ኤክቱስ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም
በዲላ ከተማ አስተዳደር በተዘጋጁ 34 በተመረጡ ቦታዎች ላይ ከ94 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል የታቀደው የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ መካሄድ ጀምሯል። መርሃ-ግብሩ በዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ጸሎትና ቡራኬ የተከፈተ ሲሆን የከተማው ህብረተሰብ ከማለዳው አንስቶ በመውጣት በችግኝ ተከላው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
ብፁዕ አቡነ ገሪማ በመርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ችግኝ በመትከል አባታዊ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን ባስተላለፉት መልእክትም የጌዴኦ ማኅበረሰብ በዛፍ መትከል እና በተፈጥሮ ጥበቃ የሚታማ ሳይሆን ለዓለም አርአያ የሚሆንና ከደን ጋር አብሮ የሚኖር ማኅበረሰብ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም «በአጠቃላይ የጌዴኦ የተፈጥሮ ጥበቃ ለዓለም መሠረት የሚሆን እንዲሁም በደንብ ልናስተዋውቀው የሚገባ ቅርስ ነው» ሲሉ የአካባቢው ማህበረሰብ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ቁርኝት አጉልተው ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኢድሪ ኢርኮ በበኩላቸው «የዲላ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተፈጥሮ ጥበቃ እና በግብርና ሥራዎች ለከተማችን ሞዴል የሚሆን ደብር ነው» ሲሉ አድንቀዋል።
በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ብርሃኑ ክፍሌ፣ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ታሪኩ በየነ እና ሌሎች የከተማው አመራሮች ተገኝተው አሻራቸውን አሳርፈዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግና ተፈጥሮን በመንከባከብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ድረስ የሚቆየው ይህ የአንድ ጀንበር ችግኝ የመትከል እንቅስቃሴ ቀኑን ሙሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
