ኤክቱስ ጳጉሜን 5/2018 ዓ.ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
“እግዚኦ ባርክ ፍሬሃ ለምድር መሐሪ ወጻድቅ መኑ ከማከ ዘታርኁ ክረምተ በጸጋከ ነፍስ ድኅንት ወነፍስ ርህብት እንተ ጸግበት ተአኩተከ – አቤቱ የምድርን ፍሬ ባርክ በሥጦታህ ክረምትን መልሰህ የምታመጣው ሆይ! እንደ አንተ ጻድቅና ርኅሩኅ አምላክ ማን ነው የታመመች ሰውነት በተፈወሰች ጊዜ የተራበች ሰውነት በጠገበች ጊዜ ታመሰግንሃለች”
ባሮክ ፪ ፥ ፮
በሀገረ ስብከታችን፣ በሀገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምዕመናንና ምዕመናት በሙሉ፤ ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር እንደርሱ ፈቃድና ቸርነት አሮጌውን ዓመት ዘመነ ማርቆስን አሳልፈን ወደ አዲሱ ዘመነ ሉቃስ የ2019 ዓመተ ምሕረት ስለሸጋገረን ዘለዓለማዊ ስሙ የከበረና የተመሰገነ ይሁን።
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!
እንደሚታወቀው አዲስ ዓመት ሲመጣ የጊዜያት መለወጥና የዘመን መፈራረቅ ብቻ ሆኖ እኛ የሕይወት መታደስ ሳይኖረው እጅግ ብዙ ዓመታትን አሳልፈናል። በሥራችን፣ በመውጣታችን፣ በመግባታችን፣ በንግግራችን፣ በሀሳባችን…. አምላካችን እግዚአብሔርን ስናሳዝን ቆይተናል። ያለፈውን ዓመት በንስሐ፣ በኃዳጌ በቀል ልብና በይቅርታ ቋጭተን አዲሱን ምዕራፍ በፍቅር፣ በሰላም፣ በበጎ ሥራ ሁሉ ልንጀምረው ካልቻልን የዘመን መፈራረቅ በራሱ ዋጋ ያለው ነገር ሆኖ ብቻውን ሊቆም እንደማይችል ግልጽ ነው።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምዕመናን እና ምዕመናት
እኛ ክርስቲያኖች ተብለን በክርስቶስ ስም እየተጠራን ነገር ግን ክርስቶስ ያላስተማረንን ቂም፣ በቀል እና ዘረኝነትን ገንዘብ አድርገን የምንኖር ከሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የሕግ ባለቤት ነን” እያሉ ነገር ግን ሕጉን የማይጠብቁትንና በግብዝነት የሚኖሩትን አይሁድን በሮሜ መልእክቱ “የእግዚአብሔር ስም በእናንተ ምክንያት በአህዛብ መካከል ይሰደባልና” ብሎ እንደገሰጸ እኛም እርስ በእርሳችን በይቅርታና በአንድነት በመቆም የክርስቶስን ፍቅርና ቸርነት በሕይወታችንና በሥራችን መግለጽ ካልቻልን ዛሬም ይህ መልእክት ለእኛ ነው።
ውድ ምእመናን ለሀገረ ስብከታችን፣ ለቤተክርስቲያናችንና ለሀገራችን ሰላም፣ ዕርቅና አንድነት የበኩላችንን ክርስቲያናዊ ኃላፊነት እንድንወጣ አደራ እንላለን።
በአዲሱ ዘመነ ሉቃስ ሀገረ ስብከታችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ከዚህ በላይ ተዳራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋት፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ለመደገፍ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት፣ ወጣቶችን በሃይማኖትና በበጎ ምግባር ለማነጽ፣ እንዲሁም የተቸገሩትንና ደካሞችን በመደገፍ ረገድ የተጀመሩ ዐበይት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል። ለዚህም ቅዱስ ዓላማ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የምትገኙ ምዕመናን የምታደርጉትን ያልተገደበ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አዲሱ የ2019 ዓመተ ምሕረት ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለመላው ዓለም የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና እና የበረከት ዓመት እንዲሆንልን ወደ እግዚአብሔር አምላካችን እንጸልያለን።
የዘመነ ኦሪት መጨረሻ፣ የዘመነ ሐዲስ መነሻ፣ በአጥማቂነቱ ካህን፣ የዓለምን ኃጢአት ይቅር የሚል ከእኔ በኋላ ይመጣል በማለቱ ነቢይ እና ስለክርስቶስ ሕይወቱን በመስጠቱ ሰማዕት ከሆነው ከቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት በረከት ያድለን።
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬ እና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
ዲላ/ኢትዮጵያ
