በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

በሁለት ወሩ የካህናት ሥልጠና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እስከ ፕሮጀክት ቀረጻ ድረስ መዳሰሱ በሪፖርቱ ተመላከተ!

ኤክቱስ ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም

የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የመንፈሳዊ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ዮሐንስ ምሕረቱ ለሁለት ወራት በአንዲዳ መድኃኔዓለም የአብነት ትምህርት ቤት ለሁለት ወራት በተሰጠው ሥልጠና የምርቃት መርሃግብር ሪፖርት አቅርበዋል። ኃላፊው እንዳብራሩት ሥልጠናው ከሐምሌ 7 ቀን እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ወራት በአንዲዳ መድኃኔዓለም አብነት ትምህርት ቤት የተካሄደ ሲሆን ዓላማውም የካህናቱን ቀኖናዊ፣ ዶግማዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም የአመራር፣ የማኅበረሰብ ምክርና የልማት አቅም ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ 27 ካህናት በአዳሪነት የሠለጠኑ ሲሆን 1 ካህን ከአንዲዳ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በራሳቸው ወጪ በመከታተላቸው በአጠቃላይ 28 ካህናት ሥልጠናውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። በሁለት ወራት ቆይታቸውም ትምህርተ ሃይማኖት፣ አምስቱ አእማደ ምሥጢራት፣ ነገረ ክርስቶስና ነገረ ድኅነት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትና ሥርዓት፣ ነገረ ማርያምና ነገረ ቅዱሳን፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ አንጻራዊ ትምህርተ መለኮት፣ ትምህርተ ኖሎት እና ባሕረ ሐሳብን ጨምሮ 12 ዋና ዋና መደበኛ ኮርሶችን ተምረዋል።

ከእነዚህ መደበኛ ኮርሶች ጎን ለጎን የተግባቦት፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የምክር አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ኦርቶዶክሳዊ የልጆች አስተዳደግና ጋብቻ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ቃለ አዋዲ እንዲሁም የፕሮጀክት ቀረጻና ሀብት ማሰባሰብ የክህሎትና የአስተዳደር ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል። በተጨማሪም እያንዳንዱ ሠልጣኝ ለሁለት ዙር ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት የስብከት ልምምድ ማቅረባቸውን የተከታታይ ምዘና ሲደረግበት መቆየታቸው ገልጸዋል።

ለሥልጠናው መሳካት በሀገረ ስብከቱ በበጎ ፈቃደኝነት እና በቋሚነት ከሰጡት መምህራን በተጨማሪ ከዲላ ውጭ እንደ መጋቤ ሐዲስ ግሩም፣ ላዕከ ወንጌል ያሬድ አደመ፣ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ እና ሊቀ ሊቃውንት ብርሃን ያሉ ሊቃውንት መጥተው ኮርሶችንና ሥልጠናዎችን መስጠታቸውን ገልጸዋል።

Scroll to Top