ኤክቱስ ኅዳር 06/2019 ዓ.ም
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት በገርቦታ 02 ቀበሌ በለክቻ ገበያ ሲያካሂድ የቆየውን የሦስት ቀናት መንፈሳዊ ጉባኤ አጠናቋል። ጉባኤው በአካባቢው የሚገኙ ምእመናንን በቋንቋቸው በመንፈሳዊ እውቀት እንዲያገኙ፣ ኦርቶዶክሳዊ ሕብረትን ለማጠናከርና የመንግሥቱን ወንጌል ይበልጥ ለማስፋፋት አልሞ የተዘጋጀ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በጉባኤው ከዚህ ቀደም በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ያልነበሩ ምዕመናን በጉባኤው ባገኙት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ተማርከው አሥራ አምስት ሰዎች ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ ቃል ገብተው ተመዝግበዋል። በዚህም የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መምህር በመመደብ የቅድመ ጥምቀት ትምህርት እንዲሰጣቸው እና ለጥምቀት እንዲያበቋቸው መመሪያ ተሰጥቷል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ የይርጋጨፌ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ጸሐፊ መጋቤ ሃይምኖት ቀሲስ ብዙአየሁ ዳመነ፣ ቀሲስ ሀብታሙ ሮቤ የሀገረ ስብከቱ የጌዴኡፋ ቋንቋ ትርጉም ክፍል ኃላፊ በጌዴኡፋ ቋንቋ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በተጨማሪም ዘማሪ አማረ ደበበ (ዲ/ን)፣ ዘማሪት ባህርነሽ እና ዘማሪ አብርሃም ጥላሁን በዝማሬ ያገለገሉ ሲሆን በዜማ መሣሪያ (በክራር) ደግሞ ዘማሪ ነጋልኝ አጅበዋል።
በጉባኤው እንደተገለጸው ሀገረ ስብከቱ መሰል መንፈሳዊ ጉባኤያትን በገጠራማና ራቅ ባሉ አካባቢዎች በቋንቋቸው አጠናክሮ የመቀጠል እቅድ አለው። የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እስከ ገጠር ድረስ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።
