ኤክቱስ ጥቅምት 22/2019 ዓ.ም
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት በገጠራማዋ በኦኖንቾ ቀበሌ ገበያ አካባቢ ሲያካሂድ የቆየውን የሦስት ቀናት መንፈሳዊ ጉባኤ አጠናቋል። ጉባኤው በአካባቢው የሚገኙ ምእመናንን በቋንቋቸው በመንፈሳዊ እውቀት እንዲያገኙ፣ ኦርቶዶክሳዊ ሕብረትን ለማጠናከርና የመንግሥቱን ወንጌል ይበልጥ ለማስፋፋት አልሞ የተዘጋጀ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በዚህ ጉባኤ ከዚህ ቀደም የንሥሐ አባት የሌላቸው ስድስት ምዕመናን የተመዘገቡ ሲሆን የኦኖንቾ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የንሥሐ አባት እንዲመድብና የቅዱሳት ምሥጢራት ተሳታፊ እንዲሆኑ እንዲያደርግ በሀገረ ስብከቱ መመሪያ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በአሚነ ሥላሴ ያልነበሩ ምዕመናን በጉባኤው ባገኙት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ተማርከው አሥራ አንድ ሰዎች ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ ቃል ገብተው ተመዝግበዋል። በዚህም የደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መምህር በመመደብ የቅድመ ጥምቀት ትምህርት እንዲሰጣቸው እና ለጥምቀት እንዲያበቋቸው መመሪያ ተሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች እርስ በእርስ ተጋጭተው የነበሩ የአከባቢው ማኅበረሰብ እዚያው በሕዝቡ ፊት ይቅርታ እንዲጠያየቁ እና እርቀ ሰላም እንዲያቀርዱ ተደርጓል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ የኮቾሬ ገደብና ጮርሶ ወረዳዎች ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም እኔምአየሁ ዓለሙ የተገኙ ሲሆን መምህር ሀብታሙ አየለ(ዲ/ን) እና መምህር እሥራኤል ብርሃኑ በጌዴኡፋ ቋንቋ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በተጨማሪም ዘማሪ ምንያህል ዶሬ (ዲ/ን) እና ዘማሪ አዲስ ነጋሽ በዝማሬ ያገለገሉ ሲሆን በዜማ መሣሪያ (በክራር) ደግሞ ዘማሪ ሃይማኖት ታደሰ አጅበዋል።
በጉባኤው እንደተገለጸው ሀገረ ስብከቱ መሰል መንፈሳዊ ጉባኤያትን በገጠራማና ራቅ ባሉ አካባቢዎች በቋንቋቸው አጠናክሮ የመቀጠል እቅድ አለው። የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እስከ ገጠር ድረስ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።
