ኤክቱስ ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት የዕረፍት መታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀው መንፈሳዊ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። ይህ መርሃ ግብር ተግባራዊ ክርስትና በተግባር የታየበት ጉባኤ ሆኖ አልፏል።
በጉባኤው ወቅት መጋቤ ጥበባት መምህር ኤርምያስ እንዳሻው እና መምህር ሙሉዓለም ዐባይ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲሆን በዝማሬ ደግሞ ዘማሪ ዕዝራ ኃይለሚካኤል በአማርኛ ቋንቋ፣ ዘማሪ ጌታሁን ታደሰ እና ዘማሪት የአብሥራ መለሰ በጌዴኡፋ ቋንቋ መንፈሳዊ መዝሙራትን አቅርበዋል። ዘማሪ ኃይለአብ ግርማ ደግሞ በዜማ መሣሪያ ሲያገለግል ቆይቷል።
በጉባኤው ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል እርስ በእርስ ተጣልተው የነበሩ ምዕመናን በብፁዕነታቸው ጥሪ በታማኝነት ወደ ዐውደ ምሕረት በመውጣት እርቅ እንዲፈጽሙ የተደረገበት ይገኝበታል።
በተጨማሪም በሀገራችን ወቅቱን የጠበቀ ዝናም አለመኖሩን ምክንያት በማድረግ በብፁዕነታቸው መሪነት በታቦቱ ፊት ጸሎተ ምሕላ የተደረገ ሲሆን የምሕረት አምላክ ዝናመ ምሕረቱን እንዲልክ በመማጸን ጸሎተ ምሕላው ተከናውኗል።
በሌላ በኩል በማጠቃለያው ቀን በማታው መርሃግብር የንሥሐ አባት ያልነበራቸው ሃያ ስምንት ምዕመናን የንሥሐ አባት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህም ምዕመናኑ በምክረ ካህን እየተመሩ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጸኑ ለማስቻል የተከናወነ የመንፈሳዊ አገልግሎት አካል ነው።
