በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

የሀገረ ስብከት ታሪክ

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ሥር የሚገኙ ሦስት ዞኖችን በማካተት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ የሚያከናውን መዋቅር ነው። ሀገረ ስብከቱ ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የዲላ ከተማ የመንበረ ጵጵስና መቀመጫውን (ማዕከልነቱን) አድርጎ የሚንቀሳቀስ የቤተ ክህነት አስተዳደር ነው። ​ምንም እንኳን ሀገረ ስብከቱ በአሁኑ የሀገረ ስብከት አደረጃጀቱ ጥቅምት 21 ቀን 2012 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ቢቋቋምም በአካባቢው ያለው የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ግን የቆየ መሠረት አለው። ከእነዚህም መካከል በኮሬ ዞን የሚገኘው የየሮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መመሥረቱ በአካባቢው የነበረውን ጥንታዊ የሃይማኖት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ዋነኛ ማስረጃ ነው። ​በተመሳሳይ በ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በ1882 የተመሰረተው የቡሌ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ፣ በ1891 የተመሰረተው የመንዶ ቅዱስ ሚካኤል፣ በ1895 የተመሰረተው የላባ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በ1827 የተመሰረተው የጪጩ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በ1892 የተመሰረተው የገርቦታ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በ1891 የተመሰረተው የሲጊጋ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንደአብነት በአካባቢው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ዘንድ ለረጅም ዘመናት የቆየ መንፈሳዊ ተደራሽነት እንደነበራት ማሳያ ነው። ይህ ታሪካዊ መሠረት ሀገረ ስብከቱ አሁን ላለው መዋቅራዊ እድገት እንደ መነሻ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ​የሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ መቋቋም አስፈላጊ የሆነው ቀድሞ የነበረው የሲዳማና ጌዴኦ ዞኖች አማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት መዋቅር እጅግ ሰፊ በመሆኑ እና ለመንፈሳዊ አገልግሎት ተደራሽ አለመሆኑ ነው። ይህ ሰፊ መልክዓ ምድር ለአስተዳደር ምቹ ባለመሆኑ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚደረገው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ተዳክሞ ቆይቷል። ​በዚህ ምክንያት በአካባቢው ያለው የምዕመናን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ ለሀገረ ስብከቱ መመሥረት ዋነኛው ምክንያት ሆኗል። አገልግሎቱን ወደ ምዕመኑ ለማቅረብና የአቅም ችግር ላለባቸው አብያተ ክርስቲያናት መልሶ ለማጠናከር ስፋቱን ማጥበብና ራሱን የቻለ አመራር መስጠት የግድ ነበር። ​ሀገረ ስብከቱ ከተመሰረተ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሲዳማ ሀገረ ስብከት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ ይመራ ነበር። በዚህም አሰራር በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆኑም ይህ ሁኔታ ሀገረ ስብከቱ ራሱን በቻለ አቅም እንዲንቀሳቀስና አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን እንዲያከናውን ዕድል ሳይሰጠው ለጥቂት ዓመታት ቆይቷል። ​ይህንን ክፍተት ለመሙላት በ2015 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ገሪማን ሀገረ ስብከቱን በቋሚነት እንዲመሩ ሾመ። ​በአሁኑ ወቅት ሀገረ ስብከቱ አገልግሎቱን በስድስት የወረዳ ቤተ ክህነት መዋቅሮች በኩል ያከናውናል። እነዚህም የዲላ እና ወናጎ(በተለምዶ መንበረ ጵጵስና)፣ የይርጋጨፌ፣የኮቾሬ ገደብና ጮርሶ፣ የቡሌና ረጴ፣ የኮሬ ዞን እንዲሁም የቡርጂ ዞን ወረዳ ቤተ ክህነቶች ናቸው። ​በእነዚህ ስድስት ወረዳዎች ስር በአጠቃላይ 78 አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ። ይኸውም በዲላና ወናጎ 17፣ በይርጋጨፌ 15፣ በቡርጂ 15፣ በኮቾሬ ገደብና ጮርሶ 13፣ በኮሬ 11 እና በቡሌና ረጴ 7 አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።