ኤክቱስ ሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም
የጌዴኦ ኮሬ እና ቡርጂ ሀገረ ስብከትን አስተዳደራዊ፣ ሐዋርያዊ እና የልማት ተግባራት በቴክኖሎጂ ለማገዝ እየተገነባ ያለው የዳታቤዝ ማኔጅመንት ሥርዓት እጅግ አበረታች በሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ብፁዕነታቸው ከአዮ ቴክ (AYO TECH) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በመሆን ባከናወኑት የግምገማና የምክክር መርሐ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ መማክርት ጉባኤ አባላት እና የቴክኖሎጂ ድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ይህ የዳታቤዝ ግንባታ ፕሮጀክት በሀገረ ስብከቱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የአዮ ቴክ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን ቦጋለ ቢታኔ በገቡት ቃል መሠረትና ሥራውን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በነፃ አበልጽገው ለማስረከብ ቃል በገቡት መሠረት እየተከናወነ ያለ ሥራ ነው።
ይሁን እንጂ ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ በሦስት ወራት ውስጥ ለውይይትና ለሙከራ ዝግጁ መሆኑ ተመልክቷል።
የአዮ ቴክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን ቦጋለ ቢታኔ በበኩላቸው፤ ይህንን የዳታቤዝ ዝግጅት እንደ “አሥራት በኩራት” ለቤተ ክርስቲያን በነፃ ለማበርከት እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ በቀረቡት አስተያየቶች መሠረት አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ ቃል ገብተዋል።
የጉባኤው ሰብሳቢ ቀሲስ ብሩክ እና የጉባኤው አባላት በበኩላቸው፣ የዳታቤዝ ግንባታው ሀገረ ስብከቱን እንደ አርአያ የሚያስቆጥር መሆኑን ጠቅሰው ለሥራው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ብፁዕነታቸው እንደገለጹት፤ “የዳታቤዙ መበልጸግና አሁን የደረሰበት ደረጃ ለሀገረ ስብከቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ለቤተ ክርስቲያናችን ጭምር ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ ነው” በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። አክለውም ሥራው በፍጥነት መከናወኑን አድንቀው፣ በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ አባታዊ መመሪያና የአደራ ቃል አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም መርሃ ግብሩ በብፁዕነታቸው አባታዊ ቡራኬ ተጠናቋል።
