በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በከፍተኛ ውጤት የተመረቁ ተማሪዎች የተሸለሙት ዋንጫዎች በዐውደ ምሕረት ላይ ለሰንበት ትምህርት ቤታቸው አበረከቱ!

ኤክቱስ ሐምሌ 7/2018 ዓ.ም

​በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት የዲላ መካነ ቅድስት ሥላሴ ወአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን የፍሬ ተዋሕዶ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ከተማሩባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ማዕረግ መመረቃቸው ተበስሯል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ዘማሪት እስከዳር እሸቴ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ የትምህርት ክፍል 3.98 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚና የማዕረግ ተመራቂ መሆን ችላለች።

በተመሳሳይ ወጣት የምስራች ምትኩ ከዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በዲግሪ መርሃግብር 4.00 ሙሉ ነጥብ በማስመዝገብ ከግቢው ጠቅላላ አንደኛ በመሆን ባለ ሁለት ዋንጫ እና ባለ ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆናለች።

​ዛሬ በተከበረው ዓመታዊው የሐምሌ ቅድስት ሥላሴ የንግሥ በዓል ላይ ወጣት የምስራች ምትኩ ያስመዘገበችውን ታላቅ ስኬት ተከትሎ ያገኘችውን የክብር ሽልማት ይዛ ቀርባለች። ለዚህ ማዕረግ ላበቃ ለእግዚአብሔር አምላክ ምስጋናዋን ካቀረበች በኋላ በዕለቱ ዐውደ ምሕረት ላይ የተሸለመችውን የክብር ዋንጫ ለዓመታት በእምነትና በአገልግሎት ኮትኩቶ ላሳደጋት ለፍሬ ተዋሕዶ ሰንበት ትምህርት ቤት በአደባባይ በአደራነት አስረክባለች።

​በዕለቱ በዐውደ ምሕረቱ ላይ የተከናወነው ይህ ሥነ ሥርዓት በበዓሉ ላይ በታደሙት አገልጋዮችና ምዕመናን ዘንድ መንፈሳዊ ኩራትን የፈጠረ ነበር። ይህም ወጣቶች በመንፈሳዊ አገልግሎታቸው እየጠነከሩ በዓለማዊ ትምህርታቸውና በሳይንሱ ዘርፍም ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ በተግባር ያሳየ አርአያ ሆኖ አልፏል።

Scroll to Top