ኤክቱስ መስከረም 23/2019 ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በጽሕፈት ቤታቸው ከተመረጡት ኮሚቴዎችና ከጥምቀትን በዲላ ማኅበር ጋር በዛሬው ዕለት የምክክር መርሃ ግብር አከናውነዋል። የስብሰባው ዋና ዓላማ ወር በገባ በመጨረሻው ሰንበት በብፁዕነታቸው መሪነትና በጥምቀትን በዲላ ማኅበር አዘጋጅነት የሚከናወነውን ወርሃዊ የወጣቶች መንፈሳዊ መርሃ ግብር በቀጣይ ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለና በተደራጀ ሁኔታ ማካሄድ እንዲቻል ለማድረግ ነው።
በውይይቱ መነሻነት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የተዘጋጀው “የኦርቶዶክሳዊ ወጣቶች መንፈሳዊና ምግባራዊ ሕይወት” የተሰኘ ምክረ ሃሳብ ለተሳታፊዎቹ የቀረበ ሲሆን አጠቃላይና አንድ ወጥ የሆነ የወጣቶች ሥርዓተ ትምህርት ማዘጋጀት፣ በዲጂታል ሚዲያና በፖድካስቶች ዘመኑን የዋጀ የወንጌል ትምህርት ማሰራጨት፣ እንዲሁም ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራና የክህሎት ማሳደጊያ መርሃ ግብሮችን ማደራጀት የሚሉ ዐበይት ነጥቦች ተዳስሰዋል። በተጨማሪም ወጣቶች በዓመት ውስጥ ለቀናት በገዳማትና ማዕከላት ገብተው የሚያሳልፉበት የመንፈሳዊ ሕይወት ማደሻ መርሃ ግብር ማዘጋጀት፣ በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የጥናት ማዕከላትን ማቋቋም እና ወጣቶች በቅዳሴ፣ በንሥሐ፣ በቅዱስ ቁርባንና በመንፈሳዊ አገልግሎት በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ በስፋት ተመልክተዋል።
በመቀጠል በብፁዕነታቸው ምክረ ሃሳብ መነሻነት የውይይቱ ተሳታፊዎች ተጨማሪ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን የቀረበውን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ በመደገፍ መርሃ ግብሩን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ገንቢ ሃሳቦችንም አክለዋል።
በመጨረሻም የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል መርሃ ግብር የተነደፈ ሲሆን የዕለቱ የምክክር መርሃ ግብር በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ቡራኬና ጸሎት ተፈጽሟል።
