በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት

የቅዱስ ዑራኤል ዓመታዊ በዓል ብፁዕነታቸው በተገኙበት በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተከበረ!

ኤክቱስ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በተገኙበት የሊቀ መላእክት የቅዱስ ዑራኤል ዓመታዊ በዓል በዲላና ወናጎ ወረዳ ቤተ ክህነት በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

የደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያም ለዕለቱ የሚስማማ ያሬዳዊ ዝማሬ ካቀረቡ በኋላ በወረቡ መነሻነት “ለነፍሳት የቆሙ እሊህ ሊቃናት ለይቅርታ ከልዑል ዘንድ ይላካሉ” ብለው የሀገረ ስብከቱ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ማእምራን ሰሎሞን ፈጠነ በሰፊው አስተምረዋል።

በደብሩ ለሚሠሩ የልማት ሥራዎች ዲያቆን ዐቢይ የይርጋጨፌ ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሒሳብ ክፍል ኃላፊ ተከናውኗል። በተጨማሪም የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ንጉሤ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገሪማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በዓሉን በተመለከተ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን ቅዱሳን መላእክት የእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅርታ ለሰው ልጅ ፤ የሰውንም ጸሎትና ልመና ወደ እግዚአብሔር እንደሚያሳርጉ አንስተው በሰፊው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። አክለውም የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደመሆኑ ራሱን በንጽሕና እና በቅድስና ጠብቆ ይልቁንም ከአልባሌ ልማድ መራቅ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

Scroll to Top