ኤክቱስ ኅዳር 17/2019 ዓ.ም
በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በገጠራማ ቦታዎች በማኅበረሰቡ በአካባቢ ቋንቋ እንዲያገለግሉ የተሰማሩ ሰባኪያነ ወንጌል የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገም እና የወደፊቱን ማሻሻያ የውይይት መርሐ ግብር ተካሄደ።
በመድረኩ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ፣ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች፣ የስድስቱም ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች እንዲሁም ሰባኪያነ ወንጌል ተገኝተዋል።
ግምገማው ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30/2018 ዓ.ም ባለው አንድ ዓመት በኮንትራት ቅጥር በጌዴኡፋ፣ በኮሪቴና በDASHETE/ቡርጂ ቋንቋዎች የተሰጠውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ያተኮረ ሲሆን በመርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ሀብታሙ አበበ ገለጻ አቅርበዋል።
አገልግሎቱ ወንጌልን ምዕመናን በሚረዱት ቋንቋ ማድረስን፣ በትምህርትና በክትትል የእምነት እድገትን ማጠናከርን እንዲሁም አዳዲስ ተጠማቂዎችንና የተመለሱ ምዕመናንን መደገፍን ዋና ዓላማው ያደረገ መሆኑ ተገልጿል። በግምገማው ሂደት የሰባኪያኑ የግል ራስ-ግምገማ፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች ግብረ መልስ፣ የአድባራት ማረጋገጫና የተመዘገቡ መረጃዎች በጋራ ተፈትሸዋል። አፈጻጸሙ በዕቅድ አዘገጃጀት፣ በስብከት ጥራትና ብዛት፣ በምዕመናን ለውጥ፣ በተደራሽነትና ተሳትፎ፣ በሥራ ሥነ-ምግባር፣ በቅንጅት እንዲሁም በመረጃ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ መስፈርቶች መሠረት መገምገሙ ተመላክቷል።
በተጨማሪም አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋት ሰባኪያነ ወንጌሉ በአገልግሎት ጊዜ የሚያጋጥማቸውን የትራንስፖርት፣ የቁሳቁስ፣ የግንኙነትና የአቅም ተግዳሮቶች እንዲሁም ወደፊት ሊሠሩ በሚገባቸው ሥራዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ሐሳብ ተነስቷል። በመድረኩ የተሻሉ የአገልግሎት ልምዶችን ማስፋትና ያልተዳረሱ አድባራትና መንደሮችን በዕቅድ መሸፈን በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ የተለዩ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችሉ ውሳኔዎችና የቀጣይ የማሻሻያ ዕቅዶች ተቀምጠዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን በንግግራቸው በሀገረ ስብከቱ ወሰን ሥር የሚገኙ እያንዳንዱ ቦታዎች ብዙ መሠራት የሚጠበቅባቸው እና ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ገና እንቅስቃሴ የተጀመረባቸው መሆኑን አንስተዋል። ብፁዕነታቸው አክለውም ሀገረ ስብከቱ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው ሰባኪያኑም ከዚህ በላይ ቢበረቱ ብዙ መሥራት እንደሚቻል አሳስበዋል።
