በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት የእረፍት በዓል ብፁዕነታቸው በተገኙበት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ!

ኤክቱስ ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም

የምድራዊው ሱራፊ፣ ሐዲስ ሐዋርያ፣ መምህረ ትሩፋት የጻድቁ የአቡነ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት በኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በገደብ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በዕለቱ ታቦቱ ከመንበሩ ከወጣ በኋላ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን የሚያሳይ ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል።

የዕለቱን ትምህርት መጋቤ ጥበባት መምህር ኤርምያስ እንዳሻው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቦሌ በሻሌ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የቁጥጥር ክፍል ኃላፊ የጻድቁን ዜና ሕይወታቸውን በመተረክ፣ ስለክብራቸው፣ ስለአማላጅነታቸው በሰፊው አስተምረዋል።

በመቀጠል ቀሲስ ሙሉዓለም ዐባይ የሐዋሳ ደብረ ምጥማቅ መድኃኔዓለም የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ከሊቀ ትጉሃን ሀብታሙ አበበ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ጋር በመሆን በደብሩ ለሚሠሩ የልማት ሥራዎች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር አከናውነዋል።

በመጨረሻም በወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ሰላም እኔምአየሁ ዓለሙ ጋባዥነት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በዚያ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው በንግግራቸው አሁን ያለውን የቅዱሳት ምሥጢራት ተሳትፎ ደካማነት በማንሳት ምዕመናን በቅዳሴ፣ በንሥሐ፣ በቅዱስ ቁርባን ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈው በጸሎት ፈጽመዋል።

Scroll to Top