በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በአንዲዳ የአዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት የጉብኝትና የውይይት መርሃ ግብር ተካሄደ!

ኤክቱስ ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በሀገረ ስብከቱ ዕቅድ መነሻነት የአንዲዳ አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት በመገኘት የአሁናዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን እና በማኅበረ ቅዱሳን እየተገነባ የሚገኘውን አዲስ የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል። የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የአብነት ትምህርት ቤቱን ነባራዊ ሁኔታ በመመልከት የትምህርት ሂደቱን ይበልጥ ማጠናከር እና የሕንጻውን ግንባታ አፈጻጸም መገምገም ላይ ያተኮረ ነበር።

የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች በመርሃ ግብሩ ወቅት በአብነት ትምህርት ቤቱ ተገኝተው ከመማር ማስተማር ሂደቱ ጎን ለጎን ከደቀ መዛሙርቱ እና ከመምህራን ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

በሌላ በኩል በማኅበረ ቅዱሳን እየተገነባ የሚገኘውን አዲስ የአብነት ትምህርት ቤት ሕንጻ የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ዲላ ማዕከል የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምንላርግህ የትዋለ እና ኢንጅነር ዲያቆን በእርሱፈቃድ ተገኝተው ስለ ግንባታው ሂደት ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሥራውን በፍጥነት እና በጥራት ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ላይ መክረዋል።

በዚህ የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን አጥናፉ ማሞ፣ የመንፈሳዊ ትምህርትና የካህናት አገልግሎት ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች እና የዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጠበብት መሠረት ይልማ በቦታው ተገኝተዋል።

Scroll to Top