ብፁዕነታቸው ለዘመቻው ስኬት 10,000 (አስር ሺህ) ብር የለገሱ ሲሆን፣ በተጨማሪም 2,000 (ሁለት ሺህ) ብር በመክፈል የማኅበሩ የዕድሜ ልክ አባል ሆነዋል። ​ይህ የገንዘብ ድጋፍ የተበረከተው የጌዴኦ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለአንድ ወር የሚቆይ የሀብት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው። ብፁዕነታቸው በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት እንዲህ ያሉ ሰብአዊ ተግባራት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ያላቸውን ፋይዳ በማብራራት ማኅበሩ እያከናወነ ያለውን ተግባር እንደሚያደንቁ ገልጸዋል። ​በተጨማሪም ብፁዕነታቸው በመላው በጌዴኦ ዞን የሚገኙ ሁሉም በዚህ የበጎ አድራጎት ጥሪ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል። ድጋፉ የተቸገሩ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግና ሰብአዊ ቀውሶችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ብፁዕነታቸው አስገንዝበዋል።

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለሰብአዊነት ድጋፍ የሚውል የገንዘብ ልገሳ አደረጉ! Read More »

ብፁዕ አቡነ ገሪማ በምሥራቅ አርሲ የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ!

ኤክቱስ የካቲት 22/2018 ዓ.ም “ወተዓገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት – ስለመንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ” ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ​በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ኦርቶዶክሳውያን በታጣቂዎች በግፍ መገደላቸውን እና ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ስንሰማ እጅግ ከፍተኛ ኀዘን ተሰምቶናል። ​ቀደም ሲልም በዚሁ ዞን በኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚፈጸመውን ግድያ በመቃወም የኀዘን መግለጫ መስጠታችን የሚታወስ ቢሆንም ድርጊቱ ዛሬም በባሰ ሁኔታ ተደግሞ ንጹሐን ደማቸው መፍሰሱ እጅግ የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ነው። በመሆኑም በሀገረ ስብከቱ በተለያዩ ጊዜያት በኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመውና የተፈጸመው ዘግናኝና እጅግ አሳዛኝ ግድያዎች የኦርቶዶክሳዊያን ልጆቻችንን በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በነጻነት የመኖርና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የመፈጸም መብትን የሚጋፋ በመሆኑ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ መከታተልና የማያዳግም መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው እያሳሰብን፤ የሚመለከተው አካልም የአካባቢው ችግር ከሥር መሠረቱ እስከሚፈታ ድረስ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እንወዳለን። ​በመጨረሻም በዚህ ዘግናኝና አሳዛኝ ግድያ ሕይወታቸውን ላጡ ልጆቻችን እግዚአብሔር አምላክ መንግሥተ ሰማያትን እንዲያወርስልን እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን የዘወትር ጸሎቷ መሆኑን እንገልጻለን።​እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ! አባ ገሪማየጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስየቅዱስ ሲኖዶስ አባል

ብፁዕ አቡነ ገሪማ በምሥራቅ አርሲ የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ! Read More »

የየካቲት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ በዓል በይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት ተከበረ!

ኤክቱስ የካቲት 16/2018 ዓ.ም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ዓመታዊ የየካቲት ኪዳነ ምሕረት በዓል ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ተከብሯል። ታቦቱ ከመንበሩ ከወጣ በኋላ በደብሩ ኰኵኃ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን ለዕለቱ የሚሆን ትምህርት ቀሲስ ሙሉዓለም ዐባይ የሐዋሳ ደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ አስተምረዋል። በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ ጋባዥነት ብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት በጸሎት ፈጽመዋል።

የየካቲት ኪዳነ ምሕረት ዓመታዊ በዓል በይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ገሪማ በተገኙበት ተከበረ! Read More »

ሀገረ ስብከቱ ለኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት የሞተር ሳይክል ስጦታ አበረከተ!

