ኤክቱስ መስከረም 27/2019 ዓ.ም
በዲላ ከተማ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ድርብ የሒሳብ አመዘጋገብ (Double-Entry Accounting) ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ መተግበር መጀመራቸውን ተከተሎ፤ ይህንኑ አሠራር በይርጋጨፌ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የምክክርና የሥልጠና መርሃ ግብር ተካሄደ።
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከወረዳ ቤተ ክህነቱ፣ ከከተማው የሦስቱ አድባራት አስተዳዳሪዎችና የአስተዳደር አካላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በመርሃ ግብሩ ብፁዕነታቸው ራሳቸው ያዘጋጁትን «የደብል ኢንትሪ የሒሳብ አያያዝ፣ የፋይናንስ ግልጽነት እና የሕጋዊነት አስፈላጊነት» የተሰኘ ሰፊ ገለጻና ፕረዘንቴሽን (Presentation) ለአስተዳደር አካላቱ አቅርበዋል። በገለጻቸውም የፋይናንስ አስተዳደርን ማዘመን፣ በየደረጃው ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን እንዲሁም የቤተክርስቲያኗን ሀብት በሕጋዊና በዘመናዊ መንገድ ማስተዳደር የሚቻልበትን አቅጣጫ አመላክተዋል።
ቀደም ሲል በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረትም አሠራሩን በቴክኖሎጂ ለማደገፍና የሥራ ቅልጥፍናን ለመጨመር በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁና የፒችትሪ (Peachtree) ሶፍትዌር ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎችን የማደራጀት ሥራ የሚቀጥል ይሆናል።
የስብሰባው ተሳታፊዎችም የተሰጠውን ትምህርታዊ ገለጻ እንዲሁም መመሪያ በመቀበል አዲሱን ዘመናዊ የሒሳብ አመዘጋገብ አሠራር በከተማው ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደጉ ቀነ ገደብ በማስቀመጥ ገልጸዋል።
በመርሃግብሩ የሀገረ ስብከቱ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ኃላፊ መልአከ ብርሃን ዳንኤል ነቢዩ፣ መምህር በየነ ክፍሌ የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥርና ምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ፣ መልአከ ሰላም ይባቤ ይልማ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ ኃይማኖት ብዙአየሁ ዳመነ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር አካላት ተገኝተዋል።