​ምንም እንኳን መዋቅራዊ አደረጃጀቱ አሁን ከበፊቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢደርስም ሀገረ ስብከቱ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳያመጣ እንቅፋት የሆኑ በዋናነት አራት ተጨባጭ ችግሮችን መጥቀስ ይቻላል። ​በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚታየው የሰባኪያነ ወንጌል እጥረት፣ ምዕመናን ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በቂ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው አድርጓል። ይህን ክፍተት ለመሙላት ሀገረ ስብከቱ ለባለ ድርሻ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ግንዛቤ በመፍጠር ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ ይገኛል። ሆኖም ይህ በቂ ባለመሆሙ ምክንያት የምዕመናንን ቁጥር በተፈለገው መጠን ልክ ማብዛት አልተቻለም። ​ 2. የአብነት ትምህርት ቤት አለመኖር በሀገረ ስብከቱ ውስጥ አንድም የአብነት ትምህርት ቤት አለመኖሩ ሌላኛው ችግር ነው። አብነት ትምህርት ቤት አገልጋዮችን ለማፍራት መሠረት ቢሆንም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ባለመኖሩ ምክንያት አዳዲስ ተተኪ አገልጋዮችን የማግኘት ዕድል እጅግ አነስተኛ ነው።ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ የተወሰኑ አገልጋዮችን ማፍራት የተቻለው በከተማ የሚገኙ ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት በጎ ፈቃድ ያላቸውን ካህናት በመመደብ ልጆችን በመሰብሰብ በሚሰጡት መሠረታዊ መንፈሳዊ ትምህርት ብቻ ነው። ይህ ሁኔታ ለሀገረ ስብከቱ የወደፊት የአገልጋይ ፍላጎት አስተማማኝ መፍትሔ አይደለም። ለዚህም መፍትሄ እንዲሆን ሀገረ ስብከቱ በአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ የመቃብር ቤቶችን በማደስ፣ ማደሪያ በማዘጋጀት፣ መምህር በመቅጠር እና አስፈላጊውን ሁሉ ግብዓት በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር የተወሰኑ ደቀ መዛሙርትን እያስተማረ ይገኛል። በተጨማሪም ከደብሩ መሬት በመውሰድ እና በመግዛት አዲስ የአብነት ትምህርት ቤት በማኅበረ ቅዱሳን እየተገነባ ይገኛል። ቢሆንም የመማር ማስተማር ሂደቱ በጎ ፈቃደኛ ምዕመናንን በማስተባበር እንጂ ቋሚ ገቢ የለውም። በአገልጋይ እጥረትና በንዋየ ቅድሳት እጥረት ምክንያት በርካታ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተው መቆየታቸው ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። እነዚህ አጥቢያዎች አገልግሎት አለመስጠታቸው በአካባቢው የሚገኘው ምዕመን ከመንፈሳዊ ሕይወት እንዲርቅና ወደ ሌላ ምርጫ እንዲያመራ አድርጎታል።​ሀገረ ስብከቱ እነዚህን የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት መልሶ ለመክፈትና አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላት ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ ያለው አቅም ግን ከችግሩ ስፋት ጋር ሲነጻጸር ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀረው ያሳያል። ይህ በገጠር የሚገኝን ምዕመን የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ የሀገረ ስብከቱ ቀዳሚ ተግባር ነው። ከዚህ ቀደም ሀገረ ስብከቱ የሚከተለው ዘመኑን ያልዋጁ እና ኋላ ቀር አሠራሮችን ነበር። ይህንን​የአስተዳደር ሥርዓቱንም ዘመኑን ወደ ዋጀና ቀልጣፋ ወደ ሆነ አሠራር የመቀየር አስፈላጊነት አሁንም በሀገረ ስብከቱ ዘንድ ይታመናል። ይህንንም ለማሳካት ሀገረ ስብከቱ በሒሳብ ሥራ ረገድ ከዚህ ቀደም የሚከተለው ኋላ ቀር አመዘጋገብ የሆነውን የነጠላ የሒሳብ አመዘጋገብ የሚከተል ሲሆን ይህንን ሥራውን አዘምኖ የድርብ አመዘጋገብ ሂደትን ተግባራዊ አድርጓል። ሀገረ ስብከቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ረገድ ዌብሳይት አዘምኖ መረጃ እያሠራጨ ይገኛል። በተጨማሪም በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ማለትም በፌስቡክ፣ በቴሌግራም፣ በቲክቶክ፣ በኢንስታግራም ኤክቱስ የተባለ ገጽ በመክፈት መረጃዎችን በንቃት እያሰራጨ ይገኛል። ​እንዲሁም ከዚህ ቀደም ሀገረ ስብከቱ በዕቅድ የሚመራ ያልነበረ ሲሆን አሁን ግን የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎ ወረዳ ቤተ ክህነትና አጥብያዎች ድረስ በማውረድ ሥራዎችን በዕቅድ መነሻነት እያከናወነ ይገኛል። በጌዴኦ በኮሬና በቡርጂ ዞኖች በአከባቢው ቋንቋዎች ወንጌልን ለማድረስ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በሀገረ ስብከቱ የቋንቋ ትርጉም ሥራዎችን የሚሠራ ክፍል ተቋቁሟል። ነገር ግን ከሥራው ስፋት የተነሳ ያለው የገንዘብ እና የሰው ኃይል በቂ አይደለም። ​በአጠቃላይ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት አሁን ላይ ያለው መዋቅራዊ እድገት ጥሩ ቢሆንም፣ ከላይ የተጠቀሱት ተግዳሮቶች የምዕመናን ቁጥር፣ የተጠናከረ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ጠንካራ አስተዳደራዊ መዋቅር በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን እንቅፋት ሆነዋል። ​ሀገረ ስብከቱ እነዚህን ችግሮች በመለየትና ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት፣ ወንጌልን በማስፋፋት፣ ወደፊት የተሻለ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠትና የምዕመናን ቁጥርን ለማሳደግ በሂደት ላይ ያለ ተቋም ነው።

