ኤክቱስ ኅዳር 15/2019 ዓ.ም
በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የተመራ ግብረ ኃይል በትናንትናው ዕለት በዲላ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሰፊ የመስክ ጉብኝት ማድረጋቸው፣ ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አካላትና ከልማት ኮሚቴ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
በዛሬው ዕለት የሁለተኛውን ቀን የመስክ ጉብኝት መርሃግብር የሀገረ ስብከቱ ልዑካን በጪጩ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል፣ በወናጎ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያምና በቆቲ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት ተገኝተው የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የደብሩን የልማት ሥራዎች፣ አስተዳደራዊ አደረጃጀት፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶችን ነባራዊ ሁኔታ ለመገምገም በተዘጋጀው የመስክ መቃኛ ሰነድ መሠረት የተካሄደ ነው።
በመስክ ጉብኝቱ ወቅት አድባራቱ እያከናወናቸው የሚገኙትን የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተመልክተዋል። በተለይም በጪጩ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የእንሰትና የቡና ልማቶች፣ የንብ ቀፎ ሥራዎች እንዲሁም የወፍጮ ቤት ልማት እንቅስቃሴዎች ወዘተ ሥራዎች፣ በወናጎ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቡና፣ የእንሰት፣ የባሕርዛፍ፣ የወተት ላም እርባታ፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ጅምር የአዳራሽ ሥራዎች ወዘተ እንዲሁም በቆቲ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንሰት፣ ቡና፣ ባሕርዛፍ፣ የሸንኮራ አገዳ፣ የከብት ማደለብ ወዘተ ሥራዎች በምልከታው ተቃኝተዋል።
ጉብኝቱ የአድባራቱን የልማት አቅምና ጠንካራ ጎኖች ለመለየት የሚስተዋሉ ችግሮችንና ቀደም ሲል ተጀምረው የቆሙ ሥራዎች ካሉ ምክንያታቸውን ለመፍታት እንዲሁም ለቀጣይ የልማት አቅጣጫ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ እንደሆነ ተጠቁሟል።
