በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት መንፈሳዊ አገልግሎትን ከልማት ጋር የሚያቀናጅ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ!!!

ኤክቱስ ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል እና በአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም አብያተ ክርስቲያናት ገቢን ለማጠናከርና የአብነት ተማሪዎችን በቋሚነት ለመርዳት የታለመ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት በይፋ ተጀምሯል።

ይህ ተስፋ ሰጪ የልማት ሥራ በዶ/ር ሙሉእመቤት ወርቁ አነሳሽነት እንዲሁም በላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ እና በወ/ሪት ሰላም አያሌው አስተባባሪነት የተጀመረ ነው። በመጀመሪያው ዙር በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን 250 የሥጋ ዶሮዎች እንዲሁም በአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን 100 የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንዲገቡ ተደርጓል።

ለሥራው ስኬታማነትም የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ተቋም (ILRI) ሰራተኛና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ወንድሜነህ እሳቱ፣ ዶ/ር አሉላ አለማየሁ እና ዶ/ር መኮንን ግርማ ዶሮዎችን ከአዲስ አበባ በማምጣት፣ በማስገባትና የማስጀመር ሥራውን በማከናወን ሙያዊ ፣ የቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

ከዲላ መንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ከሚገኙ 13 አብያተ ክርስቲያናት ለተውጣጡ 24 ሰልጣኞች በዘርፉ ባለሙያዎች ስለ ዶሮ እርባታ ጥልቅ ስልጠና ተሰጥቷል። ስልጠናውም፦
•  ጥምር ጠቀሜታ ያላቸው ዶሮዎች እርባታ፤
•  የዶሮ መኖ አዘገጃጀት፤
•  ሳይንሳዊ የዶሮ እንክብካቤና ጤና አጠባበቅ እና
•  የዶሮ እርባታ ትርፋማነት ላይ ያተኮረ ነበር።

ሰልጣኞቹ በሰጡት አስተያየትም “ይህ ስልጠና ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን ሰፊ መሬትና የሰው ኃይል በመጠቀም እንዴት ውጤታማ መሆን እንደምትችል ዓይን ከፋች ሆኖልናል፤ ወደ ተግባር ለመግባትም ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በዕለቱ ተገኝተው  ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ያስተባበሩትን፣ ድጋፍ ያደረጉትንና ስልጠና የሰጡ ባለሙያዎችን አመስግነው ሀገረ ስብከቱ የፕሮጀክቱ ባለቤት በመሆን ወደ ትግበራ እንደተገባና ወደፊትም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ አባታዊ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል። ብፁዕነታቸው በመልእክታቸውም “ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን በስፋት ለማከናወን ራሷን በኢኮኖሚ መደገፍ ይኖርባታል። ይህ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት የአካባቢውን ምዕመናንና ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልና የአብነት ተማሪዎቻችንን ለመመገብና የቤተ ክርስቲያንን ገቢ ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ አለው” በማለት አሳስበዋል።

በዕለቱ እንግዶች በአንዲዳ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ የአብነት ተማሪዎችን በመጎብኘት የትምህርት ሂደታቸውን ተመልክተዋል።

Scroll to Top