ኤክቱስ ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በዲላ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ የሕግ ታራሚዎች በተጠናከረ መልኩ በዘረጋው የትምህርት መርሃ ግብር መሠረት ላለፉት ስድስት ወራት የመንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የሕግ ታራሚዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ተመረቁ። በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በመገኘት ለተመራቂዎቹ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል።
በዕለቱ የምርቃት መርሃ ግብር ላይ መምህር ያሬድ አደመ ለቦታው የሚሆን ትምህርት በሰፊው አስተምረዋል።
ተመራቂዎቹ በስድስት ወራት የትምህርት ቆይታቸው ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ነገረ ማርያም እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ተከታተለዋል። ይህም በማረሚያ ቤት በቆዩበት ጊዜ ያገኟቸው መንፈሳዊና ሥነ-ምግባራዊ እውቀቶች ለቀጣይ ሕይወታቸው መልካም ዜጋ ሆነው እንዲወጡና ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑ ተገልጿል።
በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የዲላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኢንስፔክተር ትእግስት ሮቤ፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ኅሩያን እሸቱ ዋለ እንዲሁም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አባላት ተገኝተዋል።
በመርሃግብሩ ንግግር ያደረጉት የዲላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኢንስፔክተር ትእግስት ሮቤ የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት በሚኖራቸው ቆይታ በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲወጡ መንፈሳዊ ትምህርት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም ብፁዕ አቡነ ገሪማ ወደ ሀገረ ስብከቱ ከተመደቡ በኋላ የማረሚያ ቤት መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።
ብፁዕነታቸው በበኩላቸው ለማረሚያ ተቋሙ ምስጋና አቅርበው፣ ተመራቂዎች ያገኙትን መንፈሳዊ እውቀት በስብዕናቸውና በአኗኗራቸው በመግለጥ በበጎ መንገድ እንዲመላለሱ አባታዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል። ማረሚያ ቤቶች የቅጣት ቦታዎች ብቻ ሳይሆኑ የሥነ-ምግባር፣ የሃይማኖትና የዕውቀት መማሪያ ተቋማት እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑንም አስረድተዋል።
በመጨረሻም በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተመራቂ የሕግ ታራሚዎች የማጠናቀቂያ ምስክር ወረቀትና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን ለማረሚያ ተቋሙ፣ ትምህርቱን ላስተማሩ መምህራን እና ለወረዳ ቤተ ክህነቱ የምሥጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ መርሃ ግብሩ በብፁዕነታቸው ጸሎተ ቡራኬ ተጠናቋል።