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት Read More »

የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ

የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ምዕራፍ ስድስት፣ ዐንቀጽ ሠላሳ ስምንት እስከ አርባ አምስት ድረስ በተዘረዘረው መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠረት የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መሥርቶ እና አጠናክሮ መሥራቱ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡በቃለ ዐዋዲው ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው» በእንግሊዝኛው «ዳዮሰስ» የሚለው ቃል dioikesis ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡  በመሆኑም ሀገረ ስብከት ማለት በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ አንድ አካባቢ ማለት ነው፡፡ሀገረ ስብከት ለመጀመርያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ለማስተማር በወጡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ይመቻል፣ አይመችም ሳይሉ በተሠማሩበት ሀገረ ስብከት ገብተው አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል፣ ምእመናንን አስተምረው በማጥመቅ፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን በመሾም የወንጌልን ቃል ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሀገረ ስብከቱ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊው በታናሽ እስያ ሀገረ ስብከቱ፣ ቶማስ በሕንድ ሀገረ ስብከቱ፣ማርቆስም በእስክንድርያ የሠሩት ሥራ ለዚህ ማስረጃችን ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ነገሥታት እና ሕዝብ በጎ ፈቃድ እና አርቆ አስተዋይነት ወደ እስክንድርያ ተልእኮ ለጵጵስና የበቃው የመጀመርያው ጳጳስ ፍሬምናጦስ ሀገረ ስብከት «ጳጳስ ዘአኩስም ወዘኩላ ኢትዮጵያ» የሚል ነበር፡፡ ከእርሱ በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር እንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ ቆይታለች፡፡የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በተለያዩ ጊዜያት ከአንድ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት ተሾመው መጥተው ስለነበር ከአንድ በላይ አህጉረ ስብከት እንደነበራት ይጠቁማል፡፡ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1438 ዓም ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ከግብጹ ፓትርያርክ ዮሐንስ 14ኛ ተሾመው መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ለአምሐራ፣ አቡነ ገብርኤልም ለሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተመደቡ፡፡ ይህም በወቅቱ የነበረውን የሀገረ ስብከት አደረጃጀት ያመለክታል፡፡ በዐፄ ዮሐንስ ጊዜም በ1874 ዓ.ም አራት ጳጳሳት ከግብጽ መጥተው አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ማቴዎስ የሸዋ ጳጳስ፣ አቡነ ሉቃስ የጎጃም፣ አቡነ ማርቆስ የበጌምድር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡ እነዚህ አበው በውል የተለየ ቦታ ተከልሎ ተሰጥቷቸው እንደነበር ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በጻፉት «ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ» በተባለው መጽሐፋቸው የአቡነ ማቴዎስን ሀገረ ስብከት ሲዘረዝሩ «ሸዋን ከበሽሎ ወዲህ መደብ አድርገው የጁን፣ ዋድላን፣ ደላንታን፣ ዳውንትን፣ ግራ መቄትን፣ ከበጌምድር መጃን፣ ስዲን፣ ፎገራን፣ ጭህራን፣ደምቢያን፣ አርማጭሆን፣ መረባን፣ ጃን ፈቀራን፣ ጃንዋራን፣ ቆላ ወገራን፣ ጠገዴን፣ ወልቃይትን» እያለ ይዘረዝራል፡፡ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ  ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመርያዎቹን ጳጳሳት ስታገኝ የታወጀው ዐዋጅ ዐንቀጽ አንድ «የኢትዮጵያ የመላው ሊቀ ጳጳሳት በአቡነ ቄርሎስ ሆኖ ደቡቡ ለአቡነ ሳዊሮስ፣ ምዕራቡ ለአቡነ አብርሃም፣ ምሥራቁ ለአቡነ ጴጥሮስ፣ አዜቡ ለአቡነ ሚካኤል፣ ሰሜኑ ለአቡነ ይስሐቅ ይሁን» ይላል፡፡ ይኼው ዐዋጅ የየአንዳንዱን ጳጳስ የሀገረ ስብከት ክልል ዝርዝር እና የመንበረ ጵጵስናውን ማረፊያ ከተማ ይተነትናል፡፡ በጣልያን ዘመን ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እና ጳጳሳት ተሰባስበው ብጹዕ አቡነ አብርሃምን ሊቀ ጳጳስ አድርገው አምስት ጳጳሳትን ሲሾሙ አዳዲስ አህጉረ ስብከት ተመሠረቱ፡፡ አቡነ ዮሐንስ የሸዋ፣ አቡነ ማርቆስ የኤርትራ፣ አቡነ ማቴዎስ የወሎ፣ አቡነ ገብርኤል የጎንደር እንዲሁም አቡነ ሉቃስ የወለጋ አህጉረ ስብከት ጳጳሳት ሆነው ተሾመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራስዋን አህጉረ ስብከት መመሥረት የጀመረችው ከራስዋ ልጆች መካከል ፓትርያርክ ባገኘች ጊዜ ነበር፡፡ በ1943 ዓም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አቡነ ታዴዎስን ለጎሬ፣ አቡነ ገብርኤልን ለወሎ፣ አቡነ ማርቆስን ለኤርትራ፣ አቡነ ፊልጶስን ለኢየሩሳሌም፣ አቡነ ጎርጎርዮስን ለከፋ ጳጳሳት አድርገው ሾመው ነበር፡፡ ይህም አዳዲስ አህጉረ ስብከት መመሥረታቸውን ያመለክታል፡፡ በ1948 ዓ.ም ትግራይ በሀገረ ስብከትነት ተቋቁሞ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ተሾመውበታል፡፡  በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአህጉረ ስብከት ቁጥር በየጊዜው እያደገ መጥቶ፣ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ» በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጡት፣ በ1974 ዓ.ም የአህጉረ ስብከቱ ዕድገት ወደ አሥራ ዘጠኋ ያህል ደርሶ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም» የተሰኘው  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፍ እንደሚገልጠው አርባ በሀገር ውስጥ፣ ስምንት ከሀገር ውጭ፤ በድምሩ አርባ ስምንት አህጉረ ስብከት ይገኛሉ፡፡ ሀገረ ስብከት ሀገረ ስብከት ቤተ ክህነቱን ወክሎ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ ከክርስቶስ ጀምሮ የመጣውን ሀብተ ክህነት ለመጠበቅ እና ለማስተላለፍ፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ ገዳማት እና አድባራት እንዲረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከሉ፣ ምእመናን ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መብት እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ወጥ እና ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የካህናት አስተዳደር እና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት እንዲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት እና ንብረት በሕግ እና በሥርዓት መሠረት እንዲጠበቅ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲሰጡ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ተግባሮቹ ናቸው፡፡

የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ Read More »

Scroll to Top