ኤክቱስ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ገሪማ የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በዲላ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በተከበረው በዓል ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት አባታዊ ቃለ ምዕዳን ምእመናን ከሱሰኝነትና ከማይገቡ ልማዶች ወጥተው ለንስሐ ሕይወታቸው ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ብፁዕነታቸው በትምህርታቸው ወቅት «የሰው ልጅ እሞታለሁ ብሎ ዕድር ይገባል፤ እሞታለሁ ብሎ ግን ንሥሐ አይገባም» ብለው ያለውን መንፈሳዊ ድክመት በጥበብ ያስረዱ ሲሆን ሰዎች ለቀብርና ለልቅሶ ዝግጅት እንዲሁም ለሥጋዊና ለምድራዊ ነገር ትኩረት የሚሰጡትን ያህል ለነፍሳቸው መዳንና ለዘላለም ሕይወት ዝግጅት እንደማይሰጡ እና መስጠት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
አክለውም በተለይም ኦርቶዶክሳውያን ሕይወታቸውንና ሥጋቸውን ከሚያበላሹ የተለያዩ ሱሶችና ከአልባሌ ልማዶች ሙሉ በሙሉ መውጣት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመሆኑ ራሱን በንጽሕና፣ በቅድስናና በበጎ ሥነ-ምግባር በመጠበቅ በንስሐ ሊመላለስ እንደሚገባ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈው መርሃግብሩን በጸሎት ፈጽመዋል።
