በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በብፁዕነታቸው መሪነት የደመወዝ እርከንና ማስተካከያ አፈጻጸም ግንዛቤ መድረክ ተካሄደ

ኤክቱስ ኅዳር 05/2019 ዓ.ም.

በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መሪነት ለአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ለሰበካ ጉባኤ አባላትና ለሚመለከታቸው አካላት በአብያተ ክርስቲያናት የአገልጋዮች የደመወዝ እርከን፣ ማስተካከያና ጭማሪ አፈጻጸም የግንዛቤ መስጫ ሰነድ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሄደ።

ብፁዕነታቸው የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት አባታዊ መመሪያ እና ቃለ ምዕዳን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሕይወት መደገፍ እና የአገልግሎት ተነሳሽነታቸውን ማሳደግ የአስተዳደሩ ዋነኛ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ወቅታዊውን የኑሮ ሁኔታና የአብያተ ክርስቲያናቱን የፋይናንስ አቅም ያገናዘበ ፍትሐዊና ወጥነት ያለው የደመወዝ ስኬል ተግባራዊ ማድረግ ለአገልግሎቱ ጥራት እና ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑን በመክፈቻ ንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመቀጠል በመልአከ ብርሃን ዳንኤል ነቢዩ አቅራቢነት በተሰጠው ሥልጠና በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አድባራት በሶስት ምድቦች የተከፋፈሉበት ሁኔታ እና የደመወዝ እርከን አወቃቀር ቀርቦ ሰፊ ምክክር ተደርጎበታል።

ተሳታፊዎቹም የአድባራቱን የልማት ሥራ ከማሳደግ አንጻር እና የኑሮ ውድነት በማገናዘብ ፍትሐዊ፣ ግልጽና ዘላቂነት ያለው አሠራር መዘርጋት በሚያስችሉ ሐሳቦች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በተጨማሪም የደመወዝ ማስተካከያና ጭማሪ ጥያቄ ከደብር ሰበካ ጉባኤ እስከ ሀገረ ስብከት ባለው መዋቅር በምን ቅደም ተከተል መቅረብ፣ መመርመርና መጽደቅ እንዳለበት የእያንዳንዱ አካል ድርሻና ኃላፊነት ተለይቷል። የደመወዝ ስኬሉ በወጥነት መተግበሩን የሚከታተል እና የሚያስፈጽም አሠራር እንዲጠናከር አቅጣጫ ተቀምጧል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በብፁዕነታቸው ሰፊ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

መርሃ ግብሩም በብፁዕ አቡነ ገሪማ ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።

Scroll to Top