በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በዲላ ከተማ ለሚገነባው የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ የገቢ ማስገኛ ሎተሪ መዘጋጀቱ ተገለጸ!

ኤክቱስ ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም

​በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ከተማ ለሚያስገነባው የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ ለገቢ ማስገኛ የሚሆን የሎተሪ ዕጣ መዘጋጀቱን ሀገረ ስብከቱ አስታውቋል። ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ፕሮጀክት ከብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ መቀመጫነት ባለፈ በሀገረ ስብከቱ የሚከናውኑ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚከናወኑበት መሆኑ ተገልጿል።

​በዛሬው ዕለት በተከናወነው የሎተሪ ማከፋፈያ መርሃ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገሪማ የተገኙ ሲሆን ሥራው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሁሉም ሰው ኃላፊነት መሆኑን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው እንዲህ ያሉ የልማት ሥራዎች የቤተ ክርስቲያንን ክብር ከማስጠበቅ ባለፈ ምእመናን በረከት እንዲያገኙ ዕድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

​በመርሃ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የየክፍል ኃላፊዎች፣ የየወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጆችና ጸሐፍት፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች እና የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ አሠሪ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል።

​ሀገረ ስብከቱ ለገቢ ማስገኛው ያዘጋጀውን ይህንን የሎተሪ ዕጣ ለስድስቱ ወረዳ ቤተ ክህነትና ለማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል በዛሬው ዕለት አከፋፍሏል።

​ይህ በዲላ ከተማ የሚገነባው የመንበረ ጵጵስና ሕንጻ ግንባታው ሲጠናቀቅ የሀገረ ስብከቱ ለመንፈሳዊ አገልግሎት መሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

ዕጣው የሚወጣበትን ቀን ሀገረ ስብከቱ የሚያሳውቅ ይሆናል።

Scroll to Top