ኤክቱስ የካቲት 16/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም በ44ተኛው ዓለም አቀፍ ጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ባሳየው ከፍተኛ አፈጻጸም በምድብ 6 ከተካተቱት አህጉረ ስብከቶች መካከል አንደኛ በመውጣት የምስክር ወረቀትና የመቶ ሃምሳ ሲሲ ባለ ሁለት እግር የሞተር ሳይክል መሸለሙ ይታወቃል። ይህንን ሞተር ሳይክል በዛሬው ዕለት ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ ለበኩረ ትጉሃን ቀሲስ አስቻለሁ ገብረ መድኅን ያስረከቡ ሲሆን የበለጠ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

ሀገረ ስብከቱ ለኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት የሞተር ሳይክል ስጦታ አበረከተ! Read More »

የመንበረ ጵጵስና ገቢ ማስገኛ ዕጣ ይፋ ሆነ!

ኤክቱስ የካቲት 16/2018 ዓ.ም የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ለሚያስገነባው የመንበረ ጵጵስና ግንባታ ገቢ ማስገኛ ሎተሪ በዛሬው ዕለት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በዐውደ ምሕረት ይፋ ሆኗል። 1ኛ ዕጣ ሞተር ሳይክል ………180252ኛ ዕጣ ፍሪጅ………………….128753ኛ ቴሌቭዥን…………………..120414ኛ ምስለ ፍቁር ወልዳ…………125215ኛ መጽሐፍ ቅዱስ……………0041406ኛ መዝገበ ጸሎት…………006147 ነው። ዕጣው የደረሳችሁ በሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት በአካል በመቅረብ መውሰድ እንደምትችሉ ተገልጿል።

የመንበረ ጵጵስና ገቢ ማስገኛ ዕጣ ይፋ ሆነ! Read More »

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለአምስት ደቀ መዛሙርት ማዕረገ ዲቁና ሰጡ!

ኤክቱስ የካቲት 16/2018 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት በይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርታቸው ሲከታተሉ ለቆዩ ለአምስት ደቀ መዛሙርት ማዕረገ ክህነት ሰጥተዋል። በተጨማሪም ለአንድ እናት ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጽመዋል። ብፁዕነታቸው ዲያቆናቱ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት ጠብቀው በትጋት ማገልገል እንዳለባቸው አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።

ብፁዕ አቡነ ገሪማ ለአምስት ደቀ መዛሙርት ማዕረገ ዲቁና ሰጡ! Read More »

ወደ ኦቲልቾ የስብከተ ወንጌል ኬላ በሚደረገው የእግር ጉዞ ላይ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ውይይት ተደረገ!

ኤክቱስ የካቲት 15/2018 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሪነት በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ወደ ኦቲልቾ የስብከተ ወንጌል ኬላ በተዘጋጀው የእግር ጉዞ ላይ ተጓዦች በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል። ውይይቱ በአምስት ምድብ ማለትም የቅዱስ ማቴዎስ፣ የቅዱስ ማርቆስ፣ የቅዱስ ሉቃስ፣ የቅዱስ ዮሐንስና የቅዱስ እስጢፋኖስ ምድብ ተከፋፍሎ ውይይት ተደርጓል። የመጀመርያው ርእሰ ጉዳይ በገጠር አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማጠናከር ምን እንደሚጠበቅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በከተማ የሚገኙ ምዕመናን ወደ ገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ የአገልግሎቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምን ማድረግ እንደሚገባ በተጨማሪም ምዕመናንን መንፈሳዊ ዕውቀት እንዳይኖራቸው የሚያደርጋቸው ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ በሰፊው በመወያየት የተለያዩ ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል።

ወደ ኦቲልቾ የስብከተ ወንጌል ኬላ በሚደረገው የእግር ጉዞ ላይ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ውይይት ተደረገ! Read More »

ልዩ መንፈሳዊ የእግር ጉዞ

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር በሚገኘው የኦቲልቾ የስብከተ ወንጌል ኬላ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሪነት የካቲት 15/2018 ዓ.ም ስለተዘጋጀ ሁላችሁም ምዕመናን በቦታው ተገኝታችሁ የጉዞው ተሳታፊ እንድትሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን! የጉዞ ቀን- የካቲት 15/2018 ዓ.ም ዕለተ ሰንበትየጉዞው ሰዓት – ከጠዋቱ 1:00 ሰዓትመነሻ ቦታ – የአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንመድረሻ ቦታ – የኦቲልቾ የስብከተ ወንጌል ኬላ

ልዩ መንፈሳዊ የእግር ጉዞ Read More »

Scroll to Top