በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በብፁዕነታቸው የተመራው የሀገረ ስብከቱ ልዑካን ቡድን የሦስተኛ ቀን የመስክ ጉብኝት አካሄደ!

ኤክቱስ ኅዳር 16/2019 ዓ.ም

በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የተመራው የሀገረ ስብከቱ ልዑካን በሦስተኛው ቀን የመስክ መርሃ ግብር በሻራ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም፣ በንቆ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል እና በጎላ ቅዱስ ራጉኤል አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት የመስክ ጉብኝትና ቅኝት አካሂደዋል።

ጉብኝቱ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱን የልማት ሥራዎች፣ አስተዳደራዊ አደረጃጀት፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶችን ነባራዊ ሁኔታ ለመገምገም በተዘጋጀው የመስክ መቃኛ ሰነድ መሠረት ነው።

ልዑካኑ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በተደረገው የመስክ ምልከታና ውይይት የሚከተሉትን ዋና ዋና ሥራዎች የተመለከቱ ሲሆን በሻራ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አዲስ የደወል ቤት፣ ሰፊ የሸንኮራ፣ የባሕር ዛፍ፣ የእንሰት፣ የቡና፣ የእንሰት፣ የከብት እርባታ ሥራዎች ተጎብኝተዋል። በጎላ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የቡና፣ እንሰት፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ የድንጋይ ካባ እና ዕድሳት እየተደረገለት የሚገኘው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተጎብኝቷል። በተጨማሪም በበንቆ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቦለቄ፣ ቡና፣ እንሰት፣ ሸንኮራ እና ባሕርዛፍ ተጎብንቷል።

በመስክ መቃኛ ሰነዱ መሠረት የተከናወነው ይህ ቅኝት የሰበካ ጉባኤውን ክትትልና ድጋፍ፣ የልማት ኮሚቴ አደረጃጀትን፣ የገቢና ወጪ እንቅስቃሴን እንዲሁም የመሠረተ ልማትና የመሣሪያ ዝግጁነት ሁኔታን ለመገምገም ያስቻለ ነው።

ጉብኝቱ የአጥቢያዎቹን የልማት አቅምና ጠንካራ ጎኖች ለመለየት፣ የሚስተዋሉ ችግሮችንና ቀደም ሲል ተጀምረው የቆሙ ሥራዎች ካሉ ምክንያታቸውን በመለየት መፍትሔ ለማመላከት እንዲሁም ለቀጣይ የልማት አቅጣጫ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

Scroll to Top