ኤክቱስ መስከረም 16/2019 ዓ.ም
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን!
– የተከበሩ የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ
– የተከበራችሁ የመንግሥት ባለሥልጣናት
– የተከበራችሁ የሀገረ ስብከታችን፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊዎች እና ሠራተኞች
– ክቡራን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና መምህራን
– ይህንን በዓል ለማክበር ከሩቅም ከቅርብም የተገኛችሁ እንግዶቻችንን ሁላችሁም ክቡራንና ክቡራት
እንኳን ለሁለት ሺህ አሥራ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ለቅዱስ መስቀል የደመራ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ!
“ወአልቦ ኅቡዕ ዘኢይትከበት ወአልቦ ክዱን ዘኢይትከሠት – እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም።”
ማር ፬-፳፪
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለድኅነተ ዓለም ሲል በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ዓለምን ካዳነ በኋላ፤ ቅዱስ መስቀሉ እጅግ ድንቅ ድንቅ ገቢረ ተአምራት ሲያደርግ ያዩት አይሁድ በምቀኝነት ተነሡ። የጌታ መስቀል እጅግ ብዙ ተአምራትን ማድረግ እንደሚችል ስላወቁና ይህንን ትምህርት ለማጥፋት ስለፈለጉ ቅዱስ መስቀሉን ከሁለት መስቀል ጋር በመውሰድ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ቀበሩት፤ በላዩም ላይ የከተማው ሕዝብ ቆሻሻ እንዲጥልበት አዘዙ። ለሦስት መቶ ዓመታትም ያኽል የከተማው ጥራጊና ቆሻሻ በላዩ ላይ ሲጣልበት በመቆየቱ ሥፍራው ትልቅ የቆሻሻ ተራራ ወይም ኮረብታ ሆነ።
ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ክብር በጥቂት ሰዎች ተንኮል ምክንያት ተሸሽጎ ሊቀር አልቻለም። ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ንግሥት ዕሌኒን አስነሣ። ጻድቃንን አነሳስቶ ወደገዳም፣ ሰማዕታትን አነሳስቶ ወደ ደም፣ ሐዋርያትን አነሳስቶ ወደ ዓለም ጫፎች የሚሰድ አምላክ ንግሥት ዕሌኒ የጠፋውንና ለዘመናት በተራራ ሥር ተሰውሮ የኖረውን የጌታን ቅዱስ መስቀል ፈልጋ እንድታወጣ ታላቅ መንፈሳዊ ፍላጎት አሳደረባት፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተጓዘች።
በዚያም አረጋዊውን ኪራኮስን አግኝታ በሚሰጣት መመሪያ መሠረት ደመራ አስደምራ ከንጹሕ ዕጣን ጋራ ጸሎት አደረገች። የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ቁልቁል ሰግዶ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ሥፍራ አመላከተ። በዚህም መሪነት ንግሥት ዕሌኒና ሕዝቡ መስከረም ፲፯ ቀን ቁፋሮውን በመጀመር፣ የቆሻሻውን ተራራ አስነስተው መጋቢት ፲ ቀን የጌታን ቅዱስ መስቀል በይባቤና በአኮቴት ቆፍረው አወጡት።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ ተሰብሮ የአምላካችን የማዳን ሥራ በግልጽ የታየበት ትልቅ በዓላችን ነው። ዛሬ በዚህ ስፍራ የደመራው እሳት ተለኩሶ በዓሉን ስናከብር ከእግዚአብሔር ረድኤት እና በረከት እንድናገኝ ከአምናውና ካለፈው በተሻለ በንጽሐ ልብ ሆነን ልናከብር ይገባናል። መስቀል የቤተ ክርስቲያናችን አርማ የእኛም የክርስቲያኖች መለያችን ነው፤ በአንገታችንም አስረነዋል። በልባችንም ስለነዋል። በመሆኑም በልባችን ያለውን የጥላቻ አስተሳሰብ በንስሐ አስወግደን፣ ቅዱስ መስቀሉን ከተቀበረበት ከቆሸሸ ተግባራችን ሥር ልናወጣው እና “ብርሃኑም በሰዎች ሁሉ ፊት እንዲያበራ” ልናደርገው ይገባል።
ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ “አባ ኅድግ ወስረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ” በማለት ኃጢአትን ይቅር የሚል፣ በደልን የሚደመስስና መፍቀሬ ንስሐ መሆኑን በገሃድ አሳይቶናል። ይህ ከፊታችን ያለው የደመራው እሳት እንጨቱን አቃጥሎ እንደሚያጠፋው ሁሉ እኛም በልባችን ያለውን ቅሬታና ልዩነት በፍጹም ይቅርታ አቃጥለን በመካከላችን ፍቅርን ልንዘራ ይገባናል። የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ክብሯ በልጆቿ አንድነት ውስጥ ጎልቶ ይታያልና።
በተለይም በሀገረ ስብከታችን የምትኖሩ ውድ ልጆቻችን፤
ይህንን ታላቅ በዓል እያከበርን የምንገኘው በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር ላይ መሆኑ የራሱ የሆነ ዘርፈ ብዙ የሆነ ትልቅ ፋይዳ አለው። በዩኔስኮ ከተመዘገበው ታሪካዊው የመስቀል በዓላችን ጋር ተያይዞ የተገኘው ይህ ልዩ አጋጣሚ መንፈሳዊ እሴታችንንና ባህላዊ ቅርሳችንን አስተሳስሮ ለዓለም የሚያስተዋውቅ እንዲሁም የአካባቢያችንን ገጽታ የሚያጎላና ወጣቱ ትውልድ ኃይማኖቱን፣ ማንነቱንና ተፈጥሮውን አክብሮ እንዲጠብቅ የሚያነቃቃ ትልቅ ሀብታችን ነው። በመሆኑም እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ ፍቅርን በማብዛትና የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በመጠበቅ የመስቀሉ ሥራ ምስክሮች መሆናችሁን በሥራ ልታሳዩ ይገባል።
ይህ የደመራና የመስቀል በዓል ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ለሀገራችንና ለሕዝቦቿ ሁሉ የሰላም፣ የፍቅርና የበረከት በዓል ዘመኑም የተባረከ ዘመን እንዲሆንልን አምላካችንን ይፍቀድልን።
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!
መስከረም 16/2019 ዓ.ም
ዲላ፤ ኢትዮጵያ